የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቀጣይ ጨዋታዎች በምን መልኩ ይጠናቀቃሉ?

የ2016 የውድድር ዘመን ሊጠናቀቅ የአራት ጨዋታዎች ዕድሜ በቀረው በአሁኑ ሰዓት የሊጉ የመጨረሻ ጨዋታዎች የት ይከናወናሉ በሚለው ዙርያ ሶከር ኢትዮጵያ የተለያዩ መረጃዎችን አግኝታለኝ።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታዎች ምክንያት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 26ኛ ሳምንት ላይ መቋረጡ ይታወቃል። በቀጣይ ቀሪ አራት ጨዋታዎች በምን መልኩ ጨዋታዎች ይጠናቀቃሉ የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ሆኗል። ሶከር ኢትዮጵያ ባደረገችው ማጣራት ያገኘችውን መረጃ እንደሚያመላክተው ከሆነ የውድድሩ ባለቤት አክስዩን ማህበሩ የተለያዮ አማራጮችን አስቀምጧል።

የተቋረጠው ሊግ ውድድር ከሰኔ 6 ተጀምሮ ሰኔ 29 ፍፃሜውን እንዲያገኝ እንዲሁም የመጨረሻው የ30ኛ ሳምንት ጨዋታ ሰኔ 26 ቀን ረቡዕ ጀምሮ ቅዳሜ ሰኔ በ29 ቀን የፍፃሜውን እንዲያገኝ ሲታሰብ ይህም የሆነበት ምክንያት ደግሞ በኢትዮጵያ ዋንጫ ሰኔ 30 ቀን ተፋላሚ ለሆኑት ለወላይታ ዲቻ እና ለኢትዮጵያ ቡና ሁኔታዎችን ለማመቻቸት እንደሆነ ታውቋል።

ሌላው እና ዋናው ነገር የሊጉ ቀሪ ጨዋታዎች የት ከተማ ይካሄዳል የሚለው ጉዳይ ነው። ሶከር ኢትዮጵያ ለጉዳዮ ቅርበት ካላቸው ምንጮቻ እንዳገኘችው መረጃ ከሆነ የተለያዮ አማራጮች ተይዘዋል። በአንደኛነት አስቀድሞ በወጣው መርሐግብር መሰረት ከሆነ ከ27ኛው ሳምንት ጀምሮ ቀሪ የሦስት ሳምንት ጨዋታዎች በመዲናዋ አዲስ አበባ ለማድረግ ነበር። አሁን ባለው ሁኔታ አዲስ አበባ የማድረግ ፍላጎቶች በተለያዩ ተቋማት ዘንድ ቢኖርም ከፍላጎት ባለፈ ማረጋገጫ እስካሁን ማግኘት አልተቻለም። ከሚመለከተው አካል ፍቃድ ውጪ እንዲያውም ሶከር ኢትዮጵያ እንዳገኘነው መረጃ ከሆነ የአዲስ አበባ ስታዲየም የመብራት ፓውዛ ለማታ ጨዋታዎች የብርሀን መጠኑ አመቺ እንዳልሆነ የተገለፅልን ሲሆን መዲናዋ አሁን ውድድሮችን ከማዘጋጀት ይልቅ በቀጣይ ዓመት የውድድር ዘመን የመክፈቻ ጨዋታዎችን ለማዘጋጀት ዕቅድ እንደተያያዘ ሰምተናል። ይህን ተከትሎ አዲስ አበባ ውድደሩን የማዘጋጀት ዕድሏ ጠባብ አድርጎታል።

ሁለተኛ ተመራጭ እና የሊጉን የመጨረሻ ጨዋታ የማዘጋጀት ዕድሏ ሰፊ የሆላት ሀዋሳ ከተማ ናት። ሀዋሳ የመሆኑ ነገር አሳማኝ ያደረገው ምክንያት ሀዋሳ በቂ የሆነ የልምምድ ሜዳ በመኖሩ፣ የአየር ንብረቱ አስተማማኝ እየሆነ መምጣቱ(የዝናቡ ሁኔት እየቀነሰ በመሆኑ)፣ አብዛኘው ክለቦች ለተጫዋቾቻቸው የሰጡትን የዕፍት ጊዜ አጠናቀው ዝግጅታቸውን በዛው ሀዋሳ የጀመሩ መሆኑ እና የውድድር እና ስነሥርአት ኮሚቴ ለበላዮቻቸው እንደ መጀመርያ ምርጫ ያስቀመጧት ከተማ ሀዋሳ በመሆኗ ነው።

ሌላው ሦስተኛ ተመራጭ እንድትሆን የታሰበችው ከተማ አዳማ ስትሆን ይህም የሚሆነው ሀዋሳ ያለው የአየር ንብረቱ ዝናባማ የሚሆን ከሆነ ሜዳው ሊጨቀይ ስለሚችል ለጨዋታ አመቺ ባለመሆኑ በአስገዳጅ ሁኔታ አዳማ ከተማ በተጠባባቂነት ተይዛለች። አዳማ ከተማ ምንም እንኳን የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ውድድር እየተካሄደበት ቢሆንም ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጋር በመነጋገር የሴቶችን ሊግ ወደ ወንጂ ከተማ የመውሰድ ሀሳብ እንዳለ አውቀናል።

በአጠቃላይ የተቀመጡትን አማራጮች በመመልከት የመጨረሻውን ውሳኔ የአክስዮኑ ማኀበሩ የበላይ ጠባቂ ቦርዱ ዛሬ ወይም በቀጣዮቹ ቀናት ውሳኔ እንደሚሰጥ ይጠበቃል።