ድሬዳዋ ከተማ በወቅታዊ ጉዳይ ዙርያ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጠ

ድሬዳዋ ከተማ በሁለተኛው ዙር ጅማሮ ላይ ከክለቡ ያሰናበታቸው ኃይሌ እሸቱ፣ ዮናታን ከበደ እና ወሰኑ ማዜ “ከክለቡ ጋር ውል እያለን ያለአግባብ ተሰናብተናል።” በማለት ባቀረቡት ክስ መሠረት ፌዴሬሽኑ ያልተከፈላቸው ደሞዛቸውን በ10 ቀን ውስጥ እንዲከፍላቸው ውሳኔ ማስተላለፉ ይታወቃል።

ይህን ተከትሎ ክለቡ የድሬዳዋ አስተዳደር ፋይናንስና ኢኮኖሚ ቢሮ ኃላፊና የድሬደዋ ከተማ ስፖርት ክለብ ም/ፕሬዝዳንት አቶ ሱልጣን አልዪ፣ የድሬደዋ ክለብ ስራ አሰኪያጅ አቶ አንበስ አውግቸው እንዲሁም የቦርድ አባል የሆኑት አቶ ሙኒር በተገኙበት ዛሬ ረፋድ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጠ ሲሆን ፌዴሬሽኑ ውሳኔውን እንዲያጤን፤ አልያም ራሱን ከውድድሩ እንደሚያገል ተገልጿል።

” የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ክለባችን ከእኛ ጋር በተለያዩ ሦስት ተጫዋቾች ዙርያ ደሞዛቸውን በ10 ቀን ውስጥ የማትከፍሉ ከሆነ ከማንኛውም የፌዴሬሽኑ እንቅስቃሴ የማታገኙ ይሆናል በማለት የወሰነው የዲሲፕሊን ውሳኔ ተገቢ አይደለም። ይህ በተደጋጋሚ የእኛ ክለብ ላይ የሚወስነው ግብታዊ ውሳኔ እና ጫና የማንቀበል ሲሆን ፌዴሬሽኑ ውሳኔውን በአስቸኳይ በድጋሚ እንዲያጤነው፤ ይህን ውሳኔ የማያነሳ ከሆነ ድሬዳዋ እግርኳስ ክለብ ራሱን ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር የሚያገል ይሆናል። ” የሚለው በመግለጫው ላይ ከተነሱት አንኳር ጉዳዮች መካከል ዋንኛው ሀሳብ ሲሆን ምክትል ፕሬዝዳንቱ አቶ ሱልጣን አልዩ “የምንፈልገው ፌዴሬሽኑ ከፕሪምየር ሊጉ ተሰናብታችኋል የሚል ደብዳቤ እንዲሰጠን ብቻ ነው።” በማለት ጠንከር ያለ ንግግርም አድርገዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

error: