” የትም ቦታ ላይ ብጫወት ቡድኑ እኔ በማደርገው እንቅስቃሴ ውጤታማ ሲሆን ማየት ያስደስተኛል ” ሚኪያስ ግርማ

በዘንድሮው የውድድር ዓመት በፕሪምየር ሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ በድሬዳዋ ከተማ መለያ ብቅ ብሏል። ከቅዱስ ጊዮርጊስ የታዳጊ ቡድን የተገኘው ሚኪያስ ግርማ በ2009 በውሰት ወደ አራዳ ክፍለ ከተማ አምርቶ ከግማሽ ዓመት ቆይታ በኋላ ወደ ባህር ዳር ከተማ በማቅናት ለ18 ወራት ቆይታን አድርጓል። አምና ወደ ታይላንድ አምርቶ በሙከራ አሳልፎ ከመጣ በኋላ ዘንድሮ በድሬዳዋ ከተማ እየተጫወተ ይገኛል። ከአጥቂነት አንስቶ በተከላካይነት እንዲሁም ዘንድሮ ደግሞ በአማካይ ስፍራ በድሬዳዋ መልካም ጊዜን እያሳለፈ የሚገኘው ሚኪያስ ግርማ ስለ እግር ኳስ ህይወቱ እና ስለ ቀጣይ እቅዶቹ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

ትውልድ እና የእግር ኳስ አጀማመርህ?

የተወለድኩት አዲስ አበባ ጃንሜዳ በተለምዶ አጠራር ኮሪያ በሚባል ሰፈር ነው። ትውልዴም ሆነ እድገቴ፤ እግር ኳስንም መጫወት የጀመርኩት በዛው ጃንሜዳ በሰፈር ውስጥ ነበር፡፡ ፈለቀ በሚባል አሰልጣኝ የሚመራ ቴምርላንድ የተባለ ቡድን ውስጥ ነው የፕሮጀክት ህይወቴን የጀመርኩት። ከዛ በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስ በየዓመቱ በሚያዘጋጀው የአቶ ይድነቃቸው ተሰማ ውድድር ላይ ስጫወት ታይቼ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢ ቡድን በ2003 በበላቸው ኪዳኔ በሚሰለጥነው ቡድን ውስጥ መካተት ቻልኩ። በዚሁ ቡድን ውስጥ ለሶስት አመት ከቆየሁኝ በኋላ በመጨረሻው ዓመቴ የዋናው ቡድን አሰልጣኝ ኩፕማን ክረምት ላይ ከቡድኑ ጋር ለዝግጅት ይዞኝ ሄደ። በልምምድ ላይ ጥሩ ነበርኩኝ ከዛ በቢጫ ተሴራ ለዋናው ቡድን እንድንጫወት ፈልጎ ነበር። ነገር ግን ኩፕማን በቡድኑ ውስጥ ሊቆይ ስላልቻለ ማርት ኑይ መጣ። ከዛ በኋላ ከተስፋ ቡድን እየተመላለስን ለዋናው ቡድን እንድንጫወት ተደረገ። 2008 የተስፋ ቡድን ውድድሮች ላይ ባንክ ቻምፒዮን ሲሆን እኔ ደግሞ የውድድሩ ኮከብ ተጫዋች ሆንኩ፡፡

በቅዱስ ጊዮርጊስ ለዋናው ቡድን የመጫወት ፍላጎቱ ቢኖርህም ሳይሆን ቀረ። ወደ ሌላ ክለብም አመራህ። እንዴት ነበር ያ ጊዜ ?

ቅዱስ ጊዮርጊስ በውሰት ለአራዳ ክፍለ ከተማ በዛው ዓመት ሰጠኝ። ለስድስት ወር ብቻ ነው ለአራዳ የተጫወትኩት። በዛው ዓመት ውሰቴን እንዲቀይሩልኝ ጠይቄያቸው የባህር ዳር አሰልጣኝ ጌታሁን ገብረጊዮርጊስ ጠርቶኝ አመራሁ። ግማሽ ዓመቷን እዛው ጨርሼ ልወጣ ስል ውል አራዝመህ እኛ ጋር ሁን አሉኝ። ውሌንም አራዝሜ ባሳለፍነው ዓመት በቡድኑ ውስጥ ቆየሁኝ። ከቡድን ጓደኞቼ ጋርም በመሆን ባህር ዳርን ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንዲገባ አደረግን።

የባህርዳር ቆይታህ እንዴት ነበር ?

ባህር ዳር በህይወቴ አዲስ ምዕራፍ የጀመርኩበት ክለብ ነው ብዬ የማስበው። በደጋፊው ለመወደድ ብዙ አልፈጀብኝም። አማካይ ላይ ነበር የምጫወተው። በተለይ ግማሽ ላይ በቋሚነት ሙሉ 15 ጨዋታዎችን የመጫወት ጥሩ ጊዜ ነበር ያሳለፍኩት። ከዛ በኋላም አሰልጣኝ ጳውሎስ ከአማካይ ቦታ ላይ ቀይሮኝ እንድጫወት ተደርጌ የቀኝ ተከላካይ ሆንኩ። ከጳውሎስ ጋርም ተግባብቼ ለመስራት አልከበደኝም፤ ጥሩ ጊዜንም አሳልፈን ቡድኑን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ከጓደኞቼ ጋር በመሆን አስገብተናል። እስከ አሁንም በባህር ዳር ያሳለፍኳቸው ጊዜያት በውስጤ አሉ። አሁንም ድረስ ያለሁበት ያህል መስሎ ነው የሚሰማኝ። በጣም ብዙ ደጋፊ ያለው ክለብ ነው። በዛ ላይ ሁላችንም ወጣት ተጫዋቾች ነበርን። ከኔ ጋር እስከ አሁን ድረስ ቤተሰብ የሆኑ ደጋፊዎችንም አፍርቼበታለሁ። በአጠቃላይ ደስተኛ ሆኜ ነበር በባህር ዳር ያሳለፍኩት፡፡

በባህርዳር ቆይታህ መልካም የሚባል እንቅስቃሴን ታደርግ ነበር። የመጨረሻው ዓመት ላይ ግን በርካታ ውዝግቦች ተነስተውብህ ነበር …

ጥሩ ጥያቄ ነው። ክለቡን ለቅቄ ልወጣ የቻልኩበት ምክንያትን ልንገርህ። ኤጀንት ነበረኝ፤ ባህርዳር ከመፈረሜ በፊት ካስፈረሙኝ ሰዎች ጋር የውጪ ፕሮሰስ መጀመሬን በቃል ተነጋግሬ ነበር። እነሱም ምንም ችግር የለብንም እድሉ ከመጣልህ ውጪ ሄደህ እንድትጫወት ነው የምንፈልገው አሉኝ። ለኔ ይሄ እድል ሲመጣልኝ ደግሞ ባህር ዳር ወደ ፕሪምየር ሊግ ሊገባ ጫፍ የደረሰበት ጊዜ ነበር። እኔ ወደ ታይላንድ ከመሄዴ ይልቅ እዛው ክለቤ ውስጥ ሆኜ እንድጫወት ሁሉም ይፈልግ ነበር። ካለኝ ጥቅም አንፃር ይሄን እኔ በመልካም ጎኑ ነው የማየው። ያኔ ግን ምን ተፈጠረ? ወደ መጨረሻው አካባቢ ከለገጣፎ ጋር እስክንጫወት ድረስ አራት ቢጫ ነበረብኝ። ያን ጨዋታ ቢጫ ተመልክቼ አምስት ሞላኝ። ስለዚህ አንድ ጨዋታ ያልፋል፤ ካስታወስክ ያ ጨዋታ ደግሞ በዝናብ ምክንያት ተቋርጦ በማግስቱ ነበር የተጠናቀቀው። ከዛ በኃላ ወደ ታይላንድ ለመሄድ ሁሉም ነገር አልቆልኝ ስለነበረ እኔም ራሴን አዘጋጀሁ። ዓመቱ መጀመሪያ ላይ ሁለተኛ ጨዋታ ከኮምቦልቻ ጋር ስንጫወት የመጀመሪያ የውጪ ዕድል መጥቶልኝ ነበር። የክለቡ አመራሮች ” ይህን ጉዳይ ትንሽ አርዝመው። ባህር ዳር ወደ ፕሪምየር ሊግ እንዲገባ አቅደናል። ” ብለውኝ ነበር። በዚህም ምክንያት መጀመሪያ መቶሎኝ የነበረው እድል ሊቀር ቻለ። ሁለተኛው ዕድል ላይ ግን ከአሰልጣኝ ጳውሎስ ጋር ቁጭ ብለን ስናወራ ምንም ችግር እንደማያመጣ ለአንድ ሳምንት ብቻ ቆይቼ እንደምመጣ ተነጋገርን። በተጨማሪነት ደግሞ በለገጣፎ ጨዋታም ቢጫ ካርድ ስለ ተመለከትኩ ብዬ ቢሳካም ባይሳካም ስለምመጣ ተነጋግረን ነበር የሄድነው። ሄጄ ስመጣ ግን አሰልጣኝ ጳውሎስ ከእኔ ጋር ምንም እንዳላወራ እና ምንም እንዳላማከርኩት አድርጎ አሸፋፍኖ አለፈ። በሱ እና በክለቡም ዘንድ ያለመግባባት ተፈጠረ። ከዛ ሙሉ በሙሉ እኔ ጋር ሆነ ስህተቱ። ክለቡም እውቅና አልሰጠነውም በሚል፤ በዛም የተነሳ እስከ አሁን ብዙ ደጋፊዎች ስልኬ ላይ ይደውሉልኛል። በፅሁፍም ያደርሱኛል። አንዳንድ የማልጠብቃቸው ነገሮች ገጥመውኛል ያው እግር ኳስ ስለሆነ የሚያጋጥሙ ክስተቶች ስለሚሆኑ እቀበለዋለሁ፡፡ ይህም ነገር ተፈጥሮ ነው የምወደውን ክለብ እና ደጋፊ የለፋበትንም ክለብ በደንብ ማገልገል ሳልችል እየቆጨኝ ነበር ወደ ሌላ ክለብ የሄድኩት። ድሬዳዋ ስገባም አስቀድሜ ባህር ዳር የተፈጠረው ነገር እንዳይይደገም በሚል የውጪ ሙከራ ካለኝ ለመሄድ ቅድመ ሁኔታዎች ላይ ተነጋግሬ ነው የመጣሁት። ባህር ዳር መቆየት ፈልጌ ይህን ማድረግ ስላልቻሉ ነበር ልለያይ የቻልኩት እንጂ እነሱም የማቆየት ፍላጎት ነበራቸው። እኔም የመቆየት ፍላጎት ነበረኝ። በዛ መሐል ነው ይሄ ነገር የተፈጠረው ፡፡

የታይላንድ ቆይታህ ምን ይመስላል። ያልተሳካልህስ በምን ምክንያት ይሆን?

የታይላንድ ሙከራ ከሞላ ጎደል ጥሩ ነበር። የመጀመሪያ ሙከራዬም ስለሆነ ትምህርት የወሰድኩበት ነበር። ዴቪድ በሻህ እና አብሮት የሚሰራው ሰው ባመቻቹልኝ እድል ሄጄ ለ12 ቀን ቆይቻለሁ። ጥሩ ጊዜን ነበር ያሳለፍኩት። እኔ ውጪ ወጥቶ የመሞከሩ ግንዛቤው አልነበረኝም። እዚህ ጥሩ ነገር ስላሳለፍኩኝ እዛም በተመሳሳይ አሳልፋለው ብዬ ነበር። ሆኖም ከጠበኩት በላይ ነበር እዛ ያገኘሁት። በጣም ፕሮፌሽናል ናቸው። ታይላንድ ብለህ ለሰው ስታወራ ሊጉ ትንሽ ቢመስልም ብዙ ነገር ተሟልቶላቸው በጣም በትልቅ ደረጃ ነው የሚጫወቱት። በቡድኑም ውስጥ ትልልቅ ተጫዋቾች ያሉት ሊግ ነው። እኔም ልምድ መለዋወጥ ጥሩ ጊዜን ነበር ያሳለፍኩት። ከጀርመናዊው የቡድኑ አሰልጣኝ ጋር ስለ ኢትዮጵያ እግር ኳስ ግንዛቤው ስላልነበረው አውርተናል። ባለኝ ነገር ላይ አውርተን ተነጋግረን ነበረ የመጣሁት። ትንሽ ከወኪሎቼ ጋር ያልተስማማናቸው ነገሮች ነበሩ። አብረን መስራት ስላልቻልን ተለያየን። አሁን ግን አዲስ የውጪ ሀገር ዜግነት ካለው ወኪል ጋር እየተነጋገርኩኝ ነው። ከስምምነት ደርሰናል፤ ብዙ ዕድሎችንም እሱ ያመጣልኛል ብዬ አስባለሁ፡፡

ዘንድሮ የአንድ ዓመት ቆይታ ለማድረግ ድሬዳዋን ተቀላቅለሀል። እንዴት እያሳለፍክ ነው ? ከምትታወቅበት ሚናህም ለውጥ አድርገሀል..

ወደዚህ የመጣሁት ከአሰልጣኝ ዮሀንስ ጋር ተነጋግሬ ነው። ለውጪ ሙከራዎች ስለሚኖሩኝ የሱ አሰለጣጠንም ለዚህ ምቹ ስለሆነ አልፎም የውጪ ዕድል ካለኝ ልሄድ እንደምችል ተስማምተን ነው ወደ ድሬዳዋ የመጣሁት። ከመጣሁም በኃላ በሱ የልምምድ አሰጣጥ ተጠቃሚ ሆኛለሁ። አሁን ያለው አሰልጣኝም (ስምዖን) ወጣት አሰልጣኝ ነው፤ ተጫውቶም አሳልፏል። በሱም ስር ሆኜ በጣም ደስተኛ ሆኜ ነው እየሰራሁ ያለሁት። በቡድኑ ውስጥ የምንተያየው እንደ ወንድም ነው።

አምና ባህር ዳር ቀኝ ተከላካይ ነበርኩ። አሁን ግን ስምዖን ሙሉ ለሙሉ አማካይ አድርጎኝ እየተጫወትኩ ነው። በዚህም ደስተኛ ነኝ። በሊጉ የመጀመሪያ ዓመት እያሳለፍኩ እንደመሆኑ ፈታኝ ነገሮች ነበሩ፤ እነሱን እያለፍኩኝ ነው ያለሁት። በእርግጥ ከክለብ ባለፈ ብዙ ሀሳቦችን አስቤ ነበር፡፡ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን መጫወት እፈልግ ስለነበር ብጫወት ጥሩ ነበር፤ ያ አልሆነም። ለብሔራዊ ቡድን መመረጥ የሙከራ ዕድልህ እንዲሰፋ ያደርጋል። በቀጣይ ግን ጥሩ ነገር እንዲኖረኝ አሰልጣኝ ስምዖንም እየረዳኝ ነው።

ብዙ ሚናዎች ተሰጥተውህ መጫወት ትችላለህ። ላንተ ምቹ የጨዋታ ሚና ግን የቱ ነው?

ከልጅነቴ ጀምሮ ስለሚከታተለኝ ብዙ ቦታዎች ላይ መጫወት የቻልኩት በአሰልጣኝ በላቸው ኪዳኔ አማካኝነት ነው። (አሁን ካናዳ ሀገር ነው ያለው) በቢ ቡድን ደረጃ ስንጫወት ማንም ሰው ቦታ አልነበረውም። ሁሉም ሰው እየተቀያየረ ነው የሚጫወተው። አቡበከር ሳኒ ለምሳሌ ተከላካይ ላይ ነበረ በዛ ሰዓት የሚጫወተው። ይህን ልምድ ያመጣውት ከሱ (አሰልጣኝ በላቸው) ነው፤ በዚህ አጋጣሚ እሱን ማመስገን እፈልጋለሁ። ኳስን ስጀምር ተከላካይ ላይ በሁሉም ቦታዎች ላይ ተጫውቻለሁ፤ አማካይ ላይ በማጥቃት እና መከላከሉ ላይም እጫወታለሁ፡፡ ባህር ዳር ለምሳሌ በሄድኩበት ዓመት በአሰልጣኝ ጌታሁን ስር ሶስት ጨዋታ በአጥቂነት መጫወት ችያለሁ፡፡ አሁን ድሬዳዋ የምጫወተው አማካይ ላይ ነው፡፡ ወደ ኃላም ተስቤ እጫወታለሁ፤ ቡድኔ በሰጠኝ በማንኛውም ቦታ ማገልገሌ ያስደስተኛል፡፡ እኔ የትም ቦታ ልጫወት ቡድኑ እኔ በማድረገው እንቅስቃሴ ውጤታማ ማድረግ ያስደስተኛል። አበላልጥ ከተባልኩኝ ግን የተከላካይ አማካይ ሆኜ (አሁን ባለሁበት ቦታ ላይ) እየተጫወትኩ ብቀጥል ደስ ይለኛል። ምክንያቱም ይህ ቦታ ይመቸኛል፣ ጓደኞቼን ለማነቃቃት ይረዳኛል፣ የቡድኑን ሚዛን ለመጠበቅ ስልም እመርጠዋለሁ። እኔ ኃላፊነት በጣም እወዳለሁ። ማበላለጥ አለብህ ስላልከኝ ነው እንጂ በማንኛውም ቦታ መጫወት እችላለሁ።

ማን ነበር ላንተ አርዓያ የሆነህ? አሁን እየተጫወቱ ካሉትስ ማን ይመችሀል?

በነገራችን ላይ ፋሲል ተካልኝ የሰፈሬ ልጅ ነው። እሱን መነሻ አድርጌ ነው የተነሳሁት። አሁን ሶስት ቁጥርን አድርጌ የምጫወተው በሱ ምክንያት ነው። እሱ ቤት ውስጥም ስላደኩኝ ሲጫወት የሚያሳይ ቪድዮውን እመለከት ነበር። አልሸነፍ ባይነቱ፣ ለቡድኑ ያለው ፍቅር እና ለማሸነፍ ያለው ፍላጎት ስላየሁ ይህን ነገር ከሱ ወስጃለሁ። ምንም እንኳን ልጅ ስለነበርኩ ስታዲየም ገብቼ እሱን መመልከት ባልችልም እሱ የደረሰበት ደረጃ መድረስ እፈልግ ነበር። በስራ ጉዳይ ባይመቸውም አሁንም ከጎኔ ነው አልተለየኝም፤ እንገናኛለን። አሁን ላይ ደግሞ ኤልያስ ማሞን ነው። አሁን አብሮኝ ነው ድሬዳዋ የሚጫወተው። ለኔ ሞዴሌ ከሆነ ተጫዋች ጋር አብረን መጫወት በመቻላችን በጣም ደስ ብሎኛል። ከልብ ነው የምወደው። ሀዋሳ ከተማ ያለው ታፈሰ ሰለሞንንም አደንቀዋለሁ። የአክስቴ ልጅ ነው። ነገር ግን ዘመዴ ስለሆነ ሳይሆን በጣም ጎበዝ ተጫዋች ስለሆነ አደንቀዋለሁ። ደጉ ደበበንም በጣም ነው የማደንቀው። ጊዮርጊስ ባደግኩበት ዓመት አብረን ተጫውተናል። የመሪነት ችሎታ ያለው፣ አልሸነፍ ባይነቱ ልዩ ያደርገዋል። ከነዚህ ሁሉ ምረጥ ካልከኝም ደጉ ደበበን እመርጣለሁ።

በወጣትነት ዘመንህ ወደ ትዳሩ ገብተሀል። ትዳር እና እግር ኳስ እንዴት እየሄደልህ ነው? ጠቀሜታውስ?

ከምነግርህ በላይ ብዙ ጥቅሞች አሉት፡፡ ስትደሰት በልክ እንዲሆን፤ ስትከፋም እሷ ከጎንህ እንዳለች ስታስብ ጠንክረህ ስራህን ትሰራለህ። ለዚህም ደግሞ ከአጠገብህ ጠንካራ ሰው መኖር አለበት። የሷ ከጎኔ መሆን በጣም ጠቅሞኛል። ለሌሎች ተጫዋቾች የምመክረው ትዳር ጥሩ ነው ያረጋጋል ወደ ሌላ ቦታ እንዳይሄዱ ያደርጋቸዋል፡፡ ከአንድ ሰው ጋር በፍቅር መኖሩ ይጠቅማል እንጂ የሚጎዳው ነገር የለም። አሁን ብዙ የምንማርባቸው ተጫዋቾች የምናየውን ያህል በሌላ በኩል ደግሞ የሚሰሙ ያልተገቡ ነገሮች አሉ። ከምትወደው ጋር በጊዜ መኖር መጀመር በጣም ጠቃሚ ነው። እኔም የጥቅሙ ተቋዳሽ ነኝ፡፡

በመጨረሻ…

በቅድሚያ ከዚህ በኋላ በአንድ ክለብ ውስጥ የእግር ኳስ ህይወቴን ማጠናቀቅ ፈልጋለሁ። አንድ ዓመት እና ሁለት ዓመት ብቻ ፈርሞ መጫወትን አልፈልግም። ረጅም ኮንትራት ተሰጥቶኝ በአንድ መለያ ብቻ የእግር ኳስ ጉዞዬን መጨረስን እሻለሁ። ሲቀጥል በብሔራዊ ቡድን መጫወት ፈልጋለሁ። ይሄ እኔን ያጓጓኛል። አንዳንዴ ጥሩ ሆኜ ሳለው መመረጥ አለብኝ ብዬ በር ዘግቼ የማለቅስበት ወቅት አለ። ተጫዋች ስለሆንኩ ይሄን በራሴ ማድረግ አልችልም። የሚመርጠህ ሌላ ሰው ነው። እኔ ከመስራት ከመልፋት ውጪ ምንም ላመጣ አልችልም። አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ በጣም የምወደው ስብዕና ያለው አሰልጣኝ ነው። በሱ መሰልጠን ፈልጋለሁ። በቃ ለሱ ተመቻችቼ እየሰራሁ ራሴን አበቃለሁ። ቤተሰቦቼ ‘መቼ ነው ለብሔራዊ ቡድን የምትጫወተው?’ ብለው ሲጠይቁኝ ‘ጠብቁኝ… አንድ ቀን’ እላቸዋለሁ። ጠንክሬም ሰርቼ አሳካዋለሁ።

እንደሌሎቹ ተጫዋቾች ሁሉ ተፈትኜ ነው አሁን ያለውበት ቦታ ላይ የደረስኩት። ለኔ እዚህ ቦታ እንድደርስ ደግሞ የኪዳነ ምህረት ረዳትነት ስፍር ቁጥር የለውም፤ በጣም ረድታኛለች። ላመሰግናት እፈልጋለሁ። እናቴ ዘውድነሽ ማሙዬ፤ ወንድሞቼ እህቴ በጣም ረድተውኛል። እነ ፋሲል ተካልኝ እንዳሉ ሆነው ከምንም በላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት ያሰለፍኩት ብዙ ነገሮች አሉ። በዚህ ደረጃ አብሬያቸው ሆኜ በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት ካሉ ትልልቅ ተጫዋች ጋር ብዙ ልምምዶችን አብሬያቸው ሰርቻለሁ። በወዳጅነትም ሆነ በልምምድ አብሬያቸው ተጫውቻለሁ። እነሱ ለኔ ብዙ ትሞህርትን ሰጥተውኛል። ያ ስሜት አሁንም ድረስ ውስጤ አለ። ስለ ጊዮርጊስ ሲያወሩልህ ስላለመሸነፍ ሲነግሩህ መቼ ነው እኔም ደርሼ የምጫወተው እያልኩ ቁጭት ይፈጥርብኝ ነበር። እና ያ አልሆነም። አንድ ቀን ተመልሼ የልጅነት ቤቴ እንደምጫወት አምናለሁ። እነ አቶ ሰለሞን፣ የጊዮርጊስ ስራ አስፈፃሚዎች፣ እነ አቶ አብነት በጣም ላመሰግናቸው እወዳለሁ። በግል እየጠሩ እንደ ተጫዋች ሳይሆን እንደ ልጃቸው ነበር የሚያዩኝ አመሰግናቸዋለሁ። አንድ ቀን ተመልሼ ጊዮርጊስን እንደማገለግል ተስፋ አደርጋለሁ፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡