“ለበፊቱ ላለማድረጋችን እንደ ፌድሬሽን ኃላፊነቱን ወስደን ይቅርታ የምንጠይቅበት ጉዳይ ነው” አቶ ባህሩ ጥላሁን

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን በስሩ ለሚያዘጋጃቸው ውድድሮች ያለፉትን አራት ዓመታት ኮከብ ለሆኑ ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች ሽልማቶችን ለምን ሳይሰጥ እንደቀረ ለሶከር ኢትዮጵያ ማብራሪያ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን በስሩ የተለያዩ ውድድሮችን በየዓመቱ ሲያዘጋጅ መመልከት የተለመደ ጉዳይ ነው። የሀገሪቱን እግር ኳስ በበላይነት የሚያስተዳድረው ይህ ተቋም ውድድሮች እያዘጋጀ ቢቀጥልም ላለፉት አራት ዓመታት ላዘጋጃቸው ውድድሮች አሸናፊውን የሚለይ ዋንጫን ከመስጠት ውጪ የዓመቱ ምርጥ አሰልጣኝ ፣ የዓመቱ ኮከብ ተጫዋች እና ጎል አስቆጣሪ እንዲሁም መሰል የሆኑ የየውድድሩ ኮከቦች መሸለም ካቆመ ሰንበትበት ብሏል። በተለያዩ ዓመታትም በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ፣ አንደኛ ሊግ እንዲሁም በሴቶች ፕሪምየር ሊግ እና ከፍተኛ ሊግ ላይ የሚካፈሉ ክለቦች ያሳኩትን ድል ተከትሎ በዓመቱ መጨረሻ ይሰጣቸው የነበረው ይህ ሽልማት ሳይሰጣቸው መቅረቱን በተደጋጋሚ ለሶከር ኢትዮጵያ ሲናገሩ ቆይተዋል። “ፌድሬሽኑ ለምን ይሄንን ሽልማት መሸለም አቆመ ? ላሳካናቸው ስኬቶች የሚሰጠን የኮከብነት ሽልማት ለምን ቀረ ? በሽልማቱ ተስፋ ቆርጠናል በየጊዜው በጉጉት ብንጠብቅም ማግኘት አልቻልንም” ሲሉ በቅሬታቸው የክለብ አሰልጣኞች እና ተጫዋቾች ሲናገሩ ተደምጠዋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን በዘንድሮው የ2016 የውድድር ዘመን ካዘጋጃው ውድድሮች መካከል አንዱ ለሆነው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር በዓመቱ ያሳዩትን እንቅስቃሴ ተንተርሶ በዛሬው ዕለት ከአራት ዓመታት በኋላ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ፣ የዓመቱ ምርጥ አሰልጣኝ ፣ የዓመቱ ግብ አስቆጣሪ ፣ የዓመቱ ምርጥ ግብ ጠባቂ አና ሌሎች ሽልማቶችንም ጭምር ላለፉት አራት ዓመታት አቋርጦ ከቆየ በኋላ ዛሬ መሸለም ይጀምራል። ሶከር ኢትዮጵያ ለአራት ዓመታት ሙሉ መሸለም የሚገባቸውን ሳይሸለሙ ቅሬታዎችንም ሳይፈቱ መፍትሄም ሳይገኝለት እንዴት ይደረጋል ? ሳይሸለሙ የቆዩትን ሊሸለሙ ይችላሉ ወይ ? የሚሉ ጥያቄዎችን ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ባህሩ ጥላሁን አቅርባ ተከታዩን ማብራሪያ ተቀብላለች።

“ከዚህ ቀደም የነበረው ነገር ራሱን የቻለ ክፍተት ነበረው። ከዛ ክፍተትም ደግሞ በመማር ፌድሬሽኑ ሁሌም ቢሆን ሽልማቶች ፕላን ይደረጋል ፤ ቀጣይ እንሸልማለን። በዚህ ጊዜ እንሸልማለን ይባላል ከዛ በኋላ የተለያዩ ደራሽ የሆኑ ወይ ሌሎች ነገሮች ላይ ታተኩራለህ። በዘገየ ቁጥር ደግሞ ተሸላሚውም አንተ ሁሉን ነገር በሰዓቱ ስታደረገው ነው ደሰተኛ የሚሆነው ተሸላሚውም አካል የዘገየ ሽልማት እንደቀረ ነው የሚቆጠረው ስለዚህ ያ ጋፕ ነው። ስለዚህ አሁን ምን ፈጠርን ከአብርሀምም ጋር በደንብ ቁጭ ብለን ካወራን በኋላ ፤ በዚህ አጋጣሚ አብርሃምን ማመስገን እፈልጋለሁ ፤ የእኛ የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተራችን ማለት ነውና ‘ኦን ታይም እናድርገው በቃ ግምገማውንም ሽልማቱንም በሰዓቱ ካደረግነው እነዛ የበፊት ችግሮችን መቅረፍ እንችላለን’ የሚል አቋም በመያዝ ነው በቀጣይ የሴቶች ፕሪምየር ሊግም በዚሁ ዓይነት ተመሳሳይ ወጥነት ያለውን ነገር ነው ይዘን የምንሄደው ፣ አንደኛ ሊጉንም በዕርግጥ አንደኛ ሊጉ ተጠናቋል የእርሱንም በአጭር ጊዜ ውስጥ እናስተካክል እና ወደ ሽልማቶቹ እንገባለን። ከዚህ በፊት ያለፈውን ነገር ተመልሰን የምናይበት መንገድ አይኖርም ያለፈውን እንደ ድክመት እንደ ክፍተት ቆጥረነው በአዲስ መልኩ ነው ለመጓዝ ያሰብነው። ከዚህ ቀደም የምታስታውስ ከሆነ ሽልማቶችንም ለመስጠት የሚመለከታቸው ሰዎች በቦታው የሉም።

ለምሳሌ አንደኛ ሊግ ላይ ልንሸልም ብትል ማንን ነው ኮከብ አድርገህ የምትሸልመው ? የቴክኒክ ኮሚቴ አድርገህ አዋቅረን የመደብናቸው ሰዎች የሉም። የአሁኑን ግን አይተህ ከሆነ እያንዳንዱ ውድድር ላይ ቢያንስ የልጆቹን ፐርፎርማንስ የሚገመግሙ አካላት ነበሩ ቢያንስ መታማቶች አይኖሩትም። የበፊቱ ግን ዝም ብለህ ብትሸልም በምን መነሻ ሸለምክ ? ለሚለው መልስ ታጣለህ ለእነኚህ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት እንቸገር ነበር ሽልማቱን ሸልመን ቢሆንና ይሄንን ክፍተት አይተን ነው አሁን አስተካክለን በዚህ መልኩ የጀመርነውን። ወጥነት ባለው መልኩ ሽልማቱ ይሄዳል ለበፊቱ ላለማድረጋችን እንደ ፌድሬሽን ኃላፊነቱን ወስደን ይቅርታ የምንጠይቅበት ጉዳይ ነው።”