ሶከር ሜዲካል | የልብ ችግር እና የእግርኳስ ቁርኝት

በእግርኳስ በወጣትነት ዕድሜያቸው ባልታወቀ የልብ ችግር ምክኒያት ተጫዋቾች በሜዳ ላይ ተዝለፍልፈው ወድቀው ህይወታቸው ያለፈበት ተደጋጋሚ ክስተቶች በስፖርቱ ዓለም አስደንጋጭ እና አነጋጋሪ ሆነው አልፈዋል። ይህ ክስተት ከፕሮፌሽናል ስፖርተኞች አልፎ ስፖርታዊ እንቅስቃሴን ለጤና እና ለጊዜ ማሳለፊያ በሚያዘወትሩ ሰዎች ላይ ሲፈጠርም ይታያል። ከልብ ችግር ጋር በተያያዘ የሚያጋጥም ድንገተኛ ሞት በአማካይ ከ48,000 ስፖርተኞች በአንዱ ላይ እንደሚፈጠር ጥናቶች ያመለክታሉ። የዛሬው የሶከር-ሜዲካል አምዳችንም የልብ በሽታ እና ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ቁርኝት ላይ ትኩረቱን ያደርጋል።

ልብ በሰውነታችን ከሚገኙ አካላት በጣም ወሳኙ ሲሆን ዋንኛ ጥቅሙ ደምን ወደተለያዩ የሰውነታችን አካላት መላክ ነው። ደም ወደ ሰውነታችን የሚከፋፍለው ኦክስጅን እና የምግብ ንጥረ ነገሮችን በመያዝ ነው። ይህም አካላቶቻችን ለሚያደርጉት የተለያዩ ተግባራት አቅም ይሆናቸዋል። ልብ ይህንኑ ለህይወት ወሳኝ የሆኑትን ኦክስጂን እና ንጥረነገሮች ለሰውነታችን ለማድረስ በሚያደርገው ጥረትም በዓመት 40 ሚሊዮን ጊዜ ይመታል፤ ከ7500 ሊትር በላይ ደም ደግሞ በቀን ውስጥ ይረጫል።

ታዲያ እንደዚህ ወሳኝ ግልጋሎትን የሚሰጠው ልብ በተለያዩ በሽታዎች ሊጠቃ ይችላል። ላቅ ካለው አገልግሎቱ አንፃር ደግሞ ማንኛውም በልብ ላይ የሚደርስ ህመም ከፍ ያሉ ችግሮችን እና ሲበዛ ደግሞ ሞትን ያስከትላል።

በአብዛኛው በልብ ህመም በተለይም በተለምዶው የልብ ድካም (cardiac Arrest) የሚጠቁ ሰዎች እድሜያቸው የገፋ፣ በቂ እንቅስቃሴን የማያደርጉ እና የሰውነት ክብደታቸው የጨመረ ናቸው። እንቅስቃሴን አዘውትረው የሚያደርጉ እና ቁመናቸው የተስተካከለ ስፖርተኞች ለእንደዚህ ላለው ችግር ተጋላጭ ይሆናሉ ተብሎ አይታሰብም። ነገር ግን የተለያዩ የእግር ኳስ ተጫዋቾች ከልብ ጋር በተያያዘ ምክንያት ህይወታቸው አልፏል። የካሜሮኑ ተጫዋች ማርክ ቪቪያን ፎዬ እና የቀድሞው የትዌንቴ እና ኒውካስል አማካይ የነበረው አይቮሪኮስታዊው ቼክ ቲዮቴ በልብ ድካም ህይወታቸውን ያጡ ተጫዋቾች ናቸው። የቦልተን አማካይ የነበረው ፋብሪስ ሙአምባ ገና በ23 ዐመቱ በተመሳሳይ ምክንያት ሜዳ ላይ ከወደቀ በኃላ በተደረገለት የህክምና እርዳታ ህይወቱ ሊተርፍ ችሏል።

የልብ በሽታቸው የተለያዩ መንስኤዎች አሏቸው። ከውልደት (congenital) የሚመጡ እና ከውልደት በኋላ (acquired) በመባል በሁለት ረድፍ ሊፈረጁ ይችላሉ።

በተጫዋቾች ላይ በአብዛኛው የሚታየው የልብ ችግር መንስኤው ብዙ እንቅስቃሴን ከማዘውተር ጋር የተያያዘ ነው። አንድ ስፖርተኛ እንቅስቃሴን ደጋግሞና አዘውትሮ በሚሰራበት ወቅት ልክ የሰውነቱ ጡንቻዎች እንደሚጨምሩት ሁሉ በልብ የሚገኙት ጡንቻዎች (cardiac muscles) ስራቸውን በላቀ ሁኔታ ለማከናወን እየጨመሩ እና እያደጉ ይመጣሉ። የልብ መጠን በከፍተኛ ደረጃ ሲጨምርም Hypertrophic Cardiomyopathy ለተባለ ህመም ይዳርጋል። ይህ ህመም በተጫዋቾች ላይ ተዘውትሮ የሚስተዋል ነው።

በልብ ችግር ምክኒያት የሚፈጠር አደጋ በተለይም በጥቁር (አፍሪካዊ) ተጫዋቾች ላይ በብዛት ይስተዋላል። ቢቢሲ ባወጣው መረጃ መሰረት በ10 ዓመት ውስጥ በሜዳ ላይ ህይወታቸው ካለፈ 26 አፍሪካውያን ተጫዋቾች የ25ቱ መንስኤ የልብ ህመም ነበር። በመግቢያው ላይ እንደተገለፀው ከልብ ችግር ጋር በተያያዘ የሚያጋጥም ድንገተኛ ሞት በአማካይ ከ48,000 ስፖርተኞች በአንዱ ላይ የሚፈጠር ቢሆንም በጥቁር ስፖርተኞች ላይ ግን ከ18,000 አንዱ በችግሩ ይጠቃል። የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱትም ጥቁር ተጫዋቾች ከነጮች እስከ 3 እጥፍ በሚደርስ መልኩ ለዚህ ተጋላጭ ናቸው። የዚህን ምክኒያት የልብ የግራ ክፍል ግድግዳ ከሌሎች በተለየ አፍሪካዊ እና የጥቁር ዘር ባላቸው ሰዎች ላይ መጠኑ የሚጨምር ከመሆኑ ጋር የሚያያይዙት ምሁራን አሉ።

ጥቁር ተጫዋቾች በዘር ምክኒያት ለልብ ችግር ተጋላጭ ከመሆናቸው ባሻገር በሜዳ ላይ ለሚከሰትባቸው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ድንገተኛ ሞት ሌሎች ምክኒያቶች አሉ። የስፖርት ህክምና ዘርፉ ባላደገባቸው የአፍሪካ ሃገራት ሊጎች የሚጫወቱ ተጫዋቾች ተገቢው የጤና ምርመራ ሳይደረግላቸው ከቀረ የበሽታው ተጠቂ እንደሆኑ እንኳን ላያውቁ ይችላሉ። በነዚህ ሃገራት በጨዋታዎች እና የልምምድ ክፍለጊዜዎች ላይ ተጫዋቾች በልብ ህመም ምክኒያት በሜዳ ላይ ቢወድቁ እንኳን አስፈላጊ የህክምና ቁሳቁሶች ባለመኖራቸው የተጫዋቾቹን ህይወት ለማትረፍ እንኳን የማይቻልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል።

በድህነት ውስጥ ያደጉ አፍሪካውያን ተጫዋቾች እግርኳስን ከድህነታቸው ማምለጫ ብቸኛ መንገድ አድርገው በመውሰድ ያለባቸውን የልብ ህመም የሚደብቁበት አጋጣሚም ብዙ ነው። ይህም የመጣው ክለቦች ህመም እንዳለብኝ ካወቁ አይፈልጉኝም ከሚል ፍራቻ ነው። ነገር ግን አብዛኞቹ ከልብ ጋር የተያያዙ ህመሞች መፍትሄ ሊበጅላቸው የሚችሉ ናቸው። በድብቅ መያዛቸው ግን ለተለያዩ የጤና ችግሮች ሲከፋም ደግሞ ለሞት ይዳርጋል።
በተለያዩ ክለቦች ያለው የጤና ምርመራ እና የልብ ጤንነት መለኪያዎች መለያየታቸውም በተለይ ወደ አውሮፓ ሃገራት ተጉዘው የሚጫወቱ አፍሪካውያንን ህይወት ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነው። የጋና ብሔራዊ ቡድን አጥቂ የሆነው እና በ2019 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጋና ኢትዮጵያን 5-0 በረታችበት ጨዋታ ላይ 2 ግቦችን በስሙ ያስመዘገበው ራፋኤል ድዋሜና ጉዳይ ይህንን የሚያሳይ ነው። ራፋኤል በስዊዘርላንዱ ክለብ ኤፍሲ ዙሪክ የሚጫወት ሲሆን በክረምቱ የዝውውር መስኮት የእንግሊዙን ብራይተን ኤንድ ሆቭ አልቢየን ለመቀላቀል ጫፍ ደርሶ በጤና ምርመራ ወቅት የልብ ህመም ስለተገኘበት ዝውውሩ ሳይሳካ ቀርቷል። ተጫዋቹ ግን አሁንም ወደ ክለቡ ተመልሶ በኤፍሲ ዙሪክ እየተጫወተ ይገኛል። ይህ ሂደት ከልብ ችግር ጋር በተያያዘ በተጫዋቹ ቀጣይ የእግርኳስ ህይወት ላይ ለሚያጋጥም አደጋ ክለቡ ተጠያቂ እንዲሆን የሚያደርግ ነው።

ተጫዋቾች በልባቸው ላይ ችግር መኖሩን የሚያሳዩ ከእንቅስቃሴ ጋር የሚመጣ እና እጅ፣ አንገት እና ጀርባ ድረስ የሚሄድ የደረት ህመም፣ እራስን መሳት፣ የትንፋሽ መቆራረጥ (ስፖርታዊ እንቅስቃሴው ከሚያመጣው በላይ የሆነ)፣ ልብ በሃይል ሲመታ መሰማት የመሳሰሉ ምልክቶች ቢኖሩም ከ85% በላይ የሚሆኑት በሜዳ ላይ የሚፈጠር ድንገተኛ ሞት ሰለባ ተጫዋቾች ምንም አይነት ምልክት አይታይባቸውም።

በተጫዋቾች ላይ የበሽታ ምልክቶች እስኪታዩ ከመጠበቅ ይልቅ በዝውውር ወቅትም ሆነ ለሙሉ የቡድን ተጫዋቾች የሚደረግ የተሟላ እና ልብ እና የደም ዝውውር ስርዓት ላይ ትኩረቱን ያደረገ የጤና ምርመራ ወሳኝ ነው። አንዳንድ የአውሮፓ ሃገራት ድንገተኛ ሞትን ለመከላከል በስፖርታዊ ውድድሮች ላይ የሚሳተፉ ስፖርተኞች በሙሉ የጤና ምርመራ እንዲያደርጉ የሚያስገድድ ህግ አውጥተው እስከመተግበርም ደርሰዋል። ለዚህ በጣሊያን ላለፉት 30 ዓመታት ተግባራዊ የሆነው እና በፕሮፌሽናል እና አማተር ሊጎች፣ በሁሉም የእድሜ እርከኖች እና በሁለቱም ፆታዎች የሚጫወቱ ስፖርተኞች የልብ ምርመራ እንዲያደርጉ እና ውጤታቸውም በማዕከላዊ መዝገብ እንዲመዘገብ የሚጠይቀው መመሪያ አንድ ማሳያ ነው። በሃገሪቱ ምርመራ ከሚደረግላቸው ሰዎች እስከ 7% ያህሉ ምንም የልብ ችግር ሳይኖርባቸው እንዳይጫወቱ መደረጋቸው የዚህ ዘዴ አሉታዊ ጎን ቢሆንም በልብ ችግር ሊጠቁ የሚችሉ ተጫዋቾችን በበቂ ሁኔታ በመተንበይ እና ከውድድሮች በማስወጣት ድንገተኛ የሜዳ ላይ ሞት በጣሊያን እምብዛም እንዳይከሰት አድርጓል።

እነደዚህ ያሉት ችግሮች ቢያጋጥሙ እንኳን የተጫዋቾችን ህይወት ለመታደግ በስቴዲየም እና በልምምድ ቦታ ባለሙያዎች ያስፈልጋሉ። እንደዚሁም ህይወትን ለማትረፍ የሚረዱ መሳሪያዎች (Resuscitation materials and Defibrillator) ከባለሞያዎቹ ጋር ሁልጊዜም ሊኖሩ ይገባቸዋል። ተጫዋቾችም ከላይ የተዘረዘሩትን ምልክቶች በሰውነታቸው ላይ ሲያዩ በፍጥነት ወደ ባለሙያ በመሄድ እና በመታየት ህይወታቸውን ሊያተርፉ ይችላሉ። ባለሙያን ማማከራቸው ከሚከሰቱ የጤና እከሎች ተጠብቀው በአግባቡ እንዲንቀሳቀሱ ይረዳቸዋል እንጂ በሰውነታቸው አልያም በእግር ኳስ ስራቸው ላይ የሚያደርሰው አሉታዊ ተፅዕኖ የለም።

በአጠቃላይ ከልብ ህመም ጋር የተያያዘ በሜዳ ላይ የሚፈጠር ድንገተኛ ሞትን ለመከላከል ተጫዋቾች፣ ክለቦች እና የስፖርቱ አስተዳደር አካልን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የተለያዩ ሃገራትን ልምድ በመውሰድ የቅድሚያ መከላከል እና መፍትሄ አማራጮችን ሊተገብሩ እንደሚገባ መልዕክታችንን እናስተላልፋለን።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *