​የከፍተኛ ሊግ ክለቦች ዝግጅት – ወልቂጤ ከተማ

የወልቂጤ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ለ2010 የውድድር ዘመን ዝግጅቱን በሀዋሳ ኮረም ሜዳ ላይ በቀን ሁለት ጊዜ በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡

ከተመሰረተ ረዘም ያለ ጊዜን ያስቆጠረው ወልቂጤ ከተማ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ወደ ከፍተኛ ሊጉ ባደገበት አመት እስከመጨረሻው ሳምንት የዘለቀ ጠንካራ ፉክክር በማድረግ ከፕሪምየር ሊጉ ለጥቂት እንደመቅረቱ በዘንድሮው አመት ወደ ፕሪምየር ሊግ ለማደግ ከሚፎካከሩ ክለቦች አንዱ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ወልቂጤ ከተማ እስከአሁን ድረስ ቋሚ የሆነ ስራ አስኪያጅና የቴክኒክ ባለሙያ የሌለው ሲሆን ክትትል እና ድጋፍ እንዲሁም በተደጋጋሚ የፋይናንስ እጥረት ምክንያት በየውድድር አመቱ ፈተና ሲያጋጥመው ይስተዋላል፡፡ ክለቡ ይህም ችግር ቢኖርበትም ከባለሀብቶች እና ከከተማው አስተዳደር በሚደረጉ ድጎማዎች ራሱን እየገነባ ይገኛል፡፡

የቡድኑ አባላት በተለያየ ትጥቅ ቅድመ ውድድር ዝግጀታቸውን እያከናወኑ ይገኛሉ

ወልቂጤ ከተማ በዋና አሰልጣኙ አዲሴ ካሳ እና በምክትላቸው አብዱልሀኒ ተሰማ እየተመራ  ከመስከረም 3 ጀምሮ በሀዋሳ ዝግጅቱን እያከናወነ ይገኛል፡፡ ከሀዋሳ ከተማ፣ ሲዳማ ቡና እና ሀዋሳ ከተማ ወጣት ቡድን ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታ ማድረጉም ታውቋል፡፡

ክለቡ ካለፈው አመት ስብስቡ 5 ተጫዋቾችን በአቋም መውረድ ምክንያት ሲያሰናብት 2 ተጫዋቾች ውል ቢኖራቸውም ከሌላ ክለብ የተሻለ ጥቅም ስለቀረበላቸው አሳልፎ ሰጥቷል፡፡ 20 ተጫዋቾች የአንድ አመት ቀሪ ውል ያላቸው ሲሆን ለ3 ተጫዋቾችን የሙከራ እድል ሰጥቶ 7 አዳዲስ ተጫዋቾችን ማስፈረም ችሏል፡፡

የክለቡ አዳዲስ ፈራሚዎች

አዲስ ፈራሚዎች 

ግብ ጠባቂ ፡ ሙና በቀለ (ሀምበሪቾ)

ተከላካይ፡ ግሩም አንተነህ (ወልዲያ)

አማካዮች፡ ቢኒያም ግርማ (ወሎ ኮምቦልቻ)፣ ካሳሁን ገ/ሚካኤል (ካፋ ቡና)

አጥቂዎች፡ ብሩክ ክንፈ (ነገሌ ቦረና )፣ ሐብታሙ ያለው (ነገሌ ቦረና)፣ ትዕዛዙ መንግስቱ (ጅማ አባጅፋር)

ከግራ ወደ ቀኝ: አብዱልሀኒ ተሰማ (ረዳት አሰልጣኝ) እና አዲሴ ካሳ (ዋና አሰልጣኝ)

ክለቡ በአዲሱ የውድድር አመት ክፍተቱን ደፍኖ በመቅረብ ወደ ፕሪምየር ሊግ ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን የክለቡ አሰልጣኝ የሆኑት የቀድሞ የሀዋሳ ከተማ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች አዲሴ ካሳ ተናግረዋል፡፡ “ዝግጅታችን ጥሩ ነው፤  ካለፈው አመትም የተሻለ ነው፡  ቡድኑ አምና ገና ከአንደኛ ሊግ የመጣ እንደመሆኑ አዲስ የነበረ ቡድን ነው፡፡ አሁን በነበሩበት ክፍተቶች ላይ በርካታ ስራ እየሰራን ነው፡፡ ተጫዋቾቼ ላይ በደንብ መስራት ያስፈልገኛል፡፡ በአጠቃላይ ያለፈውን አመት ስህተት አርመን የተሰጠንን ኃላፊነት ለመወጣት እንሞክራለን፡፡ ወደ ሊጉ በመቀላቀልም ደጋፊዎቻችንና አመራሩን ለማስደሰት አቅደናል፡፡” ብለዋል፡፡

ወልቂጤ ከተማ በዘንድሮው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ በምድብ ለ የተደለደለ ሲሆን ጥቅምት 25 በሚጀመረው ውድድር የመጀመሪያ ጨዋታውን በሜዳው ከናሽናል ሲሚንቶ ጋር ያደርጋል፡፡ ከዋናው ውድድር በፊት ደግሞ ከጥቅምት 11 ጀምሮ በሚካሄደው አመታዊው የደቡብ ክልል የከፍተኛ ሊግ ክለቦች ካስቴል ዋንጫ ላይ የሚካፈል ይሆናል፡፡

በከፍተኛ ሊጉ ከሚገኙ ክለቦች መካከል በክረምቱ ባደረጉት እንቅስቃሴ እና ያለፈው አመት ባስመዘገቡት ውጤት መሰረት ዘንድሮ ጠንካራ ተፎካካሪ ሊሆኑ የሚችሉ ሌሎች ክለቦችን ዝግጅት በቀጣይ ይዘን እንመለሳለን፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *