​የቀድሞ ተጫዋቾችን ለማሰብ የተደረገው ውድድር ዛሬ ተጠናቀቀ

የመድሃኔዓለም ስፖርት ክለብ የኢትዮጵያ ባለውለተኞችን በማሰብ ያዘጋጀው የእግር ኳስ ውድድር በዙር እና በጥሎ ማለፍ ተከፍሎ ሲካሄድ ቆይቶ የጥሎ ማለፉ የፍፃሜ ጨዋታ ዛሬ ከቀኑ 5:30 በአዲስ አበባ ስታዲየም በቀድሞ የኦሜድላ እና የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ተጨዋቾች መካከል ተካሂዷል።
በርካታ የስፖርት ቤተሰብ በተገኘበት በዚሁ ጨዋታ የቀድሞ የኢትየጵያ ቡና ተጨዋቾች ቡድን የኦሜድላ የቀድሞ ተጨዋቾች ቡድንን 1-0 በማሸነፍ የዋንጫ ባለቤት መሆኑን አረጋግጧል። በሁለቱም ቡድኖች በኩል ስመጥር እና አንጋፋ ተጨዋቾች የተሳተፉ ሲሆን በእለቱ የተገኙ ተመልካቾችንም በብቃታቸው ሲያዝናኑ ውለዋል፡፡ በጨዋታው ጥሩ የፉክከር ስሜት የታየ ሲሆን ሁለቱም ቡድኖች ከእድሜያቸው መግፋት አንፃር ጉልበት ቆጥበው መሃል ሜዳ ላይ ያተኮረ አጨዋወትን ሲተገብሩም ተስተውሏል።

ህይወታቸው ያለፉ እንዲሁም በህይወት ላሉ እና በተለያዩ የስራ ዘርፎች ለሀገራቸው በጎ ስራን የሰሩ 40 የቀድሞ የሀገራችን ባለውለተኞችን ለማሰብ እና ስራቸውን ለማስታወሰ ታስቦ በተዘጋጀው ይህ ውድድር በቀጣይ በዙር ውድድር ለፍፃሜ በደረሱት የታደሰ ልጆች ቡድን እና የኢትዮጵያ ቡና የቀድሞ ተጨዋቾች ቡድን ጨዋታ አጠቃላይ የእግር ኳስ ውድድሩ እንደሚያበቃ ተነግሯል። እነዚህን ባለውለተኞች ለማሰብ የእግር ኳስ ውድድር ብቻ ሳይሆን ሀምሌ 23 የ15ኪሜ የሩጫ ውድድርም ለማድረግ እየተዘጋጁ እንደሆነም አዘጋጆቹ ገልፀዋል።

በእለቱ በክብር እንግድነት በተለያዩ የስራ ዘርፎች የተሰማሩ አንጋፋ ሰዎች የተገኙ ሲሆን የዋንጫው አሸናፊ የቀድሞ የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች ቡድን የዋንጫውን ሽልማት ከኢንጅነር ስመኘው በቀለ እጅ ነበር የተቀበሉት።

ባሳለፍነው አመት በዚሁ ውድድር የኢትዮጵያ ቡና የቀድሞ ተጨዋቾች የኤሌክትሪክ የቀድሞ ተጨዋቾችን በማሸነፍ የዋንጫ ባለቤት እንደነበር ይታወሳል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *