የይድነቃቸው ተሰማ መታሰብያ የታዳጊዎች ውድድር መካሄዱን ቀጥሏል

የኢትዮዽያ እና የአፍሪካ እግርኳስ ባለ ውለታ እና አባት በሆኑት ክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ስም የተሰየመውና የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማሕበር ለ12ኛ ተከታታይ አመት ያዘጋጀው ውድድር እድሜያቸው 14-16 አመት በሆኑ ታዳጊዎች መካከል ጀሞ አካባቢ በሚገኘው የዶንቦስኮ ሜዳ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

በመጀመርያው ምዕራፍ የውድድር መርሐ ግብር ከነሐሴ 6 እስከ 15 ድረስ ወደ ምድብ ድልድል የሚገቡትን ቡድኖችን ለመለየት በ82 ቡድኖች መካከል የማጣርያ ውድድር ተካሂዶ ወደ ምድብ ድልድል የሚቀላቀሉ 32 ቡድኖች ታውቀዋል።

አስቀድመው በክለብ ታቀፈው በተለያዩ ውድድሮች ይሳተፉ የነበሩ ቡድኖች የሚገኙበት በአራት ምድብ የተከፈሉ 17 ቡድኖች ሲገኙ በሌላኛው ምድብ ደግሞ በየትኛውም ውድድር ላይ መካፈል ያልቻሉ ቡድኖች ውስጥ ደግሞ በሦስት ምድብ ተከፍለው 15 ቡድኖች ይገኛሉ።

ውድድሩ በቀጣዮቹ ቀናት በሁለት ሜዳ በቀን አራት ጨዋታዎች እየተካሄደ ቀጥሎ ዻጉሜ አራት ቀን ውድድሩ ፍፃሜውን እንደሚያገኝ ለማወቅ ችለናል።

ትላንት በነበረው የምድብ የመጀመርያ ጨዋታ እንደተከታተልነው ተስፈኛ እና የተስጦ ባለቤት የሆኑ ታዳጊዎች የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ስንመለከት እንደነዚህ ያሉ የታዳጊ ውድሮች ምን ያህል ጠቀሜታ እንዳላቸው መገመት ይቻላል። ለዚህም ማሳያ የሚ ነው ደግሞ ምንተስኖት አዳነ ፣ ናትናኤል ዘለቀ ፣ ሳምሶን ጥላሁን ፣ ኤልያስ ማሞ ፣ ሳላዲን በርጌቾ ፣ አህመድ ረሺድ ፣ አቡበከር ሳኒ ፣ ዮሴፍ ዳሙዬ እና ሌሎች ዛሬ በክለብም ሆነ በብሔራዊ ቡድን ሀገርን ወክለው እየተጫወቱ የሚገኙ ተጨዋቾችን ያፈራ ውድድር መሆኑ ነው ። በዚህ ረገድ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ያለፉትን 12 አመታት ይህን ውድድር በክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ መታሰቢያነት ማዘጋጀቱ አድናቆት የሚቸረው ነው።

ሶከር ኢትዮጵያ በቀጣይ ቀናት የውድድሩን አጠቃላይ ጉዞ እየተከታተለኝ ወደ እናንተ የምታደርስ መሆኗን ከወዲሁ ትገልፃለች።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *