” የትኩረት ችግራችንን በመልስ ጨዋታ ሙሉ ለሙሉ ቀርፈናዋል ” አሰልጣኝ ሠላም ዘርዓይ

የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በቶኪዮ ኦሊምፒክ ማጣርያ ዩጋንዳን በድምር ውጤት 4-2 በማሸነፍ ወደ ተከታዩ የማጣርያ ዙር ማለፉ ይታወሳል። በደርሶ መልስ ጨዋታዎች ላይ የሚነሱ ጉዳዮችን አስመልክቶ ማክሰኞ በአዲስ አበባ ስታድየም አሰልጣኝ ሠላም ዘርዓይ እና በመልሱ ጨዋታ ብቸኛዋን የማሸነፍያ ጎል ያስቆጠረችው ሎዛ አበራ ተገኝተው ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል። የተሰጡት ዋና ዋና ሀሳቦችን እንደሚከተለው አሰናድተነዋል።

አሰልጣኝ ሠላም ዘርዓይ

እዛ ከደረስን በኋላ ሁለት ልምምዶች ነው የሰራነው። የመጀመሪያው ቀን ቀላል፤ በሁለተኛው ቀን ከባድ ልምምድ ሰርተናል። ጨዋታውን ስናየው በጣም ከባድ ነበር። እዚህ አዲስ አበባ ከገጠመን ቡድን በጣም ተቃራኒ ነበሩ። ውጤቱን ለማግኘት የገባ ደጋፊ አለ። የተወሰነ የዳኝነት ተፅዕኖ ከመኖሩ በተጨማሪ የአየር ንብረቱ በጣም ሞቃታማ ነበር። በዚህ ሁሉ ውስጥ ሆነን ነው ውጤቱን ማምጣት የቻልነው።

ስለ ሰናይት ቦጋለ እና ህይወት ደንጊሶ

በሰናይት እና በህይወት መካከል የሚና እና የልምድ ልዩነት አለ። በመጀመሪያው ጨዋታ ማጥቃት እንደመፈለጋችን መጠን ሰናይትን ተጠቅመናል። ሰናይት እና ብርቱካን ተመሳሳይ የጨዋታ ባህሪ ያላቸው ናቸው። በጨዋታው ላይ ሰናይት እና ብርቱካን ወደፊት በሚጠጉበት ወቅት በመሀል ክፍሉ እመቤት ብቻዋን በመጋለጧ እኛ ተደጋጋሚ የግብ እድል ሲፈጠርብን ስለታየ በማጥቃቱ እና መከላከሉ ላይ ሚዛናዊ ለማድረግ ህይወት ገብታለች። ከህይወት መግባት በኋላ ቡድኑ ሚዛኑን መጠበቅ ችሏል። ሁለት ተጨማሪ ግቦችም ማግባት ችለናል። ስለዚህ ይህንን ዩንጋዳ ላይ በተደረገው ጨዋታ ላይ ተግብሬዋለሁ። ህይወትን ለመከላከል እንዲሁም ሰናይትን ለማጥቃት የሚል አስተሳሰብ አለ፤ ይህ ሊታረም ይገባዋል። ሁለቱም የራሳቸው የሆነ የኳስ ችሎታ አላቸው።

ሙቀትን ስለመቋቋም

ሙቀቱን ለመቋቋም ተመሳሳይ አየር ንብረት ወዳለው አካባቢ ተጓዞ ልምምድ ማከናወን ይጠቅማል። እኛ የመጀመርያው ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ በመሆኑ እዚሁ ነው የተዘጋጀነው። የመልስ ጨዋታ ለማድረግ ደግሞ ወዲያውኑ ነው የሄድነው። እዛ የነበረው ሙቀት እስከ 37°c ይደርሳል። የትም ብትሄድ ተመሳሳይ የአየር ንብረት አታገኝም። ነገር ግን ተመሳሳይ ወደ ሆነው እየተጓዙ ልምምድ ማድረግ ይቻላል።

ሙሉ ጨዋታ ተቋቁሞ ስለመጨረስ

ቡድኔ 90 ደቂቃ ጠንክራ ሆኖ መቆየት ይችላል። ይህንንም በዩንጋዳው ጨዋታ ላይ አሳይቷል። ነገር ግን ቡድኖች የጨዋታ መጠነቃቂያ ላይ ትኩረት ያጣሉ። ይህ የብዙ ትልልቅ ቡድኖች ችግርም ነው። ወደ እኛ ቡድን ስትመጡ አዲስ አበባ ላይ ሶስት ጎሎችን ከማስቆጠራችን በተጨማሪ የጨዋታ እንቅስቃሴ ብልጫ መውሰዳችን በተጫዋቾቼ ላይ የራስ መተማመን መፍጠሩን እና ውጤቱ ያሳልፋል የሚል እምነት ማሳደሩን ነው ያየሁት። ይህም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ትኩረት እንድናጣ አድርጎናል። ይህን ችግራችንን በመልስ ጨዋታ ሙሉ ለሙሉ ቀርፈናዋል። አንድ ቡድን 90 ደቂቃ ለመጨረስ የሚያስፈልገው አካል ብቃት አይደለም፤ ትኩረት እንጂ። በዚሁ አጋጣሚ በዩንጋዳ ተጫዋቾቼ ያሳዩትን ተጋድሎ ሳላደንቅ አላልፍም። ላመስግናቸውም እፈልጋለሁ።

ስለ ሎዛ አበራ

በሷ ላይ የተነሱ ሀሳቦች ቢኖሩም ሎዛ ትልቅ ተጫዋች መሆኗን አሳይታለች።

ቀጣይ እቅድ

የቅጥሩ ሁኔታ ለ6 ወር የሚቆይ ነው። በቀጣይ ላለብን ጨዋታ ከ5 ወር በላይ ጊዜ አለን። በነዚህ ጊዚያት ውስጥ በየቡድኖቹ ውስጥ ተኝተው የሚመጡ ከሆነ ለውጥ አይመጣም። ነገር ግን ብሔራዊ ቡድኑ በየወሩ የወዳጅነት ጨዋታ እንዲሁም ለሁለት ወይም ለሶስት ቀን ሆቴል ቆይታ እንዲኖራቸው እንዲሁም በነዚህ አምስት ወራት 5 ያህል ወዳጅነት ጨዋታ ታስቧል። ሁለቱ ኢንተርናሽናል እንዲሁን በቃል ደረጃ ከፌዴሬሽኑ ኃላፊዋች ጋር አውርተናል። ቡድኑ ተደጋጋሚ የሆነ የወዳጅነት ጨዋታ እንዲያደርግ ጥረት እናደርጋለን።

የለበሰችው ልብስ

ፌዴሬሽኑም ሆነ የኦሊምፒክ ኮሚቴ በቂ ትጥቅ አቅርቦ ነበር። ነገር ግን ችግሩ የተፈጠረው ብሔራዊ ቡድኑ የተሰጠው መለያ ቢጫ ነበር፤ እኔ ጋርም ያሉት ልብሶች ቢጫ ቀለም ያላቸው በመሆኑ ቀይ ማድረግ አለብሽ ተባልኩኝ። በአጋጣሚ ሻንጣዬ ውስጥ ያገኝውትን ቲሸርት ለበስኩት። በሰዓቱ በልብሱ ላይ ስለተፃፈው ፅሁፍ አትኩሮት ሳልሰጥ ቡድኔን ለመምራት ማሰቤን ቀጠልኩኝ። ቢጫ ጃኬት ከላይ ደርቤ ነበር፤ ነገር ግን አራተኛ ዳኛዋ አስወልቃኛለች። ከጨዋታው በኋላ ጋዜጣዊ መግለጫ በቢጫው ልብስ ሰጥቼ ወጥቻለሁ። በዚሁ አጋጣሚ ሙሉ ለሙሉ የኔ ስህተት ነው፤ ይቅርታ እጠይቃለሁ።

የመስመር አጨዋወት

በትክክል መስመር ላይችግር ነበር። አዲስ አበባ ላይ በተደረገው ጨዋታ ሁለቱም ከ17 ዓመት በታች ካለው ብሔራዊ ቡድን የተመረጡ ናቸው። የኢንተርናሽናል ጨዋታ ልምድ አለመኖሩ ጫና ውስጥ ከቶን ነበር። በተለይም አንደኛዋ የመስመር ተጫዋች በፕሪምየር ሊጉ የአጥቂነት ሚና ያላት ነበረች። መልስ ጨዋታ በቦታው ላይ ለውጥ ለማድረግ ሞክረናል።

ስለ አረጋሽ ከልሳ

አረጋሽ ከአካዳሚ የተገኘች ድንቅ ልጅ ነች። በኢትዮጵያ እግር ኳስ ተስፋ የሚታይባት እምቅ ችሎታ ያላት ተጫዋች ነች። በይበልጥ ልምዱን እና እድሉን ስታገኝ የበለጠ የምታኮራን ተጫዋቾች ነች።

ስለ ቀጣይ ጨዋታ

የካሜሩንን ጨዋታ ስናከናውን ቡድኖች መርሐ ግብራቸውን የሚጨርሱበት በመሆኑ በቂ የመዘጋጃ ጊዜ ስላለን ይበልጥ ጠንክረን የምንሰራበት ጊዜ ይሆናል። ካሉት አሰልጣኞች ጋር በይበልጥ ተቀራርበን የምሰራ ይሆናል። ከዚህ ቀደምም ስንሰራ ቆይተናል። ተጋጣሚያችን ካሜሩን ጠንካራ ነው። ይህ ማለት እኛ እጆቻችን አጣምረን እንቀመጣለን ሳይሆን ባለቡን ድክመቶችን ጠንክረን ሰርተን የተሻለ ቡድን ይዘን እንገባለን። በስተመጨረሻ የቡድኑ ስብስብ እንደ አስፈላጊነቱ የሚጨምር የሚቀንስ ይሆናል። ብሔራዊ ቡድኑ የሰላም ወይም የሎዛ አይደለም። የኢትዮጵያን ህዝብ ነው። ማንም አቅም ያለው ተጫዋች የሚጫወትበት ነው። አሁን ባለው ነገር ሁሉንም በየቡድኑ ያላቸውን እንቅስቃሴ በመከታተል እንደ አስፈላጊነቱ ባለብን ክፍት ወይም ደከማ ቦታዎች ላይ ተጫዋቾችን የምንጨምር ይሆንል።

ሎዛ አበራ

የዩንጋዳው ጨዋታ ደስ ይል ነበር። ሙቀት ባለበት ቦታ ላይ እንደመጫወታችን ብዙ ፈትኖናል፤ ሜዳውም አርቴፍሻል እንደመሆኑ መጠን ይህን ውጤት በማሳካታችን በጣም ደስተኛ ነን። ከመልሱ ጨዋታ በፊት የቡድኑ መንፈስ በጥሩ መነሳሳት ላይ ነበር። ሀገራችንን አንድ ደረጃ ከፍ ማድረግ መቻል አለብን ብለን አስበን ስለነበር ይህን ማሳካት በመቻላችን ሁላችንም ደስተኛ ነን።

ከሚዲያ የነበረው ጫና

ከጨዋታው በፊት ጫናዎች ነበሩ። ነገር ግን ይህ ነገር በየትኛውም ተጫዋች ላይ የሚፈጠር ነው። እኔ በግሌ በመልካም ጎኑ ነው የተቀበልኩት። ይህም ደሞ ይበልጥ እንድሰራ እና ራሴን በይበልጥ እንዳሳይ አነሳስቶኛል። የተባለውን ነገር ተቋቁሞ ማለፍ እንዳለብኝ ትምህርት ሰጥቶኝ አልፏል። ጫና ግን አለው። እኔ ራሴን አውቀዋለሁ። ብሔራዊ ቡድን እንደመጫወቴ መጠን ሀገሬን እንደመወከሌ መጠን ሜዳ ውስጥ ያለኝን ሁሉ ለመስጠት ዝግጁ ነኝ። ይህንን ለማድረግ ሞክሬያለሁ። በኢንተርናሽናል ጨዋታም 23 ግቦች አሉኝ።

ስላመከነቻቸው የግብ እድሎች

በአዲስ አበባው ጨዋታ የጎል እድሎችን አምክኛለሁ። ከጨዋታው በኋላ ቪዲዮ ቁጭ ብዬ ስመለከተው ሁለት ንፁህ ጎል የሚሆኑ አጋጣሚዎችን አልተጠቀምኩም። ይህ ደግሞ በእግር ኳስ ያጋጥማል። ማንም ትልቅ ተጫዋች ይህ ያጋጥመዋል። ማድረግ የነበረብኝ የሳትኩትን ኳስ ረስቼ ጎል ማግባት እንደምችል ለራሴ ነገሪያዋለሁ። ሌላ ጎል ማግባት እንድምችል ነበር ለራሴ እየነገርኩት ወደ ሜዳ የገባሁት። ይህንንም ማሳካት ችያለሁ።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡