ሴቶች አንደኛ ዲቪዝዮን | በዛሬ ጨዋታዎች ድሬዳዋ እና መከላከያ አሸንፈዋል

የ2011 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ (አንደኛ ዲቪዝዮን) የመጨረሻ ሳምንት የመጀመርያ ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም በዝናብ ታጅበው ሲካሄዱ መከላከያ እና ድሬደዋ የውድድር ዓመቱን በድል አጠናቀዋል።

09:00 ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከ ድሬዳዋ ከተማ ጋር ያገናኘው ጨዋታ በእንግዳው ቡድን 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ጨዋታው ጎል መስተናገድ የጀመረው ገና በጨዋታው ጅማሬ ነበር፤ አይዳ ዑስማን ከመሐል ሜዳ ግራ መስመር አንስታ ተጫዋቾች በማለፍ ገፍታ በመሄድ ነፃ አቋቋም ለምትገኘው ስራ ይርዳው አቀብላት ስራ ኳሱን ደገፍ በማድረግ ድሬዎችን ቀዳሚ ማድረግ ችላለች።

በጨዋታው ጅማሬ በፍጥነት ጎል መቆጠሩ የጨዋታውን እንቅስቃሴንም ያግለዋል ተብሎ ቢጠበቅም ጨዋታው ደብዘዝ ብሎ ቀጥሏል። ድሬዎች አይዳ ዑስማን በምትፈጥረው የግል እንቅስቃሴ ካልሆነ በቀር የተለየ ነገር መፍጠር ባይችሉም በአንድ አጋጣሚ የቅዱስ ጊዮርጊስ ግብ ጠባቂ ብዙዓየሁ አየለ ከግብ ክልሏ በመውጣት ኳሱን አርቃለው ብላ የሰራችውን ስህተት ተከትሎ ሲና መሐመድ በቀጥታ ወደጎል የመታችው ኳስ ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣበት ለድሬዎች ተጠቃሽ ሙከራ ነበር። ከ20ኛው ደቂቃ በኃላ ሙሉ ለሙሉ ጊዮርጊሶች ኳሱን ተቆጣጥረው በመጫወት በርከት ያሉ የጎል ዕድሎችን መፍጠር ሲችሉ ዓይናለም ዓለማየሁ በተለያዩ አጋጣሚዎች የጎል ዕድል አግኝታ ሳትጠቀም የቀረች ቢሆንም በተለይ አምስት ከሃምሳ ውስጥ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝታ ያመከነችው ኳስ የሚያስቆጭ ሆኖ አልፏል።

ከዕረፍት መልስ የመሐል ሜዳ ብልጫ የተወሰደባቸው ድሬዎች የተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ ማሻሻያ ቢያደርጉም በተመሳሳይ እንደ መጀመርያው አጋማሽ ሁሉ ከዕረፍት መልስ በፈረሰኞቹ ብልጫ ተወስዶባቸዋል። ድሬዎች አልፎ አልፎ በመልሶ ማጥቃት በረጃጅም ኳሶች ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የግብ ክልል በመድረስ በአይዳ ዑስማን አማካኝነት አደጋ ቢፈጥሩም በአጥቂዋ የአጨራረስ ድክመት የተነሳ ተጨማሪ ጎል ማስቆጠር አልቻሉም። ለዚህም ማሳያ 68ኛው ደቂቃ ላይ አንድ ተከላካይ ቀንሳ ሳትጠቀምበት የቀረችው መልካም የሚባል የጎል አጋጣሚ የሚያስቆጭ ነው። ቅዱስ ጊዮርጊስ በተሻለ በመንቀሳቀስ ቀሪ ደቂቃዎችን ቢጫወቱም አስቀድመው ከዕረፍት በፊት ያገኙትን ግልፅ የጎል አጋጣሚ አለመጠቀማቸው ዋጋ አስከፍሏቸው ጨዋታው በእንግዶቹ በመጀመርያው የጨዋታ ደቂቃ ላይ ባስቆጠሩት ብቸኛ አንድ ጎል አሸንፈው የውድድር ዓመቱን በድል አጠናቀዋል።

11:00 የቀጠለውና መከላከያ ከጊዲዮ ዲላ ያደረጉት ጨዋታ አዝናኝ እና ድራማዊ በሆነ ክስተት ታጅቦ በመከላከያ 4-3 አሸናፊነት ተጠናቋል። የጨዋታውን መጀመር የዕለቱ ዳኛ ባሰሙ በአንድ ደቂቃ ውስጥ ነበር እንግዶቹ ጌዲዮ ዲላዎች የመጀመርያ ጎላቸውን በጥሩ ሁኔታ በረድኤት አስረሳኸኝ አማካኝነት ያስቆጠሩት። ጨዋታው ነፃ የነበረ እና በሁለቱም በኩል ወደ ፊት በመጫወት የጎል እድል ለመፍጠር የሚደረግ ጥረት ተጋግሎ የቀጠለ መሆኑ ተመልካቹን በጨዋታው እንዲዝናና አድርጎታል። መከላካያዎች በመዲና ዐወል እና በሔለን እሸቱ አማካኝነት ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ቢያደርጉም እንግዶቹ ጌዲዮዎች በፈጣን አጥቂዎቻቸው አማካኝነት በመልሶ ማጥቃት በግራ መስመር ረድኤት ይዛ የገባችውን ኳስ ከሳጥኑ መሀል ጠርዝ እራሷን ነፃ አድርጋ የተቀበለችውን ኳስ ትርሲት መገርሳ አክርራ በመምታት ግሩም ጎል አስቆጥራ የጌዲዮን ጎል ወደ ሁለት ከፍ አድርጋዋለች። ጎሉ ቢቆጠርባቸውም ኳሱን ተቆጣጥረው በመጫወት ጎል ፍለጋ በተደጋጋሚ ወደ ጌዲዮ የግብ ክልል የተመላለሱት መከላከያዎች ያደረጉት ጥረት ተሳክቶላቸው ብሩክቲ አየለ በቀኝ መስመር በፍጥነት ገብታ ያሻገረችው ኳስ በጌዲዮ ተከላካዮች ተደርቦ ሲመለስ መዲና አወል አግኝታው በቀጥታ ወደ ጎል በመምታት የመከላከያን የመጀመርያ ጎል አስቆጥራለች። በስቴዲዮም ውስጥ የነበረውን የቅዝቃዜ አየር የሚያስረሳ ጨዋታ ሆኖ ሲቀጥል ከሚፈጠሩት የጎል አጋጣሚዎች አንፃር የሁለቱም ቡድኖች ግብጠባቂ ስራ በዝቶባቸው ነው የዋሉት።

በሁለተኛው አጋማሽ በተመሳሳይ ጥሩ ጨዋታ ከጎሎች ጋር ታጅቦ የቀጠለ ሲሆን በጨዋታው ውጤት ይዞ ለመውጣት በመስመር በኩል ተጭነው የተጫወቱት መከላከያዎች በርከት ያሉ የጎል አጋጣሚ መፍጠር ቢችሉም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። በዋናነት መዲና ዐወል በሁለት አጋጣሚ ከግብጠባቂዋ ጋር ተገናኝታ ከውሳኔ ችግር ያልተጠቀመችው ኳስ የሚያስቆጩ ነበሩ። በአንፃሩ ጌዲዮዎች በረዣዥም ኳሶች ለፈጣን አጥቂዎቻቸው በማድረስ የግብ እድሎችን መፍጠር ቢችሉም ረድዔት አስረሳኸኝ ሳትጠቀም ቀርታለች።

የጨዋታው ደቂቃ እየገፋ በሄደ ቁጥር ውጥረቱ አይሎ በቀኝ መስመር በመከላከያ በኩል ብሩክታዊት አየለ ያሻገረችውን ኳስ አምስት ከሃምሳ ውስጥ መዲና ዐወል አገባችው ሲባል ከእግሯ ስር ያለፈውን ሄለን እሸቱ አግኝታ 72ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠረችው ጎል መከላከያዎች ሁለት አቻ መሆን ችለዋል። አፀፋዊ ምላሽ ለመስጠት ብዙም ያልቆዩት የጌዲዮ ዲላ እንስቶች በፍጥነት በፈጠሩት የማጥቃት እንቅስቃሴ የመሰሉ አበራን ስህተት ተጠቅማ ከመከላከያ ግብጠባቂ ገነት ጋር ብቻዋን የተገናኘችው ረድየት አስረሳኸኝ ቺፕ አድርጋ ለጌዲዮ በ81ኛው ደቂቃ ላይ ግሩም ሦስተኛ ጎል አስቆጥራለች። ሆኖም ጌዲዮዎች ደስታቸውን ሳይጨርሱ በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ የተመልካቹን ቀልብ እየሳበ በቀሩት ደቂቃዎች አረጋሽ ካልካሳ እና ሄለን ሰይፉን ወደ ሜዳ በማስገባት ያደረጉት ስኬታማ ለውጥ መከላከያዎችን አግዟቸው በ83ኛው ደቂቃ በአንድ ሁለት ቅብብል የጌዲዮ የግብ ክልል በመግባት መዲና አወል ለራሷ ሁለተኛ ለቡድኗ አቻ ያደረገችበትን ሦስተኛ ጎል አስቆጥራለች።

ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቀቀ ሲባል 89ኛው ደቂቃ ላይ ሙሉ ለሙሉ አጥቅተው ሲጫወቱ የቆዮት መከላከያዎች በሄለን እሸቱ ድንቅ ጎል ጨዋታውን አሸንፈው የወጡበትን ጣፋጭ አራተኛ ጎል አስቆጥረዋል። መከላከያ ላስቆጠሩት ሦስተኛ እና አራተኛ ጎሎች መቆጠር ተቀይረው ወደ ሜዳ የገቡት ሄለን ሰይፉ እና አረጋሽ ካልሳ ሚና የጎላ ነበር።© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡