ሪፖርት | ዳዋ ሆቴሳ ለአዳማ ሦስት ነጥቦች አስጨብጧል

ከ12ኛው ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች መካከል ዛሬ አዳማ ከተማ ወልዋሎን ዓ/ዩን ያስተናገደበት ጨዋታ በባለሜዳዎቹ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ሁለቱ ቡድኖች በአስራ አንደኛው ሳምንት ካደረጓቸው ጨዋታዎች የአንድ ተጨዋች ለውጥ ብቻ ነው ያደረጉት። ባለሜዳዎቹ አዳማዎች ከደደቢት ነጥብ ከተጋሩበት ጨዋታ ግራ መስመር ተከላካይ ቦታ ላይ በቴዎድሮስ በቀለ ምትክ ሱለይማን መሀመድን ሲጠቀሙ ወልዋሎዎች ባህር ዳርን ሲገጥሙ ከተጠቀሙበት የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ጉዳት የገጠመው አጥቂው ሪችሞንድ ኦዶንጎን ከቅጣት በተመለሰው አማካይ አስራት መገርሳ ተክተውታል።

ጨዋታው ሁለቱም ቡድኖች ያላቸውን የማጥቃት ፍላጎት በሚያሳይ ፈጣን እንቅስቃሴ የጀመረ ነበር። ወልዋሎዎች ከግራ መስመር በሚነሳው ፕሪንስ ሰቨሪንሆ ወደ አዳማ ሳጥን ውስጥ ለመግባት የሚያደርጉት ጥረት እና የባለሜዳዎቹ አዳማዎች ከበረከት ደስታ የሚነሳ ተመሳሳይ የቀኝ መስመር ጥቃት በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በተደጋጋሚ ይታዩ ነበር። አዳማዎች የመጀመሪያውን ሙከራ 6ኛው ደቂቃ ላይ በዳዋ ሆቴሳ ሲያደርጉም ኳሱ የተነሳው ከበረከት ነበር። በወልዋሎዎች በኩል ለግብ የቀረበ አጋጣሚ 16ኛው ደቂቃ ላይ የተፈጠረ ሲሆን ከማዕዘን የተነሳውን ኳስ ቢኒያም ሲራጅ አክርሮ ሞክሮ ተከላካዮች ተደርበው አውጥተውታል።

ከሜዳቸው ውጪ ቢጫወቱም ባገኙት አጋጣሚ ወደ ፊት ለመሄድ ይሞክሩ የነበሩት ወልዋሎዎች በተደጋጋሚ ወደ ግብ በመድረስ የተሻሉ ነበሩ። ከፊት በሚፈጥሩት ጫናም በርካታ የማዕዘን ምቶችን ያገኙ ሲሆን ከመጀመሪያው የቢኒያም ሙከራ በተጨማሪ ካገኟቸው የማዕዘን ምቶች ግን እምብዛም ውጤታማ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። 23ኛው ደቂቃ ላይ አስራት መገርሳ ከግራ ያነሳው ኳስ ተጨራርፎ ያገኘእ እንየው ካሳሁን በቀኝ በኩል ሞክሮ ወደ ውጪ የወጣበት እና 30ኛው ደቂቃ ላይ ብርሀኑ አሻሞ ከዛው ግራ መስመር ያሻገረለትን ወንድሙ ኤፍሬም አሻሞ በግንባሩ ሞክሮ ሮበርት በቀላሉ የያዘበት የሚጠቀሱት የቡድኑ ሌሎች ሙከራዎች ነበሩ። ከዚህ ባለፈ ወልዋሎዎች መሀል ላይ ከሚያስጥሏቸው ኳሶች በመልሶ ማጥቃት የመግባት አጋጣሚዎች ቢኗሯቸውም ወደ ሙከራነት መቀየሩ ላይ ግን አልተሳካላቸውም።

መሀል ሜዳ ላይ በተደጋጋሚ ቅብብሎቻቸው ሲበላሽባቸው የነበሩት አዳማዎች በመስመሮች በኩል ማጥቃትን ምርጫቸው አድርገው ታይተዋል። በቀኝ በኩል ከበረከት እና ሱለይማን መሀመድ ጥምረት ወደ ውስጥ የሚሻሙ እንዲሁም ከመሀል ተከላካዩ ተስፋዬ በቀለ በቀጥታ ለዳዋ የሚላኩ ረጃጅም ኳሶች የቡድኑ ዋነኛ የጥቃት መሳሪያዎች ነበሩ። ከዚህ ውጪ ከቀኝ መስመር የሚነሳው ቡልቻ ሹራም ወደ ውስጥ ይዞ ለመግባት የሚሞክራቸው ኳሶች ይታዩ ነበር። ሆኖም የቡድኑ የማጥቃት አማራጮች መደጋገም በቶሎ ቦታቸውን ይሸፍኑ ለነበሩት ወልዋሎዎች ፈታኝ መሆን አልቻለም። ያም ቢሆን የአዳማዎች ተደጋጋሚ ተሻጋሪ ኳሶች ጭማሪ ደቂቃ ላይ ውጤት አስገኝተዋል። ጭማሪ ደቂቃ ላይም ከቀኝ መስመር ምኞት ደበበ ያሻገራውን ኳስ ዳዋ ሆቴሳ በግንባሩ በመግጨት ማስቆጠር ችሏል። ዳዋ ግቡን ካስቆጠረ በኋላ ተጠባባቂ የነበረው ፉዓድ ፈረጃ ጋር በመሄድ በተለየ መንገድ ደስታውን ሲገልፅ ታይቷል።

ከዕረፍት መልስ የጨዋታው ግለት በዛው የቀጠለ ቢሆንም ወልዋሎዎች በተሻለ መልከ ወደ ጎል ይደርሱ ነበር። 48ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ በኩል በከፈቱት መልሶ ማጥቃት በኤፍሬም አሻሞ ካደረጉት ሙከራ በተጨማሪም 52ኛው ደቂቃ ላይ አዳማዎች ወደ ኋላ የመለሱትን ኳስ ሮበርት ለማውጣት ሲሞክር አስራት መገርሳ ተደርቦበት ኳሷ ለጥቂት ነበር ወደ ውጪ የወጣችው። በአንፃሩ አዳማዎች ብቸኛው አጥቂያቸው ዳዋ ሆቴሳን ማዕከል ያደረጉ ኳሶች ወደ ፊት በመጣሉ የገፉበት ሲሆን 57ኛው ደቂቃ ላይ ከበረከት በተቀበለው ኳስ ጥሩ የማግባት ዕድል አግኝቶ የነበረው ዳዋ ሙከራው ጉልበት ሳይኖረው ቀርቷል።

የጨዋታው አነጋጋሪ ክስተት የተፈጠረው 60ኛው ደቂቃ ላይ ነበር መሀል ሜዳ ላይ አፈወርቅ ኃይሉ ኢስማኤል ሳንጋሬ ላይ የሰረውን ጥፋት ተከትሎ በተነሳው ግርግር ጨዋታው ለአራት ደቂቃዎች ተቋርጧል። የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ሜዳ ውስጥ ገብተው በሂደት ነገሮች የተረጋጉ ሲመስሉ የዕለቱ የመሀል ዳኛ ተፈሪ አለባቸው በግርግር ውስጥ ቡጢ የሰነዘረው ቡልቻ ሹራን እና አፈወርቅ ኃይሉን በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ አስወጥተዋል። ነገር ግን አርቢትሩ ኢስማኤል ሳንጋሪን እና ብርሀኑ አሻሞ ላይም የቀይ ካርድ ከመዘዙ በኋላ ሁኔታው በስህተት የተፈጠረ መሆኑን አስረድተው ሁለቱ ተጫዋቼች ወደ ሜዳ ተመልሰዋል።

ከቀይ ካርዶቹ በኋላ አዳማዎች ወደ ኋላ አፈግፍገው በመከላከል የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን ሲጠብቁ ወልዋሎዎች ደግሞ በበረከት ደስታ ወደ ቀኝ መምጣት ምክንያት ክፍተት የነበረበትን የአዳማ የግራ መስመር ተከትለው ለማጥቃት ሞክረዋል። ወልዋሎዎች ይህንን ያድርጉ እንጂ ወደ ውስጥ ሰብረው ለመግባት አልቻሉም። በረጅሙ ወደ ፊት የሚጥሏቸው ኳሶችም በተደጋጋሚ በምኞት ደበበ ይገጩ ነበር። ጥሩ ጥሩ የመልሶ ማጥቃት ቅፅበቶችን ያገኙት አዳማዎች በአንፃሩ የግብ ዕድሎችን ፈጥረዋል። በተለይም 86ኛው ደቂቃ ላይ ዳዋ ከሱለይማን ሰሚደ ተቀብሎ ሲገባ አብዱላዚዝ ኬይታ ደርሶ ያወጣበት እና ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ከበረከት ተቀብሎ ሲሞክር ግብ ጠባቂው ኬይታ ያዳነበት የሚጠቀሱ ነበሩ። ጨዋታው ግን ተጨማሪ ግብ ሳይታይበት እስከመጨረሻው ብርቱ ፉክክር ተደርጎበት በ1-0 ውጤት ተጠናቋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *