ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ኢትዮጵያ ቡና ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

በርካታ ግቦች እና ማራኪ እንቅስቃሴ ማስተናገድ የናፈቀው የሸገር ደርቢን የተመለከቱ ጉዳዮችን በተከታዩ ቅድመ ዳሰሳችን አንስተናል።

አዲስ አበባ ከ23ኛ ሳምንት ጨዋታዎች መካከል ዘግይቶ የሚጀምረው ደርቢዋን 10፡00 ላይ ታስተናግዳለች። ከደጋፊዎች ህብረ ቀለም እና የሜዳ ውጪ ሽር ጉድ ሌላ በሜዳ ላይ እጅግ እየተዳከመ የመጣው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ አሁንም ተጠባቂነቱ እንዳለ ነው። ባለፉት ሰባት ጨዋታዎች አራቱ ያለግብ መጠናቀቃቸውን እና ኢትዮጵያ ቡና አንድ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ሦስት ግቦችን ብቻ ማስቆጠራቸውን ላስተዋለ ግን በፉክክር የተሞላ ፍልሚያን መጠበቅ ሞኝነት ይመስላል። ጨዋታው ቅዱስ ጊዮርጊስ ትናንት ወዳሸነፈው ፋሲል ለመቅረብ አለፍ ሲልም በሲዳማ እና ጅማ ደረጃውን ላለመነጠቅ የሚያደርገው ሲሆን ኢትዮጵያ ቡናም ድልን ካሳካ ወደ ስድስተኝነት ከፍ ማለትን እያለመ ወደ ሜዳ የሚገባበት ነው።

ጉድት ላይ የሚገኙት ተመስገን ካስትሮ ፣ ሚኪያስ መኮንን እና ሱለይማን ሎክዋን በዛሬው ጨዋታም የማይጠቀመው ኢትዮጵያ ቡና ባህር ዳርን በሰፊ ጎል ባሸነፈበት ጨዋታ ትክክለኛውን የጨዋታ ስሌት ያገኘ ይመስል ነበር። አቡበከር ናስርን በአጥቂ አማካይነት ሁሴን ሻባኒን ደግሞ በመጨረሻ አጥቂነት የተጠቀመው ቡድኑ በተለይም ኳስ በሚነጥቅባቸው ጊዜያት የመልሶ ማጥቃት ቅፅበቶችን በመፍጠር የተዋጣለት ሆኖ ነበር። ሆኖም በዋነኝነት የአቡበከር ቅጣት አሰልጣኝ ገዛኸኝን ዕድለ ቢስ ያደረጋቸው ይመስላል። በአዳማው ጨዋታ ካሉሻንም በጉዳት አጥቶ የነበረው ቡና ያደረጋቸው አስገዳጅ ለውጦችም በተመሳሳይ አኳኋን ጨዋታውን እንዳይቀርብ ሳያስገድዱትም አይቀርም። ዛሬም ቡድኑ የአቡበከርን አዲስ ሚና በተጨዋች ቅያሪ መሸፈንን እንጂ የቅርፅ ለውጥ ማድረግን ላይመርጥ ይችላል። ነገር ግን ባህር ዳርንም ሲገጥም ቢሆን በቀላሉ የኳስ ቁጥጥርን ሲያሳካ አለመታየቱ ዛሬም በታታሪ አማካዮች ከተሞላው የመሀል ክፍሉ የሚነሱ ኳሶችን በፍጥነት ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል በማድረስ ወደፊት እየጠበበ በሚሄድ የመልሶ ማጥቃት አቀራረብ አስቻለው ታመነ ከሌለው የቅዱስ ጊዮርጊስ የኋላ ክፍል ጋር እንደሚፋለም ይጠበቃል።

አሰልጣኝ ስትዋርት ሀል በሦስት ተከላካዮች የሚጀምረው የአሰላለፍ ምርጫቸውን ወደ አራት ከፍ ካደረጉ በኋላ ባለፉት ዓመታት የቅዱስ ጊዮርጊስ ባህሪ የነበረውን የመስመር ጥቃት አልፎ አልፎ እየተመለከትን እንገኛለን። መቐለን በገጠሙበት ጨዋታ ሁለተኛ አጋማሽ ያደረጓቸው ለውጦች ይህንን የቡድኑን አቀራረብ አጉልቶ ያሳየ መሆኑ ደግሞ የዛሬውን ጨዋታ የሚቀርቡበትን መንገድ ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ይታሰባል። በዚህም የማጥቃት ኃላፊነት ያለው አማካይ ሀምፍሬዬ ሚዬኖ በታደለ መንገሻ ከተተካ በኋላ የነበረው የቡድኑ ፈጣን የማጥቃት ሽግግር ታደለንም ከረጅም ጊዜ በኋላ የመጀመሪያ መሰለፍ ዕድል እያገኘ እንዳለው ኢሱፍ ቦውርሀና ሁሉ የአሰልጣኙን ትኩረት ሊያሰጠው ይችላል። በሌላ በኩል ብዙ ዕምነት የሚጣልበት የናትናኤል እና ሙሉአለም ጥምረት ፈርሶ ሁለቱን የማጥቃት አማካዮች አብረን ልንመለከት የምንችልባቸው ደቂቃዎች ሊኖሩ ይችላሉ። በተጨማሪም አቤል ያለውን ከመስመር እንዲነሳ ሪቻርድ አርተር ደግሞ የፊት አጥቂነት ሚና ኖሯቸው የዛሬውን ጨዋታ ሊጀምሩ ይችላሉ። ቡድኑም ከአማካዮቹ ወደ መስመር በሚላኩ ኳሶች በተለይም በአቤል ያለው በኩል ያመዘኑ ጥቃቶችን መሰንዘር ምርጫው እንደሚያደርግ ይጠበቃል። ጊዮርጊስ ከሳላዲን ሰዒድ ፣ ምንተስኖት ከበደ ፣ ጌታነህ ከበደ እና መሀሪ መና ጉዳት በተጨማሪ አስቻለው ታመነን በህመም ምክንያት አይጠቀምም።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱ ቡድኖች ከ1991 የውድድር ዓመት ጀምሮ 39 ጊዜ የተገናኙት ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ 18 እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡና 6 ጊዜ ድል ቀንቷቸዋል። በ15 አጋጣሚዎች ደግሞ ጨዋታቸውን በአቻ ውጤት አጠናቀዋል።

– 73 ግቦች በተስተናገዱባቸው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታዎች ቅዱስ ጊዮርጊስ 49 ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ 24 ጊዜ ኳስ እና መረብን አገናኝተዋል።

– 13 ጨዋታዎችን በሜዳቸው ያከናወኑት ኢትዮጵያ ቡናዎች ስድስቱን በድል ሲወጡ አራት የአቻ እና ሦስት የሽንፈት ውጤቶች አስመዝግበዋል።

– የአዲስ አበባ ስታድየም ላይ 11 ጨዋታዎች ያከናወነው ቅዱስ ጊዮርጊስ ሰባቱን ሲያሸንፍ ሦስት የአቻ እና አንድ የሽንፈት ውጤቶች አስመዝግቧል።

ዳኛ

– ጨዋታውን ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ ይመራዋል። አርቢትሩ በውድድር ዘመኑ እስካሁን በመራቸው አስር ጨዋታዎች 51 የማስጠንቀቂያ ካርዶችን ሲያሳይ አንድ ጊዜ በቀጥታ ቀይ ካርድ ሁለት ጊዜ ደግሞ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ሁለት ተጫዋቾችን ከሜዳ አሰናብቷል። ቡና ከፋሲል ፤ ጊዮርጊስ ከአዳማ ያደረጓቸውን ጨዋታዎች የዳኘው አቢትሩ የመጀመሪያውን ዙር የሸገር ደርቢ መምራቱ ይታወሳል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ኢትዮጵያ ቡና (4-2-3-1)

ወንድወሰን አሸናፊ

አህመድ ረሺድ – ክሪዝስቶም ንታምቢ – ቶማስ ስምረቱ – ተካልኝ ደጀኔ

አማኑኤል ዮሀንስ – ዳንኤል ደምሴ

እያሱ ታምሩ – ካሉሻ አልሀሰን – አስራት ቱንጆ

ሁሴን ሻቫኒ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-3-3)

ፓትሪክ ማታሲ

ሄኖክ አዱኛ – ሳላዲን በርጌቾ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ – ኢሱፍ ቡርሀና

ናትናኤል ዘለቀ – ሙሉዓለም መስፍን – ታደለ መንገሻ

አቤል ያለው – ሪቻርድ አርተር – አቡበከር ሳኒ


© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡