​የ17 አመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን አዳዲስ ተጫዋቾችን አካቶ ዝግጅቱን ቀጥሏል

በ2018 ዩራጓይ ለምታስተናግደው ከ17 አመት በታች የአለም ዋንጫ ማጣርያ ከኬንያ ጋር ጥቅምት ወር መጀመርያ ላይ ለማድረግ ሲዘጋጅ የነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በኬንያ ራሷን ከውድድሩ ማግለል ምክንያት ጨዋታ ባያደርግም ለቀጣይ ዙር ማጣርያ ዝግጅት ማድረጉን ቀጥሏል፡፡ 

በአሰልጣኝ ሰላም ዘርአይ የሚመራው ቡድኑ ለ36 ተጨዋቾች ጥሪ በማድረግ ዞላ ኢንተርናሽናል ሆቴል ማረፊያውን በማድረግ በወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ሜዳ ልምምዱን እያደረገ ይገኛል፡፡ ቡድኑ በቀጣይ የማጣርያ ዙር ናይጄርያን እስከሚገጥምበት ህዳር ወር መጨረሻ ድረስ እንዴት ባለ ሁኔታ እንደሚቆይ ለማወቅ ልምምዳቸውን ወደሚሰሩበት ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ባቀናንበት ወቅት ቡድኑ አስቀድሞ ጥሪ ከተደረገላቸው 36 ተጫዋቾች መካከል14 ተጨዋቾች ሲቀነሱ ከወጣቶች አካዳሚ 15 አመት በታች ቡድን እና ከደደቢት 4 ተጨዋቾችን በመጨመር በጥቅሉ 25 ተጨዋቾችን በመያዝ ዝግጅቱን እያደረገ ይገኛል።

ስለ ቡድኑ ቀጣይ ቆይታ እና ዝግጅት አስመልክቶ አሰልጣኝ ሰላም ዘራይ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት እስከ ጨዋታው መዳረሻ ተሰባስቦ እንደማይቆይ ገልጸዋል፡፡ ” ተጫዋቾቹ ከዚህ በኋላ በደንብ እስክናውቃቸው ድረስ ከእኛ ጋር ለአንድ ሳምንት የሚቆዩ ይሆናል፡፡ በመቀጠል ለሁለት ሳምንት ወደ ቡድኖቻቸው አምርተው እንዲዘጋጁ ካደረግን በኋላ ተመልሰው ጥሪ ተደርጎላቸው ለአንድ ሳምንት ሆቴል ገብተው በሚቆዩበት ወቅት የወዳጅነት ጨዋታዎች አድርገን ተመልሰው ወደ ክለብ ውድድሮች እንዲገቡ እናደርጋለን፡፡ የጨዋታው መቃረቢያ ሲደርስ ደግሞ ለሦስት ሳምንት ያህል ወደ መደበኛ ዝግጅት እንገባለን፡፡” ብለዋል፡፡

አሰልጣኝ ሰላም የኬንያው ጨዋታ መቅረቱ በቡድኑ ላይ የሚያሰከትለው ተፅዕኖም አብራርተዋል፡፡  “የነበረን የዝግጅት ወቅት አነስተኛ በመሆኑ ልንቸገር እንችላለን ብለን አስበን ስለነበር እንደ ጠቀሜታ እንወስደዋለን፡፡ የዛኑ ያህል ኢንተርናሽናል ጨዋታዎች አለማድረጋችን ጉዳት ቢሆንም አሁን ለቀጣዩ ጨዋታ በበቂ ሁኔታ እንድንዘጋጅ እድል ሰጥቶናል፡፡”

የኢትዮዽያ ከ17 አመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን በአንደኛው ዙር ማጣርያ ከናይጄርያ አቻው ጋር የመጀመርያ ጨዋታውን ህዳር ወር መጨረሻ ላይ (ቀኑ አልታወቀም) የሚያደርግ ይሆናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *