ሴቶች 1ኛ ዲቪዝዮን | ኤሌክትሪክ ጌዴኦ ዲላ ላይ ግማሽ ደርዘን ጎል በማስቆጠር ከግርጌው ተላቋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዝዮን 20ኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሐ ግብር ዛሬ በኤሌክትሪክ እና ጌዴኦ ዲላ መካከል ተከናውኖ ኤሌክትሪክ 6-0 አሸንፎ ላለመውረድ የሚያደርገውን ትግል ቀጥሏል።

08:00 ላይ በተጀመረው ጨዋታ የመጀመርያ አጋማሽ ተመጣጣኝ ፉክክር ቢስተዋልበትም ያገኟቸውን እድሎች በአግባቡ በመጠቀም ረገድ ስኬታማ የሆኑት ግን ኤሌክትሪኮች ነበሩ። በመሐል ሜዳ ተገድቦ የቆየው እንቅስቃሴ የመጀመርያውን ሙከራ ለማስመልከት 18 ደቂቃዎች አስጠብቋል። በግምት ከ20 ሜትር ርቀት ፀባኦት መሐመድ በቀጥታ መትታ ግብ ጠባቂዋ ገነት አንተነህ ወደ ውጪ ስታወጣው ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ከመሐል ሜዳ የተላከውን ሰንጣቂ ኳስ ረድኤት አሳሳኸኝ በጥሩ ሁኔታ ተከላካዮችን አምልጣ በመውጣት ግብ ጠባቂዋን ብታልፋትም ኳሱን ወደ ግብ መምታት ሳትችል ያመከነችው ኳስ ጌዴኦ ዲላዎችን መሪ ሊያደርጉ የተቃረቡ ነበሩ።

ከሁለቱ ሙከራዎች በኋላ የተሻለ ብልጫ የወሰዱት ኤሌክትሪኮች አጋጣሚዎችን በመፍጠር ጎሎችን ማስቆጠር ችለዋል። በ27ኛው ደቂቃ መሳይ ተመስገን ለመሐል ሜዳ ከቀረበ ቦታ በቀጥታ ወደ ግብ የላከችውን ቅጣት ምት ግብ ጠባቂዋ ምህረት ተሰማ ስትተፋው አጠገቧ የነበረችው ቅድስት ዓባይነህ ወደ ጎልነት ቀይራ ኤሌክትሪክን ቀዳሚ አድርጋለች።

በቀጣዮቹ ደቂቃዎች የጨዋታው እንቅስቃሴ ከቅብብል የዘለለ እንቅስቃሴ ሳያሳይ የዘለቀ ሲሆን የመጨረሻዎቹ የአጋማሹ ደቂቃዎች ኤሌክትሪኮች ስል ሆነው ታይተዋል። በዚህም 44ኛው ደቂቃ ላይ ከራሳቸው የግብ ክልል በረጅሙ የተጣለውን ኳስ ወርቀነሽ ሜልሜላ በአግባቡ ተጠቅማ ፍጥነቷን በመጨመር ከቀኝ የሳጥኑ ክፍል ምታ ሁለተኛውን ጎል አስቆጥራለች። ብዙም ሳይቆይ በጭማሪው ደቂቃ ላይ ደግሞ ከትበይን መስፍን ከመስመር የተሻገረውን ኳስ መሳይ ተመስገን ከግብ ጠባቂዋ ቀድማ በግንባሯ በመግጨት ሶስተኛውን አክላ የመጀመርያው አጋማሽ በኤሌክትሪክ 3-0 መሪነት ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጌዴኦ ዲላዎች ይበልጥ ተዳክመው ሲቀርቡ ኤሌክትሪኮች ደግሞ የዲላ ተከላካዮች ከጀርባቸው ትተውት የሚወጡትን ክፍተት በመጠቀም ተጨማሪ ሦስት ጎሎችን አስቆጥረዋል። በ57ኛው ደቂቃ ወርቅነሽ በፍጥነት ከቀኝ መስመር ገብታ ያመቻቸችውን ጥሩ እድል መሳይ ተመስገን መትታ ወደ ላይ ሲወጣባት በ61ኛው ደቂቃ ዓለምነሽ ገረመው ከርቀት አክርራ የመታችው ኳስ በግብ ጠባቂዋ ተጨርፎ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቷል። የተገኘው የማዕዘን ምት ተሻምቶ ሲመለስም ወርቅነሽ ሜልሜላ ከሳጥኑ የቀኝ ጠርዝ አቅራቢያ በቀጥታ መትታ አራተኛውን ጎል አስቆጥራለች።

በቀላሉ የጎል እድል መፍጠራቸውን የቀጠሉት ኤሌክትሪኮች ከተመሳሳይ ቦታ ተመሳሳይ ሁለት ጎሎችን አከታትለው አስቆጥረዋል። በ65ኛው ደቂቃ ዓለምነሽ ደካማ የነበረው የጌዴኦ የመከላከል አደረጃጀትን አምልጣ በመውጣት ከቀኝ መስመር በቀጥታ ወደ ጎል የላከችው ኳስ አምስተኛ ሆኖ ሲቆጠር በ72ኛው ደቂቃ የእለቱ ኮከብ ወርቅነሽ ሜልሜላ የግብ ጠባቂዋን መውጣት አይታ በጥሩ ሁኔታ የማሳረጊያውን፤ በግሏ ደግሞ ሐት-ትሪክ የሰራችበትን ግሩም ጎል አስቆጥራ ጨዋታው በኤሌክትሪክ 6-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ኤሌክትሪክ በድሉ ተጠቅሞ ከግርጌው በዝቅተኛ የጎል እዳ አንድ ደረጃ ከፍ ቢልም ከመውረድ ለመትረፍ ቀሪዎቹን ሁለት ጨዋታዎች አሸንፎ በአራት ነጥብ ከፍ ብለው የሚገኙትን ቡድኖች ውጤት ለመጠባበቅ ይገደዳል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡