የአሰልጣኞች አስተያየት | መከላከያ 1-0 ባህር ዳር ከተማ

በ23ኛ ሳምንት መርሐ ግብር መካከል አዲስ አበባ ላይ አዲስ አበባ ስታድየም ከተከናወነው የመከላከያ እና የባህርዳር ከተማ ጨዋታ ፍፃሜ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

“አሁን ላይ የማሸነፍ ሚስጥሩን አግኝተነዋል ” አሰልጣኝ በለጠ ገብረኪዳን

ስለ ጨዋታው

ጫዋታው እንዳያችሁት ነው ከእረፍት በፊት ኳስን ተቆጣጥረን ተጫውተናል መጨረስ የሚገቡንን እድሎች አልተጠቀምንም እንደምታውቁት ያለፏትን ጌዜያት ቡድናችን ከብዙ ሽንፈት ነው የመጣው አሁን ላይ ግን ባለፈው ከሜዳችን ውጭ አሸንፈናል ዛሬም ልጆቼ ያላቸው መነሳሳት እና የማሸነፍ ፍላጎት በጣም ጥሩ ነው በውጤቱ ልጆቹ ያደረጉት መስዋትነት በጣም ደስ ብሎኛል።

የውጤቱ ቀጣይነት

ቡድናችን ኳስን ይዞ የሚጫወት ነው። በሁሉም ቦታ ክህሎት ያላቸው ተጫዋቾች አሉን። እስካሁን ያቅተን የነበረው ማሸነፍ ነው። አሁን ላይ ይህ ችግር ተፈቶ ሚስጥሩን አግኝተነዋል። በቀጣይ እያሸነፍን የምንጓዝ ይሆናል።

” ውጤቱን በፀጋ እንቀብለዋለን” ጳውሎስ ጌታቸው

ስለ ጨዋታው

ጨዋታው ጥሩ ነበር። በአጋጣሚ ጎል ተቆጠረብን። ከዛም በኋላ ያለውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በማጥቃት እንዲሁም የአጥቂ ቁጥር በመጨመር ጫና ማድረግ ችለን የነበረ ቢሆንም አልተሳካም። ውጤቱንም በፀጋ ተቀብለናል።

ከቡድኑ ጋር ስለመቀጠላቸው

ከባህር ዳር ጋር ምንም የምንለያይበት ምክንያት የለም። አንዳንድ ክስተቶች ነበሩ ቡድኑን የማይወክሉ። በዛም ምክንያት በወቅቱ ያን ንግግር ልናገር ችያለሁ። አሁን ላይ ሁሉ ነገር በንግግር ተፈቷል። የኔ መመለስ ዘጠና ዘጠኝ በመቶ ደጋፊውን አስደስቶታል።

በቅርብ ጨዋታዎች የኋላ ክፍሉ በዛ ያለ ግብ ማስተናገዱ

ቡድናችን ሲጫወት ክፍት ነው። ዛሬ ላይ የራሳችንን ክፍል በመሸፈን ነበር ስናጠቃ የነበረው። ቡድኑ ውስጥ የተጫዋቾች ጉዳት አለብን። ዛሬ ላይ ከተጎዱብን አንፃር ስታየው በጣም ነው የምንጎዳው። ከኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ በኋላ የነበረውን ክፍተት እያረምን ነው። ከታች እንደመምጣታችን እየተስተካከለ ነው የሚመጣው። ትልቁ ችግር የዛሬ ዓመት ከከፍተኛ ሊግ ውድድር ወደ ፕሪምየር ሊጉ ሲያድግ የነበረው የእረፍት ጊዜ ማጠር አሁን ላይ ተፅዕኖ ፈጥሯል። ልጆቼ ያለ እረፍት ሁለት አመት ማለት ነው ተጫውተዋል። ይህ ደሞ ጉልበት ላይ ከፍተኛ ድካም ያስከትላል። ከዚህ በኋላ ኃላፊነቱን እኔ ጋር ነው። እነሱን በድጋሚ ብቁ በማድረግ በሚቀጥለው ጨዋታ ወደ አሸናፊነት እንመለሳለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡