ሁለት ተጫዋቾች ከዋልያዎቹ ስብስብ ጋር አይገኙም

ያሬድ ባዬህን በጉዳት ምክንያት በጊት ጋትኮች የተካው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጨማሪ ሁለት ተጫዋቾችንም በጉዳት ማጣቱ ታውቋል።


ለ2026 የዓለም ዋንጫ ለማለፍ የአህጉራችን ሀገራት በተለያዩ ምድቦች ተከፋፍለው የማጣሪያ ፍልሚያዎችን እያደረጉ የሚገኝ ሲሆን ከአንድ ሳምንት በኋላም የምድብ ሦስተኛ እና አራተኛ ጨዋታዎች በቀናት ልዩነት ይከወናሉ። የሀገራችን ኢትዮጵያ አሰልጣኝ የሆኑት ገብረመድኅን ኃይሌም ለ26 ተጫዋቾች ጥሪ ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን ጥሪ ካደረጉላቸው ተጫዋቾች መካከል ያሬድ ባዬህ በጊት ጋትኮች መተካቱን ቀደም ብለን የዘገብን ሲሆን አሁን ደግሞ እንደ መሃል ተከላካዩ ሁሉ ቡድኑን ማይቀላቀሉ ሁለት ተጨማሪ ተጫዋቾች እንዳሉ አረጋግጠናል።


ብሔራዊ ቡድኑን የማይቀላቀሉ ተጫዋቾችም የባህር ዳር ከተማው የመስመር አጥቂ ቸርነት ጉግሳ እና የቅዱስ ጊዮርጊሱ የመስመር ተከላካይ ሄኖክ አዱኛ መሆናቸው ሲታወቅ አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ በእነዚህ ተጫዋቾች ቦታ ተጨማሪ ተጫዋቾችን ይጠራሉ ወይስ ባሉት 24 ተጫዋቾች ይቀጥላሉ በሚለው ዙሪያ ማረጋገጫ እንዳገኘን የምናሳውቃችሁ ይሆናል።