ዲዲዬ ጎሜስ ከሆሮያ ጋር የጊኒ ሊግ 1 ዋንጫ አሸናፊ መሆናቸውን አረጋገጡ

በቀድሞው የኢትዮጵያ ቡና አሰልጣኝ የሚመራው የጊኒው ክለብ ሆሮያ ዋኪርያን 2-0 በማሸነፍ ለ17ኛ ጊዜ የሃገሩ ቻምፒዮን መሆኑን አምስት ጨዋታ እየቀረው አረጋግጧል፡፡

የዲዲዬ ጎሜስ ቡድን በሃገሪቱ ሻምፒዮና ስምንት ጨዋታዎችን በተከታታይ በማሸነፍና 24 ነጥቦችን በተከታታይ በመሰብሰብ ከ12 ጨዋታዎች 31 ነጥብ በመያዝ ተከታዩ ክለብ ሶንቶባን በ15 ነጥቦች በልጦ የጊኒ ሻምፒዮን ሆኗል፡፡ በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ እስከግማሽ ፍጻሜ ተጉዞ በሞሮኮው ካዛብላንካ ከውድድር የወጣው ሆሮያ ከሌሎቹ ክለቦች አንፃር አንድ ቀሪ ጨዋታ ያለው ሲሆን በአጠቃላይ አምስት ጨዋታዎች ይቀሩታል፡፡
የጊኒ ሻምፒዮን መሆናቸውን ተከትሎ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ ያደረጉት ፈረንሳያዊው አሰልጣኝ ዲዲዬ በውጤቱ በጣም መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡

«ከኢትዮጵያ ቡና ስሰናበት አዝኜ ነበር። ነገር ግን ከሆሮያ ጋር አስደናቂ ጉዞን በማድረግ ገና 5 ጨዋታ እየቀረን ቻምፒዮን መሆናችንን አረጋግጠናል። ይህ ደግሞ በጣም አስደሳች ነገር ነው፡፡

« ኢትዮጵያን እወዳታለው፤ ከቡና ጋር ያሳለፍኩት ጣፋጭ ጊዜ ሁሌም ቢሆን በልቤ ይኖራል። » ያሉት የቀድሞው የቡና አለቃ በመጪው የፈረንጆች ወር ተጫዋች ለመመልመል ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡና ቢያንስ ሁለት ተጫዋቾችን ከኢትዮጵያ የማስፈረም ሃሳብ እንዳላቸው ነግረውናል፡፡ ተጫዋቾቹ ማንና ማን እንደሆኑ የተጠየቁት አሰልጣኙ ለጊዜው የተጫዋቾችን ስም ከመግለጽ ግን ተቆጥበዋል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡