በ5ኛው የኮፓ ኮካ ኮላ የታዳጊዎች እግርኳስ ውድድር ዙርያ መግለጫ ተሰጠ

ለአምስተኛ ጊዜ የሚካሄደው ዓመታዊዉ የኮፓ ኮካ ኮላ እግርኳስ ውድድር ይፋዊ የመክፈቻ መርሐ ግብር በዛሬው እለት የኮካ ኮላ ኩባንያ ፣ ኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ አ.ማ. እንዲሁም የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ኃላፊዎች በተገኙበት በካፒታል ሆቴልና ስፓ ተካሂዷል፡፡

በመግለጫውም የዘንድሮው ውድድር ለሚቀጥሉት ሦስት ወራት በመላው ሀገሪቱ 2,500 የወንድና ሴት ቡድኖችን እንደሚያሳትፍ የተገለፀ ሲሆን እድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ከ45,000 በላይ ታዳጊ ወጣቶች መካከል ውድድሩ ይካሄዳል፡፡ ከዚህ ውስጥ 500 ትምህርት ቤቶች በሪሳይክሊንግ ፕሮግራም ላይ ተሳትፈው ፣ የተለያዩ አሮጌ የፕላስቲክ ጠርሙሶች በመሰብሰብ ለትምህርት ቤታቸው የእግርኳስ ሜዳ የማሸነፍ እድል ያገኛሉም ተብሏል፡፡

አቶ ዓለም ዓለማየሁ የኮካ ኮላ ፍራንቻይዝ ስራ አስኪያጅ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ላይ የውድድሩን ጠቀሜታ አውስተው የዘንድሮው ውድድር ከእግርኳስ ውድድሩ ጎን ለጎን በትምህርት ቤት ውስጥ የሚገኙ ታዳጊዎችን በቆሻሻ የተበከለ አካባቢያቸው በሪሳይክሊንግ እንዴት ማፅዳት እንደሚችሉ ለማስተማር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፤ በዚህም የፕላስቲክ ጠርሙሶችንና ቆርኪዎችን ለሰበሰቡ ትምህርት ቤቶች ኮካ ኮላ እውቅና ሰጥቶ እንደሚሸልምም ገልፀዋል። በዚህም አሸናፊ የሚሆነው ትምህርት ቤት የእግርኳስ ሜዳ የሚያሸንፍ ሲሆን ሁለተኛና ሦስተኛ የሚወጡት ትምህርት ቤቶች መጽሐፍት ፤ የትምህርት ቁሳቁሶች እና መሳሪያዎች በቅደም ተከተላቸው እንደሚያሸንፉ ገልፀዋል፡፡

በመቀጠል ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ምክትል ፀሐፊ የሆኑት አቶ ሰለሞን ገ/ሥላሴ እንደተናገሩት የዚህ አይነት ፕሮግራሞች መካሄድ የሀገራችንን እግርኳስ ከማዳበር በዘለለ ተዳጊዎችን በማነሳሳት ፣ ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ ለመርዳትና ወደፊት የተሻለ ተጫዋቾች ሆነው እንዲገኙ የሚያደርጉ ስለመሆናቸው ተናግረዋል፡፡

በመቀጠልም ይሰብስቡ ፤ ያሸንፉ በማለት ዘንድሮ ኮካ ኮላ ከውድድሩ ጎን ለጎን ስለሚካሄደው የማኅበራዊ አገልግሎትን በተመለከተ ገለጻ በወ/ሮ ምህረት ተክለማርያም ቀርቧል፡፡

በመጨረሻም ከመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ተሰጥተዋል። ከተነሱት ጥያቄዎች መካከል ስለውድድሩ የሚካሄድበት ወቅት የተጠቀየቁት አቶ ሰለሞን ገ/ስላሴ ሲመልሱ ውድድሩ በሶስት እርከኖች ተከፋፍሎ የሚካሄድ ሲሆን በተማሪዎች መካከል የሚደረገው የመጀመሪያ የውድድር እርከን ከሰኔ 15-30፤ ከሐምሌ 10-20 ድረስ ደግሞ በክልል ደረጃ ውድድሩ ሲቀጥል በስተመጨረሻም ከሐምሌ 20-30 ድረስ ሀገር አቀፉ የማጠቃለያ ውድድር የሚካሄድ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

error: