የኢትዮጵያ ሊጎች የሚጀመሩባቸው ቀናት ታውቀዋል

በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አወዳዳሪነት የሚካሄዱት ሊጎች (ፕሪምየር ሊግ ፣ ከፍተኛ ሊግ ፣ አንደኛ ሊግ ፣ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ፣ ሀ-20 ፕሪምየር ሊግ ፣ ሀ-17 ፕሪምየር ሊግ) መቼ እንደሚጀመሩ ታውቀዋል፡፡

ፕሪምየር ሊግ

16 ክለቦች የሚካፈሉበት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከዚህ በፊት በድረገጻችን እንደገለፅነው ጥቅምት 4 ቀን 2009 የሚጀመር ሲሆን ከሊጉ መጀመርያ ቀን ቀደም ብሎ የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ በሊጉ ቻምፒዮን ቅዱስ ጊዮርጊስ እና በጥሎ ማለፉ አሸናፊ ወላይታ ድቻ መካከል መስከረም 25 እና 27 ይደረጋሉ፡፡

ከፍተኛ ሊግ

በሁለት ምድብ ተከፍሎ 32 ክለቦችን የሚያሳትፈው የ2010 ከፍተኛ ሊግ ካለፉት አመታት በተለየ ቀደም ብሎ ጥቅምት 11 ላይ ይጀመራል፡፡ በየምድቦቹ የሚደለደሉት ክለቦች እና የ2009 ሪፖርት የሚቀርቡበት ቀንም ወደፊት ይገለጻል ተብሏል፡፡

ሴቶች ፕሪምየር ሊግ

በተጠናቀቀው የውድድር አመት በነበረው አካሄድ ወይም አዲስ አካሄድ እንደሚጠቀም በውል ያልታወቀው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የ2010 የውድድር ዘመን ጥቅምት 17 እንደሚጀምር ታውቋል፡፡ ከሊጉ መጀመር በፊት በሊጉ አሸናፊ ደደቢት እና ጥሎ ማለፉ አሸናፊ ሀዋሳ ከተማ መካከል የሚደረገው የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ መካሄድ አለመካሄዱ ግን የታወቀ ነገር የለም፡፡

አንደኛ ሊግ

በ5 ምድቦች ተከፍሎ ከ50 በላይ ክለቦች የሚካፈሉበት የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ ጥቅምት 18 ይጀመራል ተብሏል፡፡

ከ20 አመት በታች ፕሪምየር ሊግ

ዘንድሮ የተጀመረው የ20 አመት በታች ፕሪምየር ሊግ የቀጣይ አመት ውድድሩን ህዳር 2 ላይ ይጀምራል፡፡ የተስፋ ቡድን ያልነበራቸው የፕሪምየር ሊጉ ክለቦችም በዚህ ውድድር ላይ ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ከ17 አመት በታች ፕሪምየር ሊግ

በሁለት ምድብ ተከፍሎ የሚደረገው የ17 አመት በታች ፕሪምየር ሊግ ህዳር 9 ይጀመራል፡፡

ውድድሮች የሚጀመርባቸው ቀናት ቀደም ብለው ለክለቦች ማሳወቁ ባለፉት ጊዜያት ያልተለመደ እንደመሆኑ እንደመልካም ተግባር ቢወሰድም ከዚህ ቀደም ውድድሮች በታሰበባቸው ቀናት እንዳይጀምሩ የነበሩትን መሰናክሎች ፌዴሬሽኑ በአግባቡ መርምሮ በቀሩት ቀናት በመስራት በታቀደው ቀን ውድድሮች ቢደረጉ መልእክታችን ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *