​” ተጫዋቾቻችን በጨቀየ ሜዳ ላይ ተጫውተው እንዲጎዱ አንፈልግም” አቶ አብነት ገብረመስቀል

በአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሚዘጋጀው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የረጅም ጊዜ ተሳታፊ የሆነው ቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ በዚህ አመት ላይ በሚደረገው ውድድር ላይ ላይሳተፍ እንደሚችል የክለቡ ቦርድ ሊቀመንበር አቶ አብነት ገ/መስቀል ከጠቅላላው ጉባኤው መጠናቀቅ በኋላ ለሶከር ኢትዮዽያ በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል፡፡  

ሲቲ ካፕን በተመለከተ ብዙ ጊዜ አይተነዋል፡፡ እኛ በአሁኑ ሰአት ልዩ ዝግጅት እያደረግን ያለነው ለአፍሪካ ውድድር ነው ፣ ስብስባችንም ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ እንዲያውም ለአሰልጣኞቻችን ትልቅ ራስ ምታት የሚሆን ስብስብ ነው ያለን። ስለዚህ እኛ ሲቲ ካፕ ውስጥ ገብተን የምንጎዳበት ምክንያት የለም ፤ ተጫዋቾቻችን በጨቀየ ሜዳ ላይ ተጫውተው እንዲጎዱም አንፈልግም፡፡” በማለት ክለቡ በአአ ሲቲ ካፕ ላይ ላይሳተፍ እንደሚችል ጠቁመዋል።

የአአ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሰሞኑን በተደጋጋሚ የአዲስ አበባ ስታድየም ሜዳ  ያለበትን ሁኔታ በአካል በመገኘት ሲመለከት የቆየ ሲሆን የክረምቱ የዝናብ ሁኔታ እየቀነሰ የሚመጣ ከሆነ ሜዳውን ለጨዋታው ምቹ እንዲሆን የተለያዩ ስራዎችን እንደሚሰራ ገልጿል፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስን ውሳኔ ለማስቀየርም ከክለቡ የቦርድ አመራር ጋር ውይይት ሊያደርግ እንዳሰበ ሰምተናል።

የአአ ከተማ ዋንጫ ላይ የሚሳተፉ ክለቦች እነማን እንደሆኑ ማረጋገጫ ያልተገኘ ሲሆን በደቡብ ካስቴል ዋንጫ ላይ እየተሳፉ የሚገኙት ኢትዮዽያ ቡና እና ፋሲል ከተማ መስከረም 27 ይጀመራል ተብሎ በተገመተው ውድድር ላይ ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሎ ይጠብቃል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *