የዋልያዎቹ ተጋጣሚ ሁለት አጥቂዎቿን አጥታለች

ግንቦት 29 በሜዳዋ ኢትዮጵያን የምታስተናግደው ጊኒ ቢሳዎ ከጠራቻቸው ከሀገር ውጪ ከሚጫወቱ 25 ተጫዋቾች ሁለቱ በጉዳት ከስብስቡ ውጪ እንደሆኑ ታውቋል።

የ2026 የዓለም ዋንጫ የምድብ የማጣሪያ ጨዋታዎች ባለንበት ወር መጨረሻ የሚቀጥሉ ሲሆን በምድብ አንድ ከሚገኙ ሀገራት መካከልም ጊኒ ቢሳዎ ትጠቀሳለች። ጊኒ ቢሳዎ የዛሬ ሳምንት ሀሙስ በሜዳዋ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን የምታስተናግድ ሲሆን ለዚህ ጨዋታም ከሀገር ውስጥ ሊግ ውጪ ለሚጫወቱ 25 ተጫዋቾች ጥሪ አቅርባ ዝግጅቷን ጀምራለች።

ከሀያ አምስቱ ተጫዋቾች መካከል በሲውዘርላንድ ሊግ በሚሳተፈው ይቨርደን የሚጫወተው አጥቂው ማውሮ ቴሼራ እንዲሁም በፖላንዱ ራዶሚያክ ራዶም የሚጫወተው ሌላኛው አጥቂ እስሚራልዶ ሳ ሲልቫ ወይም በቅፅል ስሙ ጃርዴል ጉዳት በማስተናገዳቸው ከኢትዮጵያ እና ግብፅ ጨዋታ ውጪ እንደሆኑ ተመላክቷል።

የጊኒ ቢሳዎ መገናኛ ብዙሃኖች እያወጡት ባለው መረጃ የቡድኑ አዲስ አሠልጣኝ ልዊስ ቦዋ ሞርት በቴሼራ ምትክ ብቻ ለአማካዩ ማርሲያኖ ሳንካ ቻሚ ጥሪ እንዳቀረቡና ቡድኑ በ24 ተጫዋቾች ዝግጅቱን በመቀጠል ሁለቱንም ጨዋታዎች እንደሚያደርግ ተሰምቷል።