​የኦሮሚያ ዋንጫ ሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተፈፅመዋል

በሰበታ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው የኦሮሚያ ዋንጫ ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች ተደርገው በተመሳሳይ የአቻ ውጤት ተጠናቀዋል፡

በ8፡00 ሰበታ ከተማ ከ ለገጣፎ ለገዳዲ ያገናኘው ጨዋታ ያለግብ ተጠናቋል፡፡ በርካታ ተመልካች በታደመው በዚህ ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች ባለፈው እሁድ ይዘው ከቀረቡት ስብስብ በርካታ ለውጥ አድርገው ቀርበዋል፡፡

እምብዛም የግብ ሙከራ ባልታየበት የመጀመርያ አጋማሽ በ20ኛው ደቂቃ ላይ ኤፍሬም ቀሬ አክርሮ ወደ ግብ የመታው ኳስ አግዳሚውን የመለሰበት ሙከራ የሚጠቀሰ ነው፡፡

ከዕረፍት መልስ ሰበታ ከተማዎች ተጭነው የተጫወቱ ሲሆን በ53ኛው ደቂቃ ዜናው ፈረደ የለገጣፎን ተካላካይ አታሎ ወደ ግብ የመታው ኳስ እንደመጀመሪያው አጋማሽ ሙከራ ሁሉ የግቡን አግዳሚ ገጭቶ የተመለሰበት ኳስ ሰበታን ወደ ድል ልትመራ የምትችል አጋጣሚ ነበረች፡፡

በ10፡00 ጅማ አባቡና ከ ኢትዮጵያ መድን ያደረጉት ጨዋታ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡

ጨዋታው ከመጀመርያው በተሻለ ፈጣን እንቅስቃሴ የታየበት እና ሁለቱም ቡድኖች የግብ ዕድሎችን የፈጠሩበት ነበር፡፡ በ9ኛው ደቂቃ ላይ አዲሱ ናይጄርያዊ ፈራሚ አዳም ሣሙኤል ላይ በተሰራው ጥፋት የተገኘው ቅጣት ምት አዳነ አየለ ወደ ግብነት በመለውጥ መድንን ቀዳሚ ማድረግ ቢችልም በ 31ኛው ደቂቃ በድሉ መርዕድ ላይ  ላይ በተሰራው ጥፋት የተገኘውን ቅጣት ምት ሐይደር ሸረፋ ወደ አክርሮ በመምታት የመድን ግብ ጠባቂ ስህተት ታክሎበት ጅማ አባ ቡነ አቻ መሆን ችሏል፡፡

ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ የደረጃ ሠንጠረዡ ይህንን ይመስላል

1. ለገጣፎ ለገዳዲ  2 (+1) 4

2. ሰበታ ከተማ       2 (0) 2

3. ጅማ አባቡና       2 (0) 2

4. ኢትዮጵያ መድን  1 (1) 1

የኦሮሚያ ዋንጫ ሐሙስ በሚደረጉ ጨዋታዎች ይቀጥላል፡፡

8፡00 ሰበታ ከተማ ከ ኢትዮጵያ መድን

10፡00 ጅማ አባቡና ከ ለገጣፎ ለገዳዲ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *