በ8ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሲዳማ ቡና አሸንፎ ወደ መሪነቱ ሲመለስ ወላይታ ድቻ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ መሪዎቹ የተጠጉበትን ድል አስመዝግበዋል፡፡
ሀዋሳ ላይ በ9 ሰአት በተደረገው የሲዳማ ደርቢ ሲዳማ ቡና ባለሜዳው ሀዋሳ ከነማን 2-1 አሸንፎ የሊጉን መሪነት ከአንድ ሳምንት በኋላ መልሶ ተረክቧል፡፡ የሲዳማ ቡናን የድል ግቦች ያስቆጠሩት የቀድሞ የሀዋሳ ከነማ ተጫዋቾች የነበሩት ብሩክ አየለ እና አንዱአለም ንጉሴ ናቸው፡፡ ሲዳማ ከድሉ በኋላ በ14 ነጥቦች የሊጉን አናት ሲቆናጠጥ ሀዋሳ ከነማ በአንፃሩ ከ3 ተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ በወራጅ ቀጠና ተቀምጧል፡፡
ቦዲቲ ላይ መከላከያን ያስተናገደው ወላይታ ድቻ ጦሩን 1-0 በሆነ ውጤት በመርታት ወደ ሰንጠረዡ አናት መውጣቱን ተያይዞታል፡፡ የመከላከያን የዘንድሮ ያለመሸነፍ ጉዞ የገታችውን ግብ ያስቆጠረው አላዛር ፋሲካ ነው፡፡ ድቻ ከድሉ በኋላ በ13 ነጥቦች 3ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ሲችል መከላከያ ከመሪነቱ ወርዶ 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ሙገር ሲሚንቶን ያስተናገደው የአምናው ቻምፒዮን ቅዱስ ጊዮርጊስ በአዳና ግርማ እና ተቀይሮ በገባው ምንተስኖት አዳነ ግቦች 2-0 ሲያሸንፍ መልካ ኮሌ ላይ ወልድያ ዳሽን ቢራን በፍሬው ብርሃኑ ብቸኛ ግብ 1-0 በመርታት የውድድር ዘመኑን የመጀመርያ ድል አስመዝግቧል፡፡
አዳማ ላይ አዳማ ከነማ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር 3-3 በሆነ ኣቻ ውጤት ተለያይቷል፡፡ አዳማዎች በታከለ አለማየሁ እና በረከት አዲሱ ግቦች 2-0 ቢመራም ኢትዮጵያ ቡናዎቸ በኤልያስ ማሞ እና አስቻለው ግርማ ግቦች አቻ መሆን ችለው ነበር፡፡ ቢንያም አየለ ለአዳማ ግብ አስቆጥሮ አዳማን በድጋሚ መሪ ቢያደርግም በጥሩ አቋም ላይ የሚገኘው ቢንያም አሰፋ ግብ አስቆሮ ቡናን ነጥብ ተጋርቶ እንዲወጣ አድርጎታል፡፡
አርባምንጭ ላይ ታላቁ አጥቂ ዮርዳኖስ አባይ ማንፃባረቁን ቀጥሏል፡፡ አርባምንጭ በጨዋታው የመጀመርያ ደቂቃ በረከት ገብረ ፃድቅ ባስቆጠረው ግብ ለ77 ደቂቃዎች ያህል ሲመራ ቢቆይም ዮርዳኖስ አባይ በ78ኛው ደቂቃ ግብ አስቆጥሮ መብራት ኃይል ነጥብ ተጋርቶ እንዲወጣ አድርጓል፡፡ ውጤቱን ተከትሎ መብራት ኃይል በውድድር ዘመኑ ሽንፈት ያላስተናገደ ብቸኛው ቡድን ሆኗል፡፡
በ11፡30 አዲስ አበባ ስታድየም ላይ የተገናኙት ደደቢት እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካለ ግብ 0-0 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይተዋል፡፡
ሊጉን ሲዳማ ቡና በ14 ነጥቦች ሲመራ የደደቢቱ ሳሙኤል ሳኑሚ እና የኢትዮጵያ ቡናው ቢንያም አሰፋ በ6 ግቦች የሊጉን የከፍተኛ ግብ አግቢዎች ሰንጠረዥ ይመራሉ፡፡