ከፍተኛ ሊግ ለ| ወልቂጤ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ፕሪምየር ሊጉን ሲቀላቀል ድሬዳዋ ፖሊስ ወርዷል

የከፍተኛ ሊጉ ምድብ ለ ወሳኝ የ21ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዕሁድ ሲካሄዱ ከነገሌ አርሲ አቻ የተለያየው ወልቂጤ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ማደጉን አረጋግጧል። ድሬዳዋ ፖሊስ ደግሞ መውረዱ እርግጥ ሆኗል።

ወደ አርሲ ነገሌ ያመራው ወልቂጤ ከተማ ከነገሌ አርሲ ጋር 1-1 ተለያይቶ አንድ ጨዋታ እየቀረው ወደ ፕሪምየር ሊጉ አድጓል። ጨዋታው በጀመረበት ቅፅበት ኳስን በመቆጣጠር ረገድ የተሻሉ የነበሩት እንግዳዎቹ ግብ ለማስቆጠር አምስት ደቂቃዎች ብቻ ፈጅቶባቸዋል። ሐብታሙ ታደሰ ከቀኝ መስመር ጀምሮ እየገፋ ያመጣውን ኳስ ወደ ሳጥን ሰብሮ በመግባት ፍፁም የሆነ የነገሌ አርሲ ተከላካዮች ስህተት በመጠቀም በነፃ አቋቋም ላይ ለነበረው ወጣቱ የመስመር አጥቂ አብዱልከሪም ወርቁ አመቻችቶለት በቀላሉ በማስቆጠር ወልቂጤን መሪ አድርጓል። 

ግብ ካስተናገዱ በኋላ የወልቂጤ ስኬታማ ያልሆኑ ረጃጅም ኳሶችን በመጠቀም የጨዋታውን የበላይነት መውሰድ የቻሉት ባለሜዳዎቹ በተለይ የቴዎድሮስ ታምሩ ድንቅ እንቅስቃሴ የወልቂጤን ተከላካዮች ለተደጋጋሚ ስህተቶችን ሲዳርጋቸው ተስተውሏል። 31ኛው ደቂቃ ምትኩ ጌታቸው ወደ ወልቂጤ ሳጥን የጣለውን ኳስ ሰለሞን ብሩ መሬት ላይ ሳታርፍ አወጣለው ሲል ተጨርፋበት አጠገቡ የነበረው ቴዎድሮስ ታምሩ ተቆጣጥሮ ወደ ግብ መትቶ ግብ ጠባቂው ቤሊንጌ ኢኖህ ኳሷን ለማዳን ጥረት ቢያደርግም አምልጣው ግብ ሆና አርሲ ነገሌዎች አቻ መሆን ችለዋል።

ከዝች ግብ መቆጠር በኋላ የመጫወቻ ሜዳው የሽቦ አጥር ስላልነበረው የነገሌ አርሲ ደጋፊዎች ደስታቸውን ለመግለፅ ወደ ሜዳ በመግባታቸው በተቀያሪ ወንበር ላይ የነበሩ የወልቂጤ ተጫዋቾች እና የቡድን አባላት የምንቀመጥበት ቦታ ከደጋፊዎች የፀዳ ካልሆነ አንጫወትም በማለት ጨዋታው ለሀያ ሦስት ደቂቃ ያክል ተቋርጦ እንደገና ጨዋታው ቢቀጥልም ተጨማሪ ግብ ሳንመለከት 1-1 በሆነ ውጤት ለእረፍት አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ፍፁም የበላይነት ወስደው በተለይ ከመሀል ሜዳው በሚነሱ ኳሶች የቀኝ እና የግራ መስመሩን ለጥጠው ሲጠቀሙ የነበሩት ነገሌ አርሲዎች የሚፈጥሯቸው የግብ አጋጣሚዎች ለግብ ጠባቂው ቤሊንጌ ኢኖህ እጅጉኑ ፈተና ሆነው ተስተውለዋል። ኢሳ ሁሴን በቀኝ መስመር ያሻገራትን ኳስ አብዲሳ ጀማል በግንባሩ ገጭቶ ቤሊንጌ ኢኖህ ያዳነበት ለግብ የተቃረበች ሙከራ ነበረች።

በአንፃሩ በክትፎዎቹ በኩል ወደኋላ አፈግፍገው በመጫወታቸው ለከፍተኛ ጫና የዳረጋቸው ሲሆን በአህመድ ሁሴን የተንጠለጠለው የማጥቃት መርጫቸው ደግም ተጨማሪ ግብ የማስቆጠር አቅማቸው እንዲዳከም አድርጓል። 67ኛው ደቂቃ አብዱልከሪም ወርቁ ለአህመድ ሁሴን ያቀበለውን ኳስ ወደ ሳጥን ሰብሮ ለመግባት ያደረገው ጥረት የነገሌ አርሲ ተከላካዮች ያስጣሉት አስፈሪ አካሄድ ነበር።

የከፍተኛ ሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ አህመድ ሁሴን ሙባረክ ጀማል ላይ በሰረው አደገኛ ጥፋት ቢጫ ካርድ ባየበት ከሁለት ደቂቃ በኋላ ሁለተኛ ቢጫ ካርድ ተመልክቶ በእለቱ ዋና ዳኛ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል። በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ባለሜዳው ነገሌ አርሲ በርካታ የግብ አጋጣሚን ተጭኖ በመጫወት ለመፍጠር ቢጥሩም የኃላ መስመራቸውን በማጠናከር ተጠምደው የታዩት ወልቂጤ ከተማዎች ተሳክቶላቸው ከጨዋታው አንድ ነጥብ ይዘው በመውጣት ወደ ፕሪምየር ሊጉ የማደግ ውጥናቸውን አሳክተዋል።

መድን ሜዳ ላይ ኢትዮጵያ መድን ከ ድሬዳዋ ፖሊስ ያደረጉት ጨዋታ በመድን 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ድሬዳዋ ፖሊስም የምድቡ የመጀመሪያው ወራጅ ቡድን ሆኗል። በኃይሉ ኃይለማርያም እና አቤል ማርቆስ የጎሎቹ ባለቤቶች ናቸው።

ሶዶ ላይ ወላይታ ሶዶ ከ ኢኮስኮ ያደረጉት ጨዋታ 1-1 ተጠናቋል። ሰለሞን ፋሲካ ግብ በማስቆጠር ሶዶዎቹን ቀዳሚ ማድረግ ችሎ የነበረ ቢሆንም በሁለተኛው አጋማሽ ኢኮስኮ ሄኖክ አወቀ ባስቆጠረው ጎል አንድ ነጥብ ይዘው ወጥተዋል።

ኦሜድላ ሜዳ ላይ የካ ክፍለ ከተማ ከ ዲላ ያደረጉት ጨዋታ በየካ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ማትያስ ሹመቴ የብቸኛው ግብ ባለቤት ነው።

አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ አዲስ አበባ ከተማ ከናሽናል ስሜንት ያደረጉትን ጨዋታ አዲስ አበባ 1-0 አሸንፏል። በቀጣይ ጨዋታ ከበላዩ የሚገኙት ቡድኖች ተሸንፈው ከ20 በላይ ጎሎች ማስቆጠር የሚጠበቅባቸው ናሽናል ሴሜንቶች የከተማቸው ሌላኛው ክለብ ድሬዳዋ ፖሊስን ለመከተል ተቃርበዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

error: