የዋልያዎቹ ተጋጣሚ ዝግጅቷን ጀምራለች

ከሀገር ውስጥ ሊግ ውጪ የሚጫወቱ 25 ተጫዋቾችን የመረጠችው ጊኒ ቢሳዎ በትናንትናው ዕለት ባልተሟላ ሁኔታም ቢሆን ዝግጅቷን ጀምራለች።

በ2026 አሜሪካ፣ ሜክሲኮ እና ካናዳ አዘጋጅነት ለሚከናወነው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ የአህጉራችን ሀገራት በምድቦች ተከፋፍለው የማጣሪያ ጨዋታቸውን እያደረጉ ይገኛሉ። ሀገራችን ኢትዮጵያም ከዚህ ቀደም ሁለት የምድብ ጨዋታዎችን አከናውና አንድ ሽንፈት እንዲሁም አንድ የአቻ ውጤት ያስተናገደች ሲሆን በቀጣዩ ሳምንትም ሁለት የምድብ ጨዋታዎችን ከሜዳዋ ውጪ ታከናውናለች።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጋጣሚ የሆነው ጊኒ ቢሳዎ የውድድር ዓመቱን በፉልሀም ቤት የማርኮስ ሲልቫ ረዳት ሆነው ያሳለፉትን አሠልጣኝ ልዊስ ቦዋ ሞርት በመቅጠር ለ25 ከሀገር ውስጥ ሊግ ውጪ ለሚጫወቱ ተጫዋቾች ጥሪ በማድረግ ወሳኞቹን የኢትዮጵያ እና ግብፅ ጨዋታ ሲጠባበቅ የነበረ ሲሆን በትናንትናው ዕለትም በይፋ ልምምዱን ጀምሯል።

ለጨዋታዎቹ ከተጠሩት ሀያ አምስት ተጫዋቾች አስራ ሦስቱ በቡድኑ አዲስ አሠልጣኝ ልዊስ ቦዋ ሞርት እየተመሩ በትናንትናው ዕለት ከአውሮፓ ቢሳዎ በኮሜርሻል ፍላይት ቀትር 6 ሰዓት ኦዝቫልዶ ቬራ ዐየር ማረፊያ ደርሰዋል። የቡድኑ አባላት ከሰዓት መጠነኛ ዕረፍት ካደረጉ በኋላም አመሻሽ ላይ በስታዲዮ 24 ሴቴምብሮ የመጀመሪያ ልምምድ ሰርተዋል።

ለተመልካች ክፍት በተደረገው የመጀመሪያ የልምምድ መርሐ-ግብር የልዊስ ቦው ረዳት ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው ወጣቱ አሠልጣኝ አናክሲሜኔስ ፔሬራ ከተመልካች ጋር ስታዲየም ተገኝቶ ልምምዱን ታድሞ እንደነበር ተመላክቷል። ልምምዱም ለአንድ ሰዓት ከሠላሳ ደቂቃዎች ተከናውኖ ተጠናቋል።