የቢንያም በላይ ክለብ ስኬንደርቡ በዩሮፓ ሊግ ወደ ምድብ አለፈ

ስኬንደርቡ ኮርሲ የክሮሺያውን ሃያል ክለብ ዳይናሞ ዛግሬብን ከሜዳው ውጪ ባስቆጠረው ግብ በመጣል በታሪኩ ለሁለተኛ ግዜ ለዩሮፓ ሊግ የምድብ ድልድል ማለፍ ችሏል፡፡ በጨዋታው ላይ የአልባኒያው ክለብን ከሁለት ሳምንት በፊት ከሁለት ሳምንት በፊት በሶስት አመት ውል የተቀላቀለው ኢትዮጵያዊው አማካይ ቢኒያም በላይ በተጠባባቂ ወንበር ላይ ነበር፡፡

በኤልባሳን አሬና በተደረገው ጨዋታ ክለቦቹ ያለግብ ጨዋታቸውን ያጠናቀቁ ሲሆን ከሳምንት በፊት ዛግሬብ ላይ የ1-1 ውጤትን ይዞ የመለሰው ስኬንደርቡ ከሜዳው ውጪ ባስቆጠረው ግብ ታግዞ ወደ ምድብ ድልድሉ ማለፍ ችሏል፡፡ የጨዋታውን የመጨረሻ 17 ደቂቃዎች ማሊያዊው የአጥቂ አማካይ ባካሪ ኒማጋ በሁለት ቢጫ ከሜዳ በመውጣቱ ስኬንደርቡ በ10 ተጫዋቾች ጨዋታውን ለመጨረስ ተገዷል፡፡

 

ስኬንደርቡ በ2015 የቻምፒየንስ ሊግ ምድብ ውስጥ ለመግባት ከጫፍ ደርሶ በዳይናሞ ዛግሬብ በአጠቃላይ ውጤት 6-2 ተሸንፎ ከውድድር ተሰናብቷል፡፡ ስኬንደርቡ የዩሮፓ ሊግ የምድብ ተሳታፊነቱን ለማረጋገጥ ዳይናሞ ዛግሬብን ጨምሮ የአንዶራውን ሳንት ሁሊያ፣ የካዛኪስታኑን ካይራት እና የቼክ ሪፐብሊኩን ምላድ ቦልስላቭን መርታት ነበረበት፡፡ ቢኒያም ምንም እንኳን ከዳይናሞ ዛግሬብ ጋር በነበረው ጨዋታ ተጠባባቂ የነበረ ቢሆንም መስከረም በሚጀመረው የአልባኒያ ሊግ በክለቡ የመሰለፍ እድል እንደሚያገኝ ይጠበቃል፡፡

ስኬንደርቡ አርብ ሞናኮ ላይ በሚደረገው የዩሮፓ ሊግ የምድብ ድልድል ቋት 4 ላይ ይገኛል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *