ኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች በዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ ተመድበዋል

ኮትዲቫር እና ዩጋንዳ ላይ ለሚደረጉ የዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎች ሦስት ኢትዮጵያን ባለሙያዎች በካፍ ተመርጠዋል።

አፍሪካን በመወከል በ2026ቱ የዓለም ዋንጫ ጨዋታ ላይ የሚሳተፉ ሀገራትን ለመለየት በአፍሪካ ዞን የሚደረገው የዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎች ከያዝነው ሳምንት የመጨረሻ ቀናት አንስቶ መከናወን የሚጀምሩ ሲሆን ሦስት ኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች በሁለት ሀገራት ላይ የሚደረጉ ጨዋታዎችን በዳኝነት እና በዳኞች ኢንስትራክተርነት እንዲያገለግሉ በካፍ ስለ መመረጣቸው ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

ቤኒን ሜዳዋ መታገዱን ተከትሎ በኮትዲቫሯ ዋና ከተማ አቢጃን በሚገኘው ስታድ ፊሊክስ ሆፕ አውቲ ቦኚ ስታዲየም ሰኞ ሰኔ 3 ከናይጄሪያ ጋር የምታደርገውን ጨዋታ ኢትዮጵያዊያኑ የፊፋ ረዳት ዳኞች ትግል ግዛው እና ተመስገን ሳሙኤል ረዳት ዳኞች ሆነው ሲመረጡ ጋቦናዊው አትቾ ፔሪ ጋይስ ላይን በመሐል ዳኝነት ካሜሮናዊው ኢፋ ኢሶማ አንቶኒ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት በጣምራ ጨዋታውን ይመሩታል። በአንፃሩ ያሚኦጎ ኮውዶጎው ዴቪድ ከቡሩኪና ፋሶ ጨዋታውን በታዛቢነት እንዲያገለግሉ ተመድበዋል።

በሌላ የማጣሪያ ጨዋታ ካፍ በሜዳዋ እንድትጫወት ፍቃድ የሰጣት ዩጋንዳ ካምፓላ በሚገኘው ማንዴላ ስታዲየም ከቦትስዋና ጋር ጨዋታዋን የምታከናውን ሲሆን ኢትዮጵያዊቷ የካፍ እና የፊፋ ኢንስትራክተር ተስፋነሽ ወረታው የኮትዲቫር ዜግነት ያላቸውን ዳኞች በገምጋሚነት (Assessor) በመሆን እንድታገለግል ጥሪ ደርሷታል።