የትግራይ ዋንጫ በድጋሚ የቀን ለውጥ ተደረገበት

መስከረም 10 ቀን 2010 |የትግራይ ዋንጫ በድጋሚ የሚጀምርበትን ቀን አራዝሟል።

በትግራይ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት የክልሉን አራት ክለቦች እና ሌሎች ተጨማሪ ክለቦችን በማሳተፍ በመቐለ ስታድየም ከመስከረም 19- 26 እንዲካሄድ ቀነ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው ውድድሩ ለአንድ ሳምንት ተራዝሟል። ከዚህ ቀደም ከመስከረም 12 ቀን ጅምሮ እንደሚካሄድ ተወስኖ የነበረው ይህ ውድድር የሽረ እንደስላሴን የከፍተኛ ሊግ ውድድር ዘግይቶ መጨረስ ምክንያት አድርጎ ነበር ለአንድ ሳምንት የተራዘመው።

ሆኖም ውድድሩ የሚጀምርበትን ቀን ለተጨማሪ አንድ ሳምንት በማራዘም በድጋሜ ማሻሻያ አድርጓል። የዚህ ውሳኔ ምክንያት ደግሞ የአምናው የኢትዮጵያ ዋንጫ አንድ የሩብ ፍፃሜ እንዲሁም የግማሽ ፍፃሜ እና የፍፃሜ ጨዋታዎች የመከናወኛ ቀን ከመስከረም 12-19 በመሆኑ ነው። የመርሀ ግብሮቹን መጋጨት ለማስቀረትም የትግራይ ዋንጫ ከመስከረም 26 እስከ ጥቅምት 4 ድረስ እንደሚደረግ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። በተመሳሳይ የአዲስ አበባ ዋንጫም ከሊጉ ጅማሮ ጋር እንዲስተካከል በማሰብ የቀን ለውጥ ማድረጉ ይታወሳል።