ሲዳማ ቡና ሁለት ተጫዋቾች አስፈርሟል

በክረምቱ የዝውውር መስኮት በርካታ ተጫዋቾች የለቀቁበት ሲዳማ ቡና ምስጋናው ወልደ ዮሀንስ እና ኢኳቶሪያል ጊኒያዊው ቤን ማማዱ ኮናቴን አስፈርሟል፡፡

በትውልድ አይቮሪኮስት በዜግነት ኢኳቶሪያል ጊኒያዊው የተከላካይ አማካይ ቤን ኮናቴ በአንድ አመት ውል ሲዳማ ቡናን ተቀላቅሏል፡፡ የ29 አመቱ ኮናቴ በአይቮሲኮስት ፣ ቡርኪናፋሶ ፣ ኢክቶሪያል ጊኒ ፣ ባልሬይን ፣ ኦማን ፣ ኢራቅ ክለቦች ተዟዙር መጫወት የቻለ ሲሆን የተጠናቀቀውን የውድድር አመት በቆጵሮሱ ክለብ ደሞሉፒናር አሳልፏል፡፡ ከ2011-2014 ድረስም በኢኳቶርያል ጊኒ ብሔራዊ ቡድን ተጫውቷል፡፡

ሌላው ለክለቡ የፈረመው የመስመር አማካዩ ምስጋናው ወልደዮሀንስ ነው፡፡ ምስጋናው በድሬዳዋ ከተማ ለ6 ወራት ከቆየ በኋላ ሁለተኛውን ዙር በሀዋሳ ከተማ ያሳለፈ ሲሆን ከሰአት ላይ ፊርማውን ሙሉ ለሙሉ አጠናቆ ክለቡን የሚቀላቀል ይሆናል፡፡

ሲዳማ ቡና እስካሁን 10 ተጫዋቾችን ማስፈረም የቻለ ሲሆን ተጨማሪ ተጫዋቾችን ለማስፈረም እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የክለቡ ፕሬዝዳንት አቶ መንግስቱ ሳሳሞ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ የይርጋለሙ ክለብ የቅድመ ውድድር ዘመን ዝግጅቱን እሁድ እንደሚጀምር ይጠበቃል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *