የአሰልጣኞች አስተያየት | ወልዋሎ ዓ/ዩ 1-1 ጅማ አባ ጅፋር

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 23ኛ ሳምንት ጨዋታ ወልዋሎ ከ ጅማ አባ ጅፋር ጋር 1-1 ከተለያዩ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

“በስነ ምግባር አልደራደርም፤ እኔም ብሆን ስርዓት ከሌለኝ መቆየት የለብኝም” ዮሐንስ ሳህሌ

ስለ ጨዋታው

አሁንም የመጨረስ ችግር አለብን። ብዙ አጋጣሚዎች እናገኛለን። ግን ኃላፊነት ወስዶ የሚጨርስ የለም። በዛ እየተቸገርን ነው ያለነው።
በሚቀሩን ሰባት ጨዋታዎች ላይ እያስተካከልን እንሄዳለን። የግል ስርዓት ችግር አለ። እሱን ካስተካከልን ሌላው ነገር ጥሩ ነው። የተሰሩት ስህተቶች የሚያጋጥሙ ናቸው። ግን ያገኘናቸውን ብንጨርስ ወደዚ አንገባም ነበር። ብዙ ጊዜ አጨራረስ ላይ ችግር አለ። እሱ ማስተካከል ይገባናል።

የጨዋታ ውጭ ነው ስለተባለው ግብ

ዳኛ የጨዋታ ውጭ ነው ካለ ምንም ማድረግ አትችልም። ሌላም ስህተት ቢኖር ከዳኛው ጋር ምንም ማድረግ አትችልም። በዛ ሰዓት ባለ ስልጣኑ እሱ ነው።

ቡድኑ በጥቂት ተጫዋቾች ላይ ጥገኛ ስለመሆኑ

እኔ ብዙ ነገር ካለቀ በኃላ ነው የመጣሁት። በቡድኑ ውስጥ አምስት የውጭ ተጫዋቾች ስለነበሩ የውጭ ተጫዋችም ቢሆን የምናመጣበት ዕድል አልነበረም። ብዙ ችግሮች ስላሉብን ያንን ለመፍታት እየሰራን ነው። በዛ ላይ ስድስት ተጫዋቾች ቀንሰናል፤ ምንም የገዛነው የለም። ከታች አራት ነው ያሳደግነው። ስለዚህ ያለንን ይዘን ይሄን ችግር ከነችግራችን መወጣት ነው ያለብን።

የባለፈው ሳምንት ውጤታማ የአጥቂ ጥምረት ዛሬ አለመደገም

ችዞባ በስነ-ምግባር ችግር ከክለቡ ጋር የሚኖር አይመስለኝም። ክለቡን፣ ተጫዋቾችን፣ ደጋፊውን ባለማክበር የሰራው የስነ ምግባር ግድፈት ስላለ ነው። በስነ ምግባር ደሞ አልደራደርም፤ የምደራደርበት ምክንያት የለም። የውጭ ሃገር ተጫዋች ኢትዮጵያ መጥቶ የስራ ዕድል አግኝቶ ላደጉት ወጣት ተጫዋቾች ጥሩ አርዓያ እንጂ መጥፎ አርዓያ ከሆነ ክለቡ ውስጥ መኖር የለበትም። አንድ ተጫዋች ኳስ ይጫወታል ብለን ከነ ብልግናው ይዘን አንሄድም። ስለዚህ እሱ የሚቀጥል አይመስለኝም። ከማንም በላይ ማልያውና ክለቡ ይበልጣል።

ቀጣይ ሳምንት ስላላቸው ወሳኝ ጨዋታ

እከሌ እከሌ አንልም። እነሱ ቢያሸንፉ ሶስት ነጥብ እኛ ብናሸንፍም ሶስት ነጥብ ነው። ለማልያችን እና ለደጋፍያችን ነው የምንጫወተው። ማድረግ ያለብንን እናደርጋለን። የተለየ አቀራረብ አይኖርም። ባለን ኃይል ባሉን ተጫዋቾች ለኛ ሊመቸን በሚችል መንገድ እንጫወታለን። በርግጥ አንድ ቡድን ከአንድ ቡድን ስለሚለያይ አንዳንድ የምናደርጋቸው ለውጦች ሊኖሩ ይችላሉ። እንደ ቡድኑ እና እንደ ሜዳው የአጨዋወት ስልታችን ልንቀይር እንችላለን። ለሶስቱ ነጥቡ ከማንም ጋር አንደራደርም።

የቡድን ጥበት

ባለጌ እና ስርዓት የሌለው ይዘህ ከምትሄድ ይሻላል። የኳሱ ዋና ዓላማ መሸነፍ ብቻ ሳይሆን ከስርዓት ጋር ነው።
ገና ለገና ጎል ያገባሉ ብለህ ከህብረተሰቡ ጋር የማይሄዱ እና ለህብረተሰቡ የማይጠቅሙ ለወጣቶች አርዓያ የማይሆኑ ተጫዋቾች ይዘን መሄድ አንችልም። ሁሉም በክለቡ ህግ ስር ነው ከዛ ውጭ ግን በክለቡ አይቆይም። እኔም ብሆን ስርዓት ከሌለኝ መቆየት የለብኝም።

“ከእረፍት በኃላ አጨዋወታችንን ለውጠን ውጤቱን ይዘን ወጥተናል ” የሱፍ ዓሊ

ስለ ጨዋታው

ለሁለት ጊዜ የሚሆን የወልዋሎን ጨዋታ አይተናል። ብዙ ጊዜ በመልሶ ማጥቃት እና በረጃጅም ኳሶች ነው የሚጫወቱት። እኛም እሱን ዘግተን በ4-5-1 ኳሱን ተቆጣጥረን ለመጫወት ነበር እቅዳችን። ተጫዋቾቼም ኳሱን በመቆጣጠር ላይ ነው ያተኮሩት። ወደ ጎል ብዙ አልሄድንም።
ከእረፍት በኃላ የተሻለ ተነጋግረንበት አጨዋወታችንም ወደ 4-4-2 ለውጠን ውጤቱን ይዘን ወጥተናል።

ቡድኑ በሁለተኛው ዙር ስላደረገው ለውጥ

በመጀመርያው ዙር ጫና በዝቶብን ነበር።
በአራት ቀን ልዩነት ነበር የምንጫወተው።
ባለፈው ዓመትም ወላይታ ድቻዎች እንዲህ ጨዋታ ተደራርቦባቸው ነው ላለመውረድ የተጫወቱት እና የውጭ ጨዋታዎች ስትጫወት ጫና ይበዛብሃል።
የጨዋታ መደራረብ ስላለ ቡድንህ በፈለግከው መንገድ ልታጫውት አትችልም። በሁለተኛው ዙር ደሞ ከኦኪኪ መምጣት በኃላ አጨዋወታችን ቀይረን ውጤታማም ሆነናል የቡድኑ መንፈስም ጥሩ ነው። በዚ አጋጣሚ ለመቐለ ህዝብ ማመስገን እፈልጋለው ወደዚ ከተማ በመጣን ቁጥር ጥሩ ነገር ነው የምናየው።

በጥሩ ብቃት ያለው ማማዱ ሲድቤ በተጠባባቂ ወንበር ስለመቀመጡ

ማማዱ ሲዲቤ ህመም ነበረበት። በዛ ላይ ፆም ላይ ነው ያለው። ኦኪኪ ደግሞ ፆሙን ፈቷል። በህመምም በድካምም ነው ሲዲቤን ያስቀመጥነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡