ኢትዮጵያ ቡና የጅማ አባ ጅፋርን በሜዳው ያለመሸነፍ ግስጋሴ ገትቷል

በ28ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ኢትዮጵያ ቡና የጅማ አባ ጅፋር በሜዳ ያለመሸነፍ ግስጋሴን 2-1 በማሸነፍ ገትቷል፡፡

ጅማ አባ ጅፋሮች በ26ኛ ሳምንት ከመቐለ 70 እንደርታ አቻ ከተለያው ስብስብ ውስጥ አንድ ለውጥ በማድረግ አዳማ ሲሶኮን በመላኩ ወልዴ በመለወጥ በ 4-4-2 አሰላለፍ ወደ ሜዳ ገብተዋል። ኢትዮጵያ ቡናዎች ደግሞ በ27ኛ ሳምንት ከመቐለ 70 እደርታ ያለግብ አቻ የተለያየው ስብስብ ለውጥ ሳያደርጉ በ4-3-3 አሰላለፍ ለዛሬው ጨዋታ ቀርበዋል።

በዋና ዳኛ ተፈሪ አለባቸው ዳኝነት የተመራው የዕለቱ ጨዋታ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊ ማኅበር ከዚህ ቀደም የቡድናቸው ተጫዋቾች ለነበሩት መስዑድ መሐመድ፣ ሚኪያስ ጌቱ፣ አስቻለው ግርማ እና አክሊሉ ዋለልኝ ያዘጋጁትን የማስታወሻ ስጦታ በማበርከት ነበር የተጀመረው።

የእለቱ ጨዋታ ቀዝቃዛና ሳቢ ያልነበረ ሲሆን ጨዋታውን ለመመልከት ለታደመው ተመልካች አሰልቺ የሚባል እቅስቃሴ የተስለዋለበት ነበር። በአብዛኛው የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የኢትዮጵያ ቡና የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስደው ተጫውተዋል። ቡናዎች እንደነበራቸው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የጎል እድል በመፍጠር ረገድ ውስንነት የነበረባቸው ሲሆን ዳንኤል ደምሴና አህመድ ረሺድ ከርቀት ያደረጓቸው አስደንጋጭ ሙከራዎች በመጀመሪዎቹ አስር ደቂቃዎች ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው። በዚህ ሁኔታ በ15ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር የሳጥኑ ጠርዝ ተከላካዮችን አታሎ ወደ ሳጥን ውስጥ የገባው አቡበከር ለአስራት ቱንጆ አቀብሎት አስራት ቡናን ቀዳሚ ያደረገች ግብ አስቆጥሯል፡፡

ባለሜዳዎቹ ጅማዎች የማሸነፍ እና የመጫወት ተነሳሽነታቸው በዛሬው ጨዋታ አብሯቸው አልነበረም። እንደቡድን የሚደርጓቸው እቅስቃሴዎችም የተቀናጀና ወጥነት ያልነበረው ሲሆን የቡድኑን ፍጥነት የሚጨምረው አስቻለው ግርማ በ20ኛው ደቂቃ በጉዳት ተቀይሮ መውጣቱ የመልሶ ማጥቃት እቅስቃሴያቸው በቀኝ መስመር በዲዲዬ ለብሪ ላይ ብቻ እንዲያነጣጥር አስገድዷቸዋል። አጥቂዎቹ ከቡድኑ ተጫዋቾች ተነጥለው በግላቸው ከሚያደርጓቸው እቅስቃሴዎች ውጭ ቡድኑ እንደቡድን መንቀስ ባይችሉም አቻ ከመሆን ግን አላገዳቸውም። በ26ኛው ደቂቃ በዲዲዬ ለብሪ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ በግምት ከሀያ ሜትር ርቀት ላይ የተገኘውን ቅጣት ምት ኦኪኪ አፎላቢ በግሩም ሁኔታ አስቆጥሮ ባለሜዳዎቹን አቻ ማድረግ ችሏል።

በቀሪዎቹ የመጀመሪያ አጋማሽ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ቡና አንፃራዊ ብልጫ መሀል ሜዳ ላይ ያመዘነ እና የጎንዮሽ ቅብብሎች የበዙበት ነበር። በ35ኛው ደቂቃ አቡበክር ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ሞክሮ የግቡን ቋሚ ታካ የወጣችበት ሙከራ ውጭም የሄነው የሚባል ሙከራ ሳይታይ የመጀመሪያው አጋማሽ 1-1 በሆነ ውጤት ወደ መልበሻ አምርተዋል፡፡

ከእረፍት መልስ እንደ መጀመርያ አጋማሽ ሁሉ የኢትዮጵያ ቡና የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ሲወስዱ በ59ኛው ደቂቃ አቡበክር የግል ጥረቱን በመጠቀም ተከላካዮችን አታሎ ኢትዮጵያ ቡናን እንዲመራ ያስቻለች ግብ ቢያስቆጥርም በ61ኛው ደቂቃ የዘነበው ኃይለኛ ዝናብ ጨዋታው ለ15 ደቂቃዎች እንዲቋረጥ አስገድዷል።

የዝናቡ መጠን እንደቀነሰ የተጀመረው ጨዋታው ሜዳው ላይ በተኛው ውሃ ምክንያት ለተጫዋቾቹ ኳስን በረጅም ሆነ በአጭር ለመቀባበል አዳጋች አድርጎባቸው ነበር። የእለቱ ዋና ዳኛ ሜዳው ለጨዋታ ምቹ አለመሆኑን ቢመለከቱም ጨዋታው እንዲቀጥልና ዘጠና ደቂቃው እንዲጠናቀቅ ማድረጋቸውም አስገራሚ ነበር።

በዚህ ሁኔታ የተካሄደው ቀሪ ደቂቃ የተለየ ነገር ሳይስተዋልበት በኢትዮጵያ ቡና 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። የጅማ አባጅፋር ለ26 ጨዋታዎች የዘለቀ በሜዳ ያለመሸነፍ ግስጋሴም ተገትቷል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡