የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ | የ26ኛ ሳምንት ምርጥ 11

የ26ኛውን የጨዋታ ሳምንት መነሻ በማድረግ ይህንን ምርጥ ቡድን ሠርተናል።

አደራደር 3-4-3

ግብ ጠባቂ

አቡበከር ኑራ – ኢትዮጵያ መድን

በዚህ ሳምንት በርከት ያሉ ዒላማቸውን የጠበቁ ኳሶችን በማዳኑ ረገድ ይህ ነው ተብሎ በጉልህ የሚጠቀስ ግብጠባቂ ማግኘት አዳጋች ነበር። በአንፃራዊነት ጥቂት የሚባሉ ሙከራዎችን በጥሩ ንቃት መቆጣጠር የቻለው እና ለተከታታይ አራት ጨዋታዎች የግብ መረቡን ሳያስደፍር ወጥቶ በዕለቱ አንድ ግብ ያስተናገደውን አቡበከር ከባሕሩ ነጋሽ ጋር አፎካክረን በዚህ ሳምንትም በድጋሚ  ለመምረጥ ተገደናል።

ተከላካዮች

መድኃኔ ብርሃኔ – ሀዋሳ ከተማ

የሀዲያ ሆሳዕና የመስመር አጥቂዎች ምንም ዓይነት ጥቃት እንዳይሰነዝሩ በማድረግ በኩል የማይደክመው የመስመር ተከላካይ መድኃኔ ብርሃኔ ሚና የጎላ ነበር። በምሽቱ ጨዋታ የአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉን ታክቲክ በመተግበር ረገድ ውጤታማ የነበረው መድኃኔ የሀድያ ሆሳዕና የመስመር አጥቂዎችን በእንቅስቃሴ የጎል ምንጭ እንዳይፈጥሩ በከፍተኛ ትጋት በማሳየት የመከላከል ተግባሩን በአግባቡ በመወጣቱ በምርጥ አስራ አንድ ስብስባችን ከአስራት ቱንጆ ጋር በመፎካከር ሊመረጥ ችሏል።


ፈቱዲን ጀማል –  ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ካነሳ ትልቁን የአንበሳ ድርሻውን ከሚወስዱ ተጫዋቾች መካከል ቀዳሚው ሰው አንበሉ ፈቱዲን ጀማል ነው። ዓመቱን ሙሉ በወጥነት ቡድኑን በሜዳም ከሜዳም ውጭ በሙሉ ልብ እየመራ ያለው ፈቱዲን ፋሲል ከነማን ድል በማድረግ ከተከታያቸው መቻል ነጥባቸውን በአምስት ከፍ ባደረጉበት ጨዋታ የመከላከል ቀጠናውን ጎል ሳይቆጠርበት እንዲወጣ በማስቻል እና ቡድኑን በተረጋጋ መንገድ የመራበት ሁኔታ በምርጫ ውስጥ እንዲካተት አስችሎታል።


ሻይዱ ሙስጠፋ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ውስን በሆኑ በሚሰጡት የመጫወት ዕድሎች እራሱን ከሊጉ ጋር ለማስተዋወቅ በአዕምሮም በአካል ብቃትም በማዘጋጀት ዕድሎችን ለመጠቀም እየተጋ ያለው ወጣቱ ተስፈኛ ተጫዋች ሻይዱ ሙስጠፋ ፈረሰኞቹ ከሰባት ጨዋታ በኋላ ከናፈቃቸው ድል ጋር ሲታረቁ ትልቁን ኃላፊነት በመወጣት በመከላከሉም ረገድ እንዲሁም ወደ ፊት በመሄድም የቡድኑን የማጥቃት አቅም ለማሳደግ ያደረገው እንቅስቃሴ መልካም መሆኑን ተከትሎ ምርጫ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል።

አማካዮች

ሱራፌል ጌታቸው – ድሬዳዋ ከተማ

ድሬዳዋ ከተማ ከአስከፊው ሽንፈት አገግሞ ወደ ድል በተመለሠበት ሳምንት የአማካዩ ሚና ከፍ ያለ ነበር። የመሐል ሜዳ ክፍሉን በመቆጣጠር ለአጥቂዎች ምቹ ኳሶች ለማድረስ ጥረት ያደርግ የነበረው ተጫዋቹ ለቡድኑ የመጀመሪያዋን ግብ በፍፁም ቅጣት ምት ማስቆጠር ችሎ አንድ ግብ የሆነ ኳስ ሲያመቻች እንዲሁም በጨዋታው ጥሩ ቆይታን በማድረጉ በሳምንቱ የምርጥ ስብስባችን አካል አድርገነዋል።

ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ – ሻሸመኔ ከተማ

ሻሸመኔ ከተማ ከሊጉ ጠንካራ ቡድኖች አንዱ የሆነውን መቻልን በእጅጉ ፈትኖ አቻ በወጣበት የጨዋታ ሳምንት አንጋፋው አማካይ ጥሩ ቀን አሳልፏል ማለት ይቻላል። በተደጋጋሚ ሰንጣቂ ኳሶችን መጥኖ ሲያቀብል የነበረው ተጫዋቹ አንድ ወደ ግብነት የተቀየረ ኳስን አመቻችቶ በማቀበል እና ሁለተኛዋን ግብ ደግሞ በግሩም ሁኔታ ማስቆጠሩ ይታወሳል።

ሀይደር ሸረፋ – ኢትዮጵያ መድን

መድኖች ከዕረፍት መልስ ጠንካራ ሆነው በቀረቡበት የአዳማው ጨዋታ የቀድሞው ክለቡን የገጠመው ሀይደር አጋማሹን በጥሩ ቆይታ ቋጭቷል። ቡድኑን መሪ ያደረገች ጎልን ከዕረፍት እንደተመለሱ 63ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት ያስቆጠረው አማካዩ የመሐል ሜዳ ብልጫውን በመውሰድም ጭምር ደምቆ ውሏል።

አማኑኤል ዮሐንስ – ኢትዮጵያ ቡና

ኢትዮጵያ ቡና ስድስት ግቦች አስቆጥሮ ጣፋጭ ድል በተጎናፀፈበት ዕለት የአማኑኤል ዮሐንስ ሚና ትልቅ ነበር። ተጫዋቹ ለቡድኑ ዓይን ገላጭ የሆነች ግብ ከማስቆጠሩም ባለፈ መሐመድኑር ናስር ላስቆጠራት አራተኛ ግብ መቆጠርም ዓይነተኛ ሚና ተጫውቷል።

አጥቂዎች

ኢዮብ ገብረማርያም – ሻሸመኔ ከተማ

ሻሸመኔዎች ከመቻል ጋር አቻ በወጡበት ጨዋታ በልዩነት ነጥረው ከወጡ ተጫዋች ኢዮብ ቀዳሚው ነበር። ለመቻል ተከላካዮች በተደጋጋሚ በአንድ ለአንድ ግንኙነት ብልጫውን በመውሰድ ድንቅ የነበረው ኢዮብ ሁለተኛዋ ጎል በሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ ስትቆጠር አመቻችቶ ማቀበሉ እንዲሁም ከፈጠራቸው በርከት ያሉ የግብ አጋጣሚዎች አንፃር የስብስባችን ምርጥ ውስጥ ተካቷል።

ካርሎስ ዳምጠው – ድሬዳዋ ከተማ

ድሬዳዋ ከተማ ከሽንፈት ያገገመበትን ውጤት በጨበጠበት ሳምንት ግዙፉ አጥቂ ጥሩ የሜዳ ላይ ቆይታ ነበረው። ሁለተኛዋን ግብ ካስቆጠረ በኋላ ከፍተኛ መነቃቃትን ለቡድኑ የፈጠረው አጥቂው በመጨረሻ የተገኘችውን የፍፁም ቅጣትም ምትም በማስቆጠር ቡድኑን ውጤታማ አድርጓል።

መሐመድኑር ናስር – ኢትዮጵያ ቡና

መሐመድኑር ናስር ቡናማዎቹ በውድድር ዓመቱ በአንድ ጨዋታ ከፍተኛው ግብ በማስቆጠርም ጭምር ባሸነፉበት ጨዋታ ድንቅ እንቅስቃሴ ካሳዩት ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው። በጨዋታው ካሳየው ድንቅ እንቅስቃሴ በተጨማሪ ሁለት ግቦች አስቆጥሮ አማኑኤል አድማሱ ላስቆጠራት ግብ መነሻ የነበረው ይህ አማካይ በጨዋታው የነበረው የላቀ አስተዋጾ በሳምንቱ ምርጥ ቡድን አካቶታል። በኢትዮጵያ ዋንጫ ቡድኑን ወደ ፍፃሜ ያሻገሩ አራት ግቦች ማስቆጠር የቻለው አጥቂው በዚህ የጨዋታ ሳምንት ሁለት ግቦች ማስቆጠሩን ተከትሎ በውድድር ዓመቱ ያስመዘገባቸው ግቦች መጠን ስምንት አድርሷል።


አሰልጣኝ በጸሎት ልዑልሰገድ – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከምስረታው ጀምሮ በውጤት ረገድ ዐይቶት የማያቀውን ታሪክ ለማስመዝገብ እየታተሩ የሚገኙት ወጣቱ አሰልጣኝ በጸሎት ቡድኑን ወደ ዋንጫው እያንደረደሩትይገኛሉ። ምንም እንኳን ብዙም ያልተፈተኑበትን ፋሲል ከነማን ድል ያደረጉ ቢሆንም በዕለቱ ቡድኑ በትዕግስት ክፍቶችን እንዲያገኝ ያደረጉበት፣ የተጫዋች ቅያሪያቸው ውጤታማ መሆኑ እና የሊጉን መሪነት ከተከታያቸው መቻል በአምስት ነጥብ ያሰፉበት ውጤት በማሳካታቸው ይሄን ቡድን እንዲመሩ መርጠናቸዋል።

ተጠባባቂዎች

ባሕሩ ነጋሽ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
አሥራት ቱንጆ – ኢትዮጵያ ቡና
ሚሊዮን ሰለሞን – ኢትዮጵያ መድን
ምንተስኖት ከበደ – ሻሸመኔ ከተማ
ፍሬዘር ካሳ – ባህር ዳር ከተማ
ኢዮብ ዓለማየሁ – ሀዋሳ ከተማ
እስራኤል እሸቱ – ሀዋሳ ከተማ
ዓሊ ሱሌይማን – ሀዋሳ ከተማ
አማኑኤል አድማሱ – ኢትዮጵያ ቡና
አቡበከር ሳኒ – የት መድን