በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 8ኛ ሳምንት ወቅታዊ የውጤት ቀውስ ውስጥ የሚገኙት ደደቢት እና ንግድ ባንክ ባደረጉት ጨወታ ካለ ግብ አቻ ተለያይተዋል፡፡ የሶከር ኢትዮጵያው ሚልኪያስ አበራ ጨዋታውን ተመልክቶ ይህንን ታክቲካዊ ትንታኔ አዘጋጅቷል፡፡
በፋና ብሮድካስትንግ ኮርፖሬት FM 98.1 ዘወትር ቅዳሜ ከ 10፡00- 12፡00 በሚቀርበው ተወዳጁ ጨዋታ ፕሮግራም ላይ ባልደረባችን የነበረው የእግር ኳስ Elite Instructor ዮሃንስ ሳህሌ (ጆኒ) የደደቢት እግር ኳስ ክለብ አስልጣኝ ሆኖ ከተሾመ በኋላ የመጀመሪያ ጨዋታውን በአዲስ አበባ ስታዲየም ከፀጋዬ ኪዳነ ማርያም ቡድን ንግድ ባንክ ጋር አካሄዷል፡፡
ደደቢት በጨዋታው ይበልጥ የማጥቃት አጨዋወት ላይ ባተኮሩ አማካዮች እና በሁለት አጥቂዎች የታገዘ 4-4-2ን የተገበረ ሲሆን ባለ ሜዳ ሆኖ የተጫወተው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደግሞ ዘንድሮ በአብዛኛው እየተጠቀመበት ያለውን 4-1-4-1 አሰላለፉን ወደ ሜዳ ይዞ ገብቷል፡፡
ምስል (1)
የደደቢት High- Line Defense (ወደ መሃል ሜዳው ቀርቦ መከላከል)
ይህ የመከላከል አጨዋወት (Defending System) ከአተገባበር ጋር በተያያዘ (Tactical Implementation) ብዙ ጠቀሜታዎች ቢኖሩት የጎንዮሽ ጉዳቶችም ያስከትላል፡፡ ተከላካዮች ወደ ላይኛው የሜዳው ክፍል ቀርበው ሲጫወቱ ከኋላቸው ሰፊ ክፍተት መተዋቸው እሙን ነው፡፡ ይህም በተጋጣሚ ቡድን የሚደረጉ የተከላካይ መስመር ሰንጣቂ ኳሶችን (Through- balls) በከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲከታተሉ ያደርጋቸዋል፡፡ ፈጣን የተጋጣሚ አጥቂዎችና አማካዮችም ለአጨዋወቱ ስጋት ናቸው በተለይ ሲስተሙ ፍጥነት በሌላቸው ተከላካዮች የሚተገበር ከሆነ፡፡ በ “ከጨዋታ ውጪ ወጥመድ” (off-side trap system) አጠባበቅ ላይ የሚፈጠር የነጠላ ተጫዋች ስህተትም ሙሉ ቡድኑን ዋጋ ያስከፍለዋል፡፡ ፈጣን አዕምሮና እግርን የሚፈልግ እንዲሁም ከፍተኛ መግባባትን የሚጠይቅ የአጨዋወት ዘይቤ ነው፡፡
በተጋጣሚ ሜዳ በማጥቃት አጨዋዋት (Attacking phase) ብዙ ተጨዋቾችን በተጋጣሚ ሜዳ በላይኛው ክፍል (Higher-up the pitch) ማሳተፍ ማስቻሉ፣ በመስመር ተከላካዮችና በመሃል ተከላካዮች መካከል የሚኖረውን ክፍተት (Channels) ማጥበቡ እንዲሁም ፈጣን በማጥቃት ወደ መከላከል የሚደረግ ሽግግርን (Defending transition) መፍቀዱ የዘይቤው አዎንታው ገፅታዎች ናቸው፡፡
ደደቢት በጨዋታው ላይ ካሳያቸው መልካም ነገሮች አንዱ የተከላካይ ተጫዋቾቹ መግባባት ነው፡፡ ተጋጣሚን ከጨዋታ ውጪ የሚያደርጉበት መንገድ የተለየ ነበር፡፡ ሁለቱ የመሃል አማካዮች (ታደለ መንገሻ እና ሳምሶን ጥላሁን) ይበልጥ የማጥቃት አዕምሮ ያላቸው (Attacking -minded) በመሆናቸው ወደፊት ሲሄዱ ተከላካዮቹ በፍጥነት በመስመሮች መካከል (Between the lines) የሚፈጠረውን ክፍተት የሚያጠቡበት መንገድና የንግድ ባንኮችን የማጥቃት ማዕዘናት የሚቀንሱበት ዘዴ የተሳካ ነበር፡፡ ፈጣኑን ፊሊፕ ዳውዚን ከጨዋታ ውጪ የሚያደርጉበት ሥልትም የተጠና መሆኑ ከተከላካዮቹ የoff – side trap አጠባበቅ ዝግጅት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው እንደሆነ እርግጥ ነው፡፡ የባንክን ጠንካራ ጎን (የቀኝ መስመሩን) ተጭነው መጫወታቸውም ሌላው ጠንካራ ጎናቸው ነበር፡፡ ይህ መስመር ንግድ ባንክ በተደጋጋሚ የማጥቃት እንቅስቃሴውን የሚያስጀምርበት ነው፡፡ ሄኖክ ኢሳያስ በሁለገብነት ሚና (Versatility role) በሜዳው የተለያዩ አቅጣጫዎች (ወደ ቀኝ ፣ ወደፊት ፣ ወደኋላ ) እየተጓዘ በንግድ ባንኮች ላይ ጫና መፍጠር ችሏል፡፡ ቡድኑም ከመሰረቱ እየተሰራ ስለመሆኑ ማሳያ ነው፡፡ አጥቂዎቹም በመከላከሉ ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡ በተለይ ዳዊት ፍቃዱ፡፡
ንግድ ባንኮች በመጀመሪያው አጋማሽ ጥንቃቄ ላይ ያተኮረ አጨዋወትን ሲተገብሩ ነበር፡፡ በታዲዮስ የተከላካይ አማካይነት ሚና ብቻ በመጫወታቸው የሚፈጠረውን የጎንዮሽ ክፍተት በመድፈን የመስመር ተከላካዮቹ (አዲሱ እና አለምነህ) ሚና የላቀ ነበር፡፡ ይህም ከማጥቃቱ በበለጠ በመከላከሉ ላይ ያመዘነ አጨዋወትን ሲከተሉ እንደነበር አመላካች ነው፡፡
ፉልባኮች ታዲዮስን ሲያግዙ የመስመር አማካዮች (ተክሉ እና ኤፍሬም) ወደ ኋላ እየተመለሱ ጥብቅ የመከላከል አስተዋፅኦ (Solid- Defending system) ያበረክቱ ነበር፡፡ ይህም አጥቂያቸው ዳውዚን በጨዋታው አብዛኛው ደቂቃ በመስመሮች ላይ እንዲንቀሳቀስ አስገድዶታል፡፡
የባንክ ፉልባኮች (አዲሱ እና አለምነህ) ወደፊት መጫወት (Overlap ማድረግ) እና በመስመሮች ላይ የቁጥር ብልጫን ማስገኘት (Over load bማድረግ) መገደቡ የቡድኑን የማጥቃት እንቅስቃሴ የጎዳው ይመስላል፡፡ ዳውዚ ለቡድኑ Width ሲያስገኝ በደደቢት የጎል ክልል ሰብረው የሚገቡ አማካዮች (Cut-inside) ጊዜ አጠባበቅና ቦታ አያያዝ (Timing and positioning) ትክክለኛ አልነበረም፡፡
ምስል (2)
2ኛው አጋማሽ
ደደቢት በዚህኛው አጋማሽ የተጫዋችና የቦታ ለውጥ በማድረግ ነው ጨዋታን የጀመረው፡፡ ታደለን በማስወጣት እና ጋብሬልን በማስገባት በጨዋታ ሒደት ከ4-4-2 ወደ 4-1-3-2 በሚቀየር ሲስተም ለመጠቀም ሞክሯል፡፡ ሳምሶንም የበለጠ ወደፊት ተጠግቶ ሁለቱን አጥቂዎች ከአማካይ ክፍሉ ጋር ለማገናኘት (Link ለማድረግ) ጥሯል፡፡ ከዚህ በኋላም ቡድኑ አስጊ ያልሆኑ መጠነኛ የጎል ሙከራዎች ሲያደርግ ታይቷል፡፡ አጨዋወቱ ላይም ሚዛናዊነትን (ማጥቃት እና መከላከልን) አክሎበታል፡፡ መስመሮች ላይ ፈጣን ሽግግር (Flank Transition) በማድረግና በቁጥር በርከት ብለው በመገኘት (Overload በማድረግ) ጫና ለመፍጠር ሞክረዋል፡፡
ንግድ ባንኮችም ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ የመስመር አማካዮቻቸውና ተከላካዮቻቸው በማጥቃት እንቅስቃሴው ላይ ተሳትፎ ሲያደርጉ ተስተውለዋል፡፡ በግራ መስመር አለምነህ የበለጠ ወደፊት እየተጠጋ ለኤፍሬም አሻሞ የማጥቃት ማዕዘናትን ሲያመቻችና ኤፍሬም Channelsን ለመጠቀም ሲጥር ታይቷል፡፡
በጨዋታው የባንኮቹ አብዱልከሪምና ሰለሞን ከዚህ በፊት በቡድኑ አጨዋወት ላይ የነበራቸው የጎላ ተፅዕኖ ሊታይ አልቻለም፡፡ ልጆቹ ለቡድኑ ማበርከት የሚችሉት ብዙ ጥሩ ጎን ቢኖራቸውም በመከላከሉ ላይ ይበልጥ እንዲያተኩሩ መደረጋቸው ይህንን ሚናቸውን እንዳናይ ሳያደርገን አልቀረም፡፡
ጨዋታውም 0 ለ 0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል ፡፡
ምስል (3)