የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ የማጠቃለያ ውድድር ነገ ይጀመራል

አስር ቡድኖችን በሁለት ምድቦች በማቀፍ የሚደረገው የ2016 የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ የማጠቃለያ ውድድር ነገ በሀዋሳ ጅማሮውን ያደርጋል።

በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን አዘጋጅነት በሁለት ምድብ ተከፍሎ በድምሩ ሀያ አንድ ቡድኖችን ዓመቱን ሲያሳትፍ የቆየው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ከሳምንታት በፊት የዙር ውድድሮቹ በተለያዩ ከተሞች ሲደረጉ ሰነባብተው መቋጨቱ ይታወሳል። በሁለቱም ምድቦች ከአንድ እስከ አምስት የወጡ ቡድኖችን አንድ ላይ በማድረግ በአጠቃላይ አስሩን በሁለት ምድብ ከፍሎ የሚያሳትፈው የማጠቃለያ ውድድር በነገው ዕለት ግንቦት 21 በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ ላይ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ጅምሩን በማድረግ እስከ ሰኔ 10 ድረስ ይቆያል።

በምድብ አንድ ፡- ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፣ አርባምንጭ ከተማ ፣ ሀዋሳ ከተማ ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ወላይታ ድቻ ሲደለደሉ በምድብ ሁለት ፡- ሀድያ ሆሳዕና ፣ አዳማ ከተማ ፣ ኢትዮጵያ መድን ፣ መቻል እና ኢትዮጵያ ቡና ተደልድለዋል። ነገ በመክፈቻ ጨዋታ ከምድብ ሀ ሀዋሳ ከተማ 08፡00 ኢትዮ ኤሌክትሪክ በመቀጠል ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 10፡00 ከአርባምንጭ ከተማ ጋር የሚጫወቱ ይሆናል።