የቻን ውድድር አስተናጋጅነት መነጠቅን በተመለከተ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን መግለጫ


በ2020 የሚካሄደውን የአፍሪካ ሀገራት ዋንጫ (ቻን) የማስተናገድ እድል አግኝታ የነበረችው ኢትዮጵያ ባሳለፍነው ሳምንት መብቷን ተነጥቃ ለካሜሩን መሰጠቱ ይታወሳል። ይህን በተመለከተም ስለ ጉዳዩ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ቅዳሜ በአዲስ አበባ ስታድየም ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

በመግለጫው ላይ አቶ ተድላ ዳኛቸው (የክለብ ላይሰንሲግ) እና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው ባህሩ ጥላሁን ፌዴሬሽኑን በመወከል ተገኝተው ማብራሪያ እና ለጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።

ተድላ ዳኛቸው

የ2020 የቻን ውድድር ለማዘጋጀት ሞሮኮ ላይ በተዘጋጀው ስነ-ሥርዓት ላይ የሚኒስተር ዴኤታው አቶ ተስፋዬ ይገዙ እንዲሁም አቶ ጁነይዲ ባሻ በመገኘት የርክክቡን ሂደት እንዳደረጉ የሚታወስ ነው። ከዛም በኋላ ስራዎች እየተከናወኑ ቆይተዋል። የውድድሩ አዘጋጅ ካፍ የመጀመሪያ ጊዜ ግምገማ በኢሳክ አላዩ የሚመራና ከተለያዩ የስራ ዘርፍ የተወከሉ ስድስት ባለሞያዎችን ከሚያዚያ 16-24 ቀን 2018 ይዘው መጥተዋል። ከሚዲያ፣ ከገበያጥናት፣ ከክለብ ላይሰንሲግ እና ከካፍ ሁለት አስተባባሪዎች የነበሩ ሲሆን በግምገማው ወቅት ሁሉንም ነገር በአትኩሮት ለማየት ተሞክሯል። በዚህ በመጀመሪያው ግምግገማ ወቅት ስድስት ስታድየሞች፣ 12 መለማመጃ ሜዳዎች፣ ሀያ ሆቴሎች እና አምስት አየር ማረፊያዎች በጥልቅ ግምገማ ለማየት ተሞክሯል።

ድሬዳዋ፣ ሐረር፣ ሀዋሳ፣ ባህር ዳር፣ ትግራይ፣ አዳይ አበባ ለዕይታ የቀረቡ ስታድየሞች ናቸው። እነዚህ ስታደየሞች በግንባር በመገኘት የታዩ ሲሆን እኔም በግምገማው ወቅት የቡድኑ አስተባባሪ በመሆን ስሰራ ቆይቻለሁ። በወቅቱ አቶ ጁነይዲ የነበረበት ወቅት ነበር። በዛ ወቅት ፌዴሬሽኑ የተጠመደው በምርጫ ሁኔታ ላይ ነበር። የግምገማው ቡድን እያንዳንዱን ኹኔታ እና ተግዳሮቶች በአትኩሩት ሲከታተሉ የቆዩ ሲሆን በስተመጨረሻም ሪፖርት ተልኳል። ሪፖርቱ የሚጠቃልለው ብዙ ቢሆንም በተቻለን መጠን አጠቃልዬ ያለውን ነገር ለቤቱ የማቀርብ ይሆናል።

* በጉብኝት ወቅት የታዩት ስታድየሞች በሙሉ በግንባታ ላይ የነበሩ እና ያልተጠናቀቁ ናቸው። እነዚህን ባሉት ጊዜያቶች ውስጥ ኃላፊነት በመውሰድ ጥልቅ የሆነ ስራ ካለ ሊጠናቀቁ እንደሚችሉ፤ እያንዳንዱ ስታዲየም የካፍ መስፈርቶችን ማሟላት ያለበት መሆኑን ገልፅዋል። በተለይም የቻን ውድድር ለካፍ ከአፍሪካ ዋንጫ በቀጣይ የሚዘጋጅ ውድድር እንደመሆኑ መጠን የራሱ የሆነ መስፈርቶች አሉት። እነዚያን መስፈርቶች ማሟላት የግድ ነው።

* የግምገማው ሪፖርት ላይ ውድድሩ በኢትዮጽያ ሊካሄድ ይችላል። ነገር ግን በጥር ወር ላይ ውድድር በሚከናወንበት ወቅት የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ስላለ የጊዜ ለውጥ ቢደረግ የሚል ሀሳብ የግምገማው ጊዜ ሲጠናቀቅ ያቀረቡ ሲሆን ያላቸውንም ስጋት አያይዘውም ገልፀዋል።

* በዚህ ግምገማ በመጪው ጊዜ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስተር ስለሚመረጥ ትክክለኛውን መረጃ የሚያገኝበት መንገድ ላይኖር እንደሚችል ስጋት ነበራቸው። ከዚህ በተጨማሪ ከዚህ በፊት ውድድሩ እንዲካሄድ እሺታን የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በነበሩበት ወቅት በመሆኑ ከዛ በኋላ የተረከቡት ዐቢይ አህመድ በሚመጡበት ወቅት ይህ ሁኔታ እንዳይገጥማቸው እንዲሁም የመንግስት ለውጡን ተከትሎ ስፖርት ዙሪያ መዋቅራዊ ለውጥ ሊካሄድ እንደሚችል ስጋታቸውን ገልፀዋል።

* በስታድየሙ ዙሪያ ያስቀመጡት አጠቃላይ ምልከታ

– አደይ አበባ ስታዲየም እስካሁን በግንባታ ላይ ነው።

– በሀዋሳ ኢንተርናሽናል ስታዲየም አንዳድንድ የስታዲየሙ ክፍሎች ግንባታቸው አልተጠናቀቀም። ነገር ግን በአጭር ጊዜ ማለቅ አለባቸው።

– ባህር ዳር ኢንተርናሽናል ስታዲየም በግንባታ ላይ አይደለም። ነገር ግን የካፍን የቻን ውድድር የማያሟላ ነው፤ በተለይም የውስጠኛው ክፍሎች።

– ትግራይ ኢንተርናሽናል ስታዲየም እስካሁን ግንባታ ላይ ነው። ነገር ግን ስታደዩሙ ሲጠናቀቅ ጥሩ አቅም አለው።

– ድሬዳዋ ስታዲየም እስካሁን ግንባታ ላይ ነው።

– ሐረር ስታዲየም እስካሁን በግንባታ ላይ ነው።

ከዚህ ጋር በከፍተኛ ደረጃ የስታዲየም የአስተዳደር ችግር እንዳለ ፅፈዋል። ከአደይ አበባ በቀር ሌሎቹ ስታዲየሞች የአስተዳደር ችግር እንዳለባቸው እና የስታዲየሙን እያንዳዱን ነገር በትክክል መግለፅ እንኳን እንደማይችሉ ገልፀውልናል። በስተመጨረሻ ያሉት ነገር ቢኖር ያለን ጊዜ በጣም አጭር ነው፤ ሁሉም ስታዲየሞች በግንባታ ላይ ናቸው። ሁሉም በመንግስት የሚገነቡ እንደሞሆናቸው መጠን በማንኛውም መንገድ ከፌዴራል መንግስት ጋር በማያያዝ መንገድ መፈለግ አለባችሁ። የመንግስት ቁርጠኝነት በጣም አስፈላጊ ነው። ይህን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ሀገር በቀል ኮሚቴ በማዋቀር ለእያንዳንዱ የስታዲየም ባለቤቶች ለቻን ውድድር ሊዘጋጁ የሚገባውን ሰነዶች አስተላልፈዋል። ከዚህ በተጨማሪ የሁሉም ሜዳዎች የሳር ሁኔታ ምንም አጥጋቢ አይደለም።

* አስራ ሁለት የመለማመጃ ስፍራ የታየበት ሂደት ውስጥ ማንኛውም ሜዳ መስፈርቱን ማለፍ አልቻለም። በትንሹ ለማየት አዲስ አበባ ስታዲየም፣ አካዳሚ ሜዳ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሜዳ ወዘተ… ወደ ድሬዳዋ ስንሄድ ደግሞ ምንም አይነት የመለማመጃ ሜዳ የለም። የምናወራው ስለ ቻን መስፈርት ነው። የመለማመጃ ሜዳው ማሟላት አለበት ከተባለው ውስጥ የሜዳው የሳር ጥራት ጉዳይ፣ የሜዳ ላይ መብራት በትንሹ 500 ላክስ መኖር አለበት፣ የመልበሻ ክፍል፣ የመቀመጫ ወንበር፣ መፀዳጃ እና አጥር ሊኖረው ይገባል የሚል ነው።

* በሆቴል በኩል ሙሉ ለሙሉ ደስተኛ ናቸው። ድሬዳዋ ላይ ግን ያነሱት ቅሬታ አለ።

* በአየር መንገድ ጉዳይ በሁሉም ደስተኛ ናቸው። ነገር ግን በመጀመሪያው የግምገማ ሰዓት ላይ የሀዋሳ አየር ማረፊያ የመንገድ ስራ አላለቀም ነበር። ይህ ካላለቀ ውድድሩ በጭራሽ መምጣት እንዴሌለበት ገልፀዋል። ይህም በሁለተኛው ግምገማ ወቅት ተስተካክሏል።

በሁለተኛው የግምገማ ወቅት በመጋቢት ወር ውስጥ የተደረገ ሲሆን በዚህ ጊዜ በሁለት የካፍ የስራ አባላት፤ አህመድ ሀራስ (በመጀመርያው የግምገማ ጊዜ አብሮ የነበረው ሪፖርቱን የሚፅፈው የክለብ ላይሰንስ አስተዳደር) እንዲሁም የኢትዮጵያን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ፣ የህዝብ ግንኙነት ክፍል ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን የነበሩበት እንዲሁም ሁለት የካፍ ካሜራ ባለሙያዎች ነበሩ። በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ሀዋሳ፣ መቐለ፤ ባህር ዳር እና አደይ አበባ ስታዲየሞችን ለማየት ተሞክሯል። በዚህ ወቅት የመጀመሪያው ዕይታ የነበረው በሜዳው ላይ የነበረው የመጫወቻ ሳር፣ የሜዳው የውስጠኛው መሰረታዊ ክፍሎች የግንባታ ሂደት እንዲሁም አጠቃላይ ገፅታው ነበር የታዩት። በአጭሩ ውጤቱን ለመግለፅ፥

– ሀዋሳ የሜዳው ሳር የባለሙያ እገዛ ይፈልጋል። በስታዲየሙ ዘመናዊ ኤሌክትሮኒክስ መሳርያ መኖሩ ጥሩ ጎን ነበር።

– የትግራይ ስታዲየም ከዚህ ቀደም ኢንተርናሽናል ውድድር ለማካሄድ ፍቃድ ከትግራይ ክልል እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የጠየቅን ሲሆን አህመድ ሀራስ ሲመጣ ገና የውጪ ገፅታውን በማየት ከስምንት ወር በፊት ያየው ነገር ነው። ግንባታው ሙሉ ለሙሉ አላለቀም በማለት ፍቃዱን ከልክሏል።

– ባህር ዳር ስታዲየም በግንባታው ረገድ ምንም እንቅስቃሴም ሆነ ለውጥ የለውም። የመለማመጃው ሜዳ ምንም አልተለካም።

– የአደይ አበባ ስታዲየም ግንባታው ያልተጠናቀቀ ከመሆኑ ባሻገር የውጭም ሆነ የውስጠኛው ግንባታ ክፍል አድንቀዋል።

ከዚህ በኋላ በኢንተር-ኮንትኔንታል ሆቴል የካፍ ተወካይ ባለበት በሁለተኛው ዙርም ሆነ አንደኛው ላይ የታዩት ነገሮች ላይ ውይይት ተደርጓል። በዚህ ውይይት ከየክልሉ ስታዲየሞች ተወካይ እንዲሁም ከስፖርት ኮሚሽን ኃላፊው አቶ ርስቱ ይርዳው ባሉበት ውይይት ተደርጓል። ረዘም ላለ ሰዓት የተደረገው ይህ ውይይት የካፍ ተወካይ የተናገረው በአጭሩ ለመግለፅ ያህል ” የግምገማው ጊዜ ግምት ውስጥ በማስገባት እንዲሁም ውድድሩ ከመጀመሩ ከሶስት ወር በፊት ቅድመ ውድድር የሚዘጋጅ መሆኑን ታሳቢ አድርጎ ነው የተሰራው። በግምገማው ወቅት የታዩት ስታዲየሞች በጣም ግዙፍ በጣም አስደሳች ናቸው። ይህም ትልቅ አቅም እንዳለ የሚሳይ ሲሆን ይህን አቅም ግን ሙሉ ማድረግ የሚቻለው ግን የመንግስት ቁርጠኛ አቆም ሲኖር ብቻ ነው። እኛ ልናግዝ የምንችለውን እንሞክራለን። የራሳችሁ ማሳመኛ ይዛቹ ቅረቡ። እኛ እዚህ ስንመጣ ውሳኔ ሰጭ አይደለንም። ያየነውን ነገር ማስተላለፍ ነው። ” ሲል ገልጿል። የስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ርስቱ ይርዳው በጉዳይ ላይ በሰጡት አስተያየት ” እኛ አሁን ላይ በርካታ ስታዲየሞችን በመገንባት ላይ ነን። በደንብ አግዙን፤ ይህን ውድድር ባትወስዱብን።” በማለት ነበር የገለፁት። እነርሱም ሪፖርቱን ለካፍ እንደሚያቀርብ ገልፀው ነበር የተለያየነው። ቀጥሎም በሚያዝያ 11-12 በነበረው የካፍ ስብሰባ ላይ ውድድሩ ከኢትዮጵያ ተነጥቆ ወደ ካሜሩን ዞሯል።


ባህሩ ጥላሁን

በሁለተኛው ግምገማ ጊዜ ስለነበረው ተጨማሪ ሀሳቦች ለማንሳት ሀዋሳ ላይ የተመለከትናቸው ያልተጠናቀቁ ስራዎች በተለይም የመለማመጃ ሜዳዎች መስፈርቱን ስናያቸው፤ አንደኛ አነስተኛ ስታዲየም መስራት የሚያስችለን ነው። ሀዋሳ አርቴፍሻል ሜዳን የምለማመጃም ሜዳ በማድረግ ብናሳይም ሜዳው ተፍጥሯዊ መሆን አለበት። ነገር ግን እስቲ እንይ ብለው ወደ ውስጥ ስንገባ የውስጣዊ ክፍሉ ግንባታ መጠንቀቅ አለበት። በሀዋሳ ቆይታችን እጅጉን የተወደደው የዩንቨርስቲው ሜዳ ነው። የሜዳው ሳር ግን በድጋሚ ቅሬታን አስነስቷል። የሀዋሳ ኢንተርናሽናል ስታዲየም ላይ ሳሩ በድጋሚ ተነስቶ ቢሰራም የጥራት ጉድለት አለው። የካፍ ተወካይ አህመድ ሀራስ ኢትዮጵያ ውስጥ የጨዋታ ሜዳ ባለሙያ እንዴሌለ በመግለፅ ከሞሮኮ ወይም ከፈረንሳይ ባለሙያ ማምጣት አስፈላጊ መሆኑን ገልፀው እኛም ልናግዝ እንችላለን። አማካሪዎችን በመላክ መስራት እንዲችል ኢትዮጽያ ውስጥ ያሉ ስታዲየች ዓለም አቀፍ የሜዳ ላይ ሳር እንዲኖራቸው ያስፈልጋል። ሀዋሳ ላይ ፖውዛ እና ስክሪን መኖሩ ከሌሎች ለየት የሚደርገው ነው።

– ባህር ዳር ላይ አራት ቡድኖችን በአንድ ላይ ማስተናገድ አይችልም። በዚህም ምክንያት የዲዛይን ለውጥ ማድረግ ይኖርበታል፤ የሚዲያ እና የVIP መግቢያ አንድ ላይ ነው። ይህም ሊለያይ ይገባዋል ሲሉ ባህርዳ ር ላይ ትልቅ ኃይል ማመንጫ ጂኒሪተር መኖሩ ከሌሎቹ ለየት አድርጎል።

– ትግራይ ስታዲየም የመልበሻ ክፍል ግንባታ አለማለቁን ገልፀዋል።

– አደይ አበባ ስታዲየም ግንባታውን በማድነቅ በይበልጥ ሲጠናቀቅ አስተያየት የሚሰጡበት ይሆናል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሪሽን ይህን ችግር ለመፍታት የውስጥ ኮሜቴ በማቋቋም ምክረ ሀሳቦችን በማዛጋጀት ለመንግስት ጥያቄ አቅርበዋል። ነገር ግን እስካሁን ምላሽ አላገኘንም። ፌዴሬሽኑ ከመንግስት እንዲሁም ከክልል አስተዳደር ጋር በጋራ ለመስራት ጥረት እየተደረገ ነው። ፕሬዝዳንታችን በካፍ ስብሰባ ወቅት ተገኝተው ነበር። በወቅቱ የተላለፈው መልዕክት ኢትዮጵያ በጣም ትላልቅ ስታድየም ግንባታ ላይ ነች፤ ይህ መልካም ጅማሮ ነው። በቀጣይም ሊደረጉ የሚችሉ ውድድሮች መምራት የሚስችላት አቅም እየፈጠረች ሲሆን ለአሁኑ የቻንን ውድድር ማዘጋጀት ሊከብዳት እንደሚችል በማሰብ ለካሜሩን ተሰጥቷል። ከዚህ ጋር ውድድሩን ስትነጠቅ አብሮ የሚነሳው የቅጣት ጉዳይ ነው። ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ ከካፍ ባልሳልጣን ጋር ባደረጉት ውይይት ቅጣቱ እንዳይኖር ስራ ተስርቷል። በክልል አስተዳደር የሚገኙት ስታዲየሞች በአግባቡ ካለቁ በቀጣይ 2022 የሚደረገውን ውድድር መልሶ ለኢትዮጵያ ለመስጠት ሀሳብ እንዳለ ተገልፆል።

ከሁለቱ ማብራሪያ በመቀጠል ከጋዜጠኞች ጥያቄዎች የቀረቡ ሲሆን ምላሾቹን እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

– በፈንሳይኛው ቃለመጠይቅ ቀጥተኛ ትርጉሙ አህመድ አህመድ ኢትዮጵያ ራሷን አግልላለች ነው ያሉት። ይህ ሀሳብ ግልፅ ቢሆንልን

ስለ ፈረንሳይኛው ቃለ መጠየቅ መረጃው የለኝም። ፌዴሬሽኑን የሚመለከት ጉዳይ ከሆነ ፌዴሬሽኑ መልስ ሊሰጥበት ይገባል። እኔ እሰከማቀው ድረስ ምንም አይነት ዊዝድሮ ማድረግ የለም። በሚያዝያ ወር በቀረበው ሪፖርት ማፅደቃቸውን ነው የምናውቀው። እንደውም በእኛ በኩል የቀረበው ውድድሩ በሶስት ወር ይራዘምልን ነበር። ይህም የሆነው ዝግጅት ለማድረግ ነበር። ወዲያ ወዲህ ማለት አይጠቅምም ባለን ችግሮች ምክንያት ነው የተነጠቅነው። በቀጣይ መስፈርቱን ማሟላት ብቻ ነው የሚጠበቅብን።

የአስተዳደሩ የግንዛቤ ችግር እና የሀሳብ ልዩነት

ከዚህ በፊት አቶ ጥበቡ ጉርፉ ነበሩ በስታዲየሞች ዙሪያ መግለጫ የሚሰጡት። አቶ አዝመራው አሁን ላይ ነው የተካተተው በሁለተኛው ዙር ግምገማ ጊዜ ነበር። ልዩነት ሳይሆን በሁለተኛው ግምገማ ወቅት የነበረው መልካም ተነሳሽነት ጥሩ ስለነበር ውድድሩ ይደረጋል የሚል እምነት ስለነበር ነው። የነበረው መልካም ገፅታ ግምት ውስጥ ገብቶ ነው በተለይም አቶ ርስቱ ሲያስረዱ የነበሩት። ከነዚህ ውጭ የወለጋ፣ የአሶሳ፣ የወልድያን ወዘተ… ስታዲየም በመጥቀስ ውድድሩን ለማካሄድ የነበረ ፍላጎት ነበር። የፊፋ ስታንዳርድ ለማለት ከፊፋ ወይም ከካፍ ባለሙያ ተልኮ ማረጋጋጫው ሲደርስ ነው። የግንባታው ሂደት እግር ኳስ ሜዳ የሚፈልገው ሊሆን ይችላል። ግን የፊፋ ስታንዳርድ በማረጋገጫ ብቻ ሲሰጥ ነው።

ይህን ውድድር ስንቀበል ከጠቅላይ ሚኒስተር እሺታን አግኝታቹ ነበር?

አዎ። መጀመሪያም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ማረጋጋጫ ወስደናል። ከቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ፍቃድ አግኝቷል። ነገር ግን ከዛ በኋላ የመዋቅር ለውጥ ተደርጓል። ምንም ለውጥ ቢኖር እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ግንኙነቱን አላቆመም።

በ2022 ኢትዮጵያ ማዛጋጀት ትችላላች?

አዎ። በጣም እንችላለን። አሁን የተጀመሩት በትክክል ካለቁ ለምን አንችልም። የሚገርማቹ ነገር በዚህ ሳምንት ከፈረንሳይ ግሪጉሪ የሜዳ ሳር ጉዳይ አማካሪ ድርጅት በእያንዳንዱ ሜዳ ላይ ምክረ ሀሳብ ይዞ ይመጣል። የድርጅቱን ብሮሸሮች ለየክልል አስተዳዳሪዎች ልከናል። ድርጅቱ በካፍ ዕውቅና ያለው ነው።

የመጀመሪያው ሪፖርት ለምን ለሚዲያ አልቀረበም?

የመጀመርያ ጊዜ ሪፖርት እንደመጣ የላክነው ለየክልል አስተዳዳሪዎች ነበር። ለሚዲያ ለምን አልደረሰም የሚለው ሪፖርት ሰለማይሰጥ ነው። ነገር ግን ተጠቃሎ ተጨምቆ ቢሰጠን በሚል ቢያዝ ጥሩ ነው።

የተቋቋመው ኮሜቴ ስራውን እየሰራ ነው ወይ? ምን ያህልስ በጀት ጥያቄ አቀረበ? ከማንስ ተሞክሮ አይቷል?

ኮሚቴው ምክረ ሀሳቡን አዘጋጅቶ ያቀረበው የሞሮኮን ተሞክሮ በጥልቀት ካየ በኋላ ነው። እንደውም ሞሮኮ ሁሉም ስታዲየሞቹ ብቁ በነበሩበት ወቅት ውድድሩን ለማዘጋጀት 13 ሚሊዮን ዶላር አውጥታለች። በአንፃሩ ወደኛ ስንመጣ 10-11 ሚሊዮን ተጠይቆ ምላሽ እየጠበቅን ነው። የእግርኳስ ፌዴሬሽኑ ከክልል አስተዳደር ጋር አብሮ እየሰራ ነው። በተለይም ትግራይ ስታዲየም ስራ እየተሰራ ነው። እንዲህ አይነት መፍትሄ እየተሰጠበት ነው ያለው።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

error: