በክልል ክለቦች ሻምፒዮና ወደ አንደኛ ሊግ ያለፉ ቡድኖች ሙሉ ለሙሉ ታውቀዋል  

የኢትዮጵያ ክልል ክለቦች ሻምፒዮና 2ኛ ዙር ጨዋታዎች በዛሬው እለት ሲጠናቀቁ ወደ ኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ ያደጉ ክለቦች በሙሉ ተለይተው ታውቀዋል፡፡

ረፋድ 3:00 ላይ በተደረገው የእለቱ የመጀመርያ ጨዋታ መርሳ ከተማ የሽረ እንደስላሴ ቢ ቡድንን 4-2 በማሸነፍ ወደ አንደኛ ሊጉ ማደጉን አረጋግጧል፡፡ ከዚህ በመቀጠል በተደረገው ጨዋታ ደግሞ ጉለሌ ክፍለ ከተማ አሳሳ ከተማን 3-0 በመርታት ሌላኛው ወደ አንደኛ ሊግ ማደጉን ያረጋገጠ ክለብ ሆኗል፡፡

በከሰአቱ መርሃ ግብር ሁለቱ የአዲስ አበባ ተወካዮች አቃቂ ቃሊቲ ክፍለከተማ እና መርካቶ አካባቢ ተገናኝተው አቃቂ ቃሊቲ 5-2 በማሸነፍ ወደ አንደኛ ሊጉ አድጓል፡፡

ከጨዋታው ጅማሬ አንስቶ በማራኪ አጨዋወት ጫና ፈጥረው በተለይ ከቀኝ መስመር ከሚሻገሩ  ኳሶች ተደጋጋሚ አደጋ የፈጠሩት አቃቂዎች በ9ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር ሾልኮ የወጣው   ዳኛቸው አብረሃም በጥሩ አጨራረስ ባስቆጠረው ግብ ቀዳሚ መሆን ሲችሉ ከ1 ደቂቃ በኋላ ጉልላት ተሾመ ከሳጥን ውጭ አክርሮ በመምታት መሪነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል። በ22ኛው ደቂቃ ደግሞ በፈጣን መልሶ ማጥቃት ይዘውት የመጡትን ኳስ ፀጋዬ በኃይሉ አስቆጥሮ የአቃቂን መሪነት ወደ 3 ከፍ አድርጓል።
ከ2 ደቂቃዎች በኋላ የመርካቶው ጋሻው ሐሮን ከሳጥን ውጭ በማራኪ ሁኔታ መትቶ በማስቆጠር ልዩነቱን ማጥበብ ቢችልም ቀልብን ሳቢ እና ማራኪ ሆኖ በቀጠለው ጨዋታ ከ3 ደቂቃዎች በኋላ ከቅጥት ምት ብሩክ እንዳለ ያሻገውን ኳስ አቡበክር በድሩ አስቆጥሮ የአቃቂን መሪነት ወደ በድጋሚ ከፍ አድርጓል።

በሂደት በመጠኑ የጨዋታ መነቃቃት እያሱ የመጡት መርካቶዎች በ36ኛው ደቂቃ ወደ ግብ የተሞከረባቸውን ኳስ በአግባቡ ማራቅ ያልቻሉትን ኳስ ጋሻው ሐሮን አግኝቶ በቺፕ በማስቆጠር ልዩነቱን ማጥበብ ችሏል፡፡ ሆኖም በ45ኛው ደቂቃ ከቅጣት የተሻገረውን ኳስ ወንዲለን አስፋው አስቆጥሮ የአቃቂን የግብ ልዩነት ወደ ቦታው በመመለስ ወደ መልበሻ አምርተዋል።

ከእረፍት መልስ መርካቶ የጨዋታ ብልጫ ወስደው ተጭነው ለመጫወት ቢሞክሩም የአቃቂን ጠንካራ የመከላከል አጥር ማለፍ አልቻሉም። አቃቂዎች በአንፃሩ በመስመር በኩል በተለይም በግራ በኩል በጉልላት ተሾመ አማካኝነት አደጋ ለመፍጠር ሞክረዋል። ከእረፍት በፊት 7 ግቦችን ያስተናገደው ጨዋታም በሁለተኛው አጋማሽ ግብ ሳይስተናገድበት በአቃቂ 5-2 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ አቃቂዎች በሜዳ ከተገኘው የወልድያ የጁ ፍሬ ደጋፊዎች ጋር ደስታቸውን ገልፀዋል።

በእለቱ የማሳረጊያ መርሀ ግብር የጁ ፍሬ ወልድያ ሐረማያ ዩኒቨርሲቲን 1-0 በመርታት ወደ አንደኛ ሊግ ማደጉን ያረጋገጠ ስምንተኛ ክለብ ሆኗል፡፡ በርካታ የወልድያ ነዋሪ ተገኝቶ በታደመበት ጨዋታ  ገና ከጅምሩ ጫና የፈጠሩት ወልድያዎች በ1ኛው እኛ 2ኛው ደቂቃ በፍፁም እና ኑርዬ አማካኝኘት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች አድርገዋል።

በተደጋጋሚ የሀረማያ የአደጋ ክልል ሲፈትሹ የነበሩት የየጁ ፍሬዎች በ21ኛው ደቂቃ በፍፁም ኃይሉ ጥሩ አጨራረስ የሜዳውን ድባብ ያሞቀ ግብ አስቆጥረው ቀዳሚ መሆን ችለዋል።

ከእረፍት መልስ ተመጣጣኝ የሚባል እንቅስቃሴ የተስተዋለ ሲሆን የሙከራ ብልጫውን ግን የየጁ ፍሬዎች ወስደዋል። በ75ኛው ደቂቃ በወልድያ ተከላካዮች እና ግብ ጠባቂ በተፈጠረ አለመግባባት ሐረማያ አቻ የሚያደርጋቸው እድል ቢያገኙም በተጫዋቾች ርብርብ ከሽፏል። በጭማሪ 4 ደቂቃዎች ውስጥ ሐረማያዎች ተጭነው ቢጫወቱም በየጁ የተደራጀ መከላከል ከሽፎ ጨዋታው በየጁ ፍሬ ወልድያ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ወደ ኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ ማለፋቸውን ያረጋገጡ ክለቦች 

ሺንሺቾ ከተማ ፣ ሰንዳፋ በኬ ፣ ድሬዳዋ ኮተን ፣ ናኖ ሁርቡ ፣ መርሳ ከተማ ፣ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለከተማ ፣ ጉለሌ ክፍለከተማ ፣ የጁ ፍሬ ወልዲያ

[table id=381 /]

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *