ሰበር ዜና: ባምላክ ተሰማ የቻምፒየንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታን እንዲመራ ተመረጠ

ኢትዮጵያዊው የፊፋ ኢንተርናሽናል የመሃል ዳኛ ባምላክ ተሰማ በ2017 የቶታል ካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የፍፃሜ የመጀመሪያ ጨዋታ እንዲመራ መመረጡን የአህጉሪቱ የበላይ እግርኳስ አስተዳዳሪ አካል አስታውቋል፡፡ ቅዳሜ በሚደረገው የፍፃሜ ጨዋታ ታላቁ የግብፅ ክለብ አል አሃሊ እና የሞሮኮው ዋይዳድ ካዛብላንካ የሚጫወቱ ሲሆን የመጀመሪያው ዙር በአሃሊ ሜዳ በመጪው ቅዳሜ የሚደረግ ይሆናል፡፡

በአሌክሳንደሪያ ከተማ በሚገኘው በግዙፉ ቦርጅ ኤል አረብ ስታዲየም የሚደረገውን የመጀመሪያ ዙር የፍፃሜ ጨዋታ ባምላክ እንዲመራ በካፍ ተሹሟል፡፡ የባምላክን መመረጥም የአል አሃሊ ኦፊሲላዊ ድረ-ገፅ እና የሞሮኮው የስፖርት ቴሌቪዥን ቻናል አራዲያ አረጋግጠዋል፡፡ ባምላክ ህንድ በማስተናገድ ላይ ባለቸው የፊፋ ከዓለም ከ17 ዓመት በታች ዋንጫ ላይ ብራዚል እና ሆንዱራስ ያደረጉት ጨዋታ መምራት የቻለ ሲሆን በተለያዩ ግዜያትም የቻምፒየንስ ሊግ፣ የኮንፌድሬሽን ዋንጫ፣ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ፣ የቻን ዋንጫ፣ የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ እና ዋናው ውድድር ላይ መምራት የቻለ አርቢትር ሲሆን የህክምና ባለሙያም ነው፡፡

አንድ ኢትዮጵያዊ አርቢትር ለትልቅ የፍፃሜ ውድድር እንዲመራ ሲመረጥ ይህ ከ1980 የናይጄሪያ የአፍሪካ ዋንጫ በኃላ ለመጀመሪያ ግዜ ነው፡፡ በወቅቱ በአዘጋጇ ናይጄሪያ እና አልጄሪያ መካከል ሌጎስ ላይ የተደረገውን የፍፃሜ ጨዋታ ተስፋዬ ገብረየሱስ በመሃል ዳኝነት መርተዋል፡፡ ከኤርትራ መገንጠል በፊት ኢትዮጵያዊ ዜግነት የነበራቸው ተስፋዬ በ6 የአፍሪካ ዋንጫዎች እና በ1978 የአርጀንቲና የዓለም ዋንጫ (በረዳት ዳኝነት) ጨዋታዎችን መምራት ችለዋል፡፡ ተስፋዬ በአሁኑ ወቅት የኤርትራ ብሄራዊ እግርኳስ ፌድሬሽን ፕሬዝደንት ሁነው እያገለገሉ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ልኡልሰገድ በጋሻው በ2006 የጀርመን የዓለም ዋንጫ በረዳት ዳኛነት ሲመሩ ሊዲያ ታፈሰ ከፍተኛ ግምትን አግኝቶ የነበረውና ካሜሮን ያስተናገደችውን የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ መክፈቻ ጨዋታ በ2016 መምራቷ ይታወሳል፡፡ ሊዲያ በተጨማሪም በሴቶች ከ17 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ እና ዋናው የዓለም ሴቶች ዋንጫ ላይ መካፈል የቻለች አርቢትር ነች፡፡

ኢትዮጵያዊያን አርቢትሮች በኢንተርናሽናል መድረክ የነበራቸው ተስፋትፎ ተቀዛቅዞ የነበረ ሲሆን በቅርብ ግዜያት ግን በተደጋጋሚ ጨዋታዎችን የመምራት እድልን እያገኙ ይገኛሉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *