ሴቶች 1ኛ ዲቪዝዮን | አአ ከተማዎች ሁለት ጊዜ ከመመራት ተነስተው ከድሬዳዋ ጋር አቻ ተለያይተዋል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ 20ኛ ሳምንት ዛሬ አንድ ጨዋታ ተካሂዶ አዲስ አበባ ከተማ ከ ድሬዳዋ ከተማ ጋር 2-2 ተለያይተዋል።

09:00 ላይ በህሊና ፀሎት የተጀመረው የሁለቱ ቡድን ጨዋታ በቦታው ለታደመው የስፖርት ቤተሰብ አዝናኝ እንቅስቃሴ የታየበት ነበር። በመጀመሪያዎቹ 15 ደቂቃዎች ተጭነው ለመጫወት ሙከራ ያደረጉት ባለሜዳዎቹ በእንቅስቃሴ ብልጫ ቢኖራቸውም በግብ እድል ማጀብ ግን አልቻሉም። በተቃራኒው በመልሶ ማጥቃት ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ድሬዎች በአይዳ ዑስማን የግል ጥረት በተደጋጋሚ የአዲስ አበባን የግብ ክልል በመፈተሽ ቀዳሚውን ጎል አስቆጥረዋል። በ17ኛው ደቂቃ ላይ አይዳ ከመሐል ሜዳ ወደፊት የተጣለላትን ኳስ በአግባቡ ተቆጣጥራ በቀኝ መስመር በኩል በመግባት አክርራ መትታ ድሬን ቀዳሚ አድርጋለች።

ከጎሉ መቆጠር በኋላ መነቃቃት የታየባቸው ድሬዳዋዎች ለአዲስ አበባ ተከላካይ ራስ ምታት በነበረችው አይዳ አማካኝነት ሙከራዎች አድርገዋል። በ19ኛው ደቂቃ እንደመጀመሪያው ጎል ተመሳሳይ እድል አግኝታ ሳትጠቀመበት ስትቀር በ35ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር በፍጥነት አጥብባ በመግባት አክራ የመታችው ኳስ የግቡን ብረት ለትሞ ወጥቷል። በ38ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ከተከላካይ የተሻገረላትን ኳስ የአዲስ አበባን ግብ ጠባቂ ቀድማ ብትወጣም በግብ ጠባቂዋ አናት ላይ በማሳለፍ ለማግባት ብትሞክርም የኳሱ አቅጣጫ በመለወጡ ግብ ከመሆን ቀርቷል።

ከድሬዳዋ በተቃራኒው በግብ ሙከራ ረገድ ደካማ የነበሩት አዲስ አበባዎች በአስራት ዓለሙ እና ሕይወት ረጉ የማጥቃት አጋጣሚዎችን ቢፈጥሩም እምብዛም ስኬታማ ሳይሆኑ የመጀመርያው አጋማሽ በድሬ 1-0 መሪነት ተጠናቋል።

በሁለተኛው የጨዋታ ምዕራፍ ባለሜዳዎቹ የአቻነት ግብ ፍለጋ ተጭነው የተጫወቱ ሲሆን በሕይወት ረጉ ከርቀት በሚመቱ ኳሶች የድሬዳዋን ግብ መፈተሽ ችለዋል። በ63ኛው ደቂቃ ላይም የተገኘችውን የግብ አጋጣሚ አስራት ዓለሙ ከድሬዳዋ ግብ ጠባቂ ቀድማ ደርሳ በግብ ጠባቂዋ አናት ላይ በመስደድ የአቻነቱን ግብ ማስቆጠር ችላለች። ሆኖም አአ ከተማዎች ተጨማሪ ግብ ፍለጋ ወደ ፊት ተስበው በሚጫወቱበት ወቅት ትዝታ ፈጠነ በቀኝ በኩል ያሻገረችውን በነፃ አቋቋም ላይ የነበረችው ስራ ይርዳው በአግባቡ በመቆጣጠር አስቆስጥራ ድሬን ወደ መሪነት መልሳለች።

እንግዶቹ ተጨማሪ ግብ ባያስቆጥሩም ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ቶሎ ቶሎ በመድረስ የፈጠሩት ጫና ከባድ ነበር። አዲስ አበባዎችም በተመሳሳይ ጥረት በማድረግ ሊጠናቀቅ 10 ደቂቃ ሲቀረው የአቻነት ጎል አግኝተዋል። በ79ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይራ ወደ ሜዳ በገባችው ፎዚያ መሐመድ ከማዕዘን ምት ያሻማችው ኳስ በመንጠር ያለምንም ንክኪ ወደ ግቡ መረብ አምርቷል። ከአቻነቱ ግብ መቆጠር በኋላም በጨዋታው ጥሩ ስትንቀሳቀስ የነበረችው ህይወት ከርቀት የምትመታቸው ኳሶች ውጤታማ ባይሆኑም የድሬዳዋን ግብ ጠባቂ ሲፈትኑ ታይተዋል። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይሰተናግድበት 2-2 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

በሊጉ ትላንት ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ በሜዳው ጥረት ኮርፖሬትን በጤናዬ ለታሞ ሁለት ጎሎች 2-1 ሲያሸንፍ በሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ ነገ ኤሌክትሪክ ጌዴኦ ዲላን ያስተናግዳል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

error: