የክልል ክለቦች ሻምፒዮና የሚደረግበት ቦታ እና ቀን ታውቋል

ወደ ኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ እና ወደ ሴቶች ከፍተኛ ሊግ የሚያድጉ ክለቦች ለመለየት የሚደረገው የክልል ክለቦች ሻምፒዮና በሁለቱም ፆታ የሚደረግበት ቦታ እና ቀን ይፋ ሆኗል።

በየዓመቱ መጨረሻ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን አዘጋጅነት የሚደረገው የክልል ክለቦች ሻምፒዮና በወንድም ሆነ በሴት ዘንድሮ ይደረጋል። በወንዶች ወደ ኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ በሴቶቹ ደግሞ ወደ ከፍተኛ ሊገሰ የሚያድጉ ክለቦችን ለመለየት ሲባል የሚዘጋጀው ይህ ውድድር ዘንድሮም በርካታ ቡድኖችን ተሳታፊ በማድረግ የሚደረግበት ሀገር እና ውድድሩም የሚጀመርበትን ቀን ፌድሬሽኑ ለክልሎች በላከው ደብዳቤ አሳውቋል።

ውድድሩን እንድታስተናግድ ድሬዳዋ ከተማ የተመረጠች ሲሆን ሰኔ 22 ደግሞ እንዲጀመር ተወስኗል። ተሳታፊ የሆኑ ቡድኖች ለምዝገባ የሚከፍሉትን ገንዘብም ከፍለው በአፋጣኝ እንዲያጠናቅቁም ሲል የውድድር ዳይሬክተሬት አሳስቧል።