“የመልሱ ጨዋታ ከዚህ የተለየ ይሆናል” የሌሶቶ አሰልጣኝ ታቦ ሴኖንግ

ለኳታር 2022 የአለም ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያ ኢትዮጵያን የገጠመው የሌሶቶ ብሔራዊ ቡድን ከሜዳው ውጪ ወሳኝ የአቻነት ውጤት ካስመዘገበ በኋላ የቡድኑ አሰልጣኝ ታቦ ሴኖንግ አስተያየታቸውን ሰጥቸዋል።

ስለ ጨዋታው 

ጨዋታው በጣም ጥሩ እና ፈታኝ ጨዋታ ነበር። ኢትዮጵያ በቴክኒኩ ረገድ ጥሩ ቡድን እና ተጫዋቾቹም ጠንካሮች ናቸው። በእንቅስቃሴ ደረጃ ብልጫ ወስደውብናል፤ እኛም ይህን እናውቅ ነበር። እኛ እንደምንፈልገው ገና መቀናጀት፣ መጠናከር እና ዲሲፕሊንድ መሆን ይጠበቅብናል። ምክንያቱም ቡድኑን ከተረከብኩ ትንሽ ጊዜ ነው ያስቆጠርኩት። የአሰልጣኞች ቡድን አባላትን እና ተጫዋቾችን ለማወቅ ገና ጥረት እያደረኩ ነው። ወደ ሀገራችን ተመልሰን ጠንክረን መስራት ይጠበቅብናል። ምክኒያቱም በማጥቃት ሽግግር ወይም በመልሶ ማጥቃት አግኝተን ያልተጠቀምንባቸውን በርካታ እድሎችን ለማስተካከል መስራት አለብን። በዚህ አጋጣሚ የኢትዮጵያን አሰልጣኝ እንኳን ደስ አለህ ማለት እፈልጋለሁ። ጥሩ ኳስ የሚጫወት እና በእንቅስቃሴ ብልጫ መውሰድ የሚችል ቡድን ሰርቷል። በቀጣይ እኛ ጠንክረን ሰርተን ግብ እንዳያስቆጥሩብን ማቆም አለብን።

ስለ መልሱ ጨዋታ

ይሄ የመጀመሪያው አጋማሽ ነው፤ ሁለተኛው አጋማሽ ሌሶቶ ላይ ነው። የደርሶ መልስ ጨዋታ በጣም አስቸጋሪ ነው። የኢትዮጵያን ጥንካሬ እና ድክመት እንገመግማለን። ከዛ አዲስ የጨዋታ መርህ ይዘን እንቀርባለን። የመልሱ ጨዋታ የተለየ ነው የሚኖረው። እኛ ጫና ፈጣሪ ነው የምንሆነው፤ በአንፃሩ ኢትዮጵያ ደግሞ ጫና ውስጥ ትገባለች። በመልሱ ጨዋታ ተደራጅተን በጥሩ ሁኔታ ለጨዋታው እንቀርባለን።

የደጋፊው ጫና

እውነት ለመናገር ይህ አያሳስበኝም። እዚህ የተገኙት ደጋፊዎች እግርኳስን የሚወዱ እና በእግርኳሱ የሚዝናኑ ናቸው። ለተጫዋቾቼ የነገርኳቸውም ‘ጥሩ ኳስ ተጫወቱና ደጋፊዎችን አሰደንቋቸው፤ ደጋፊዎች የተገኙት የኢትዮጵያን ጥሩ እግርኳስ ለማየት እንደሆነው ሁሉ የኛንም ለማየት ነው’ ብዬ ነው። ስለዚህ ተጫዋቾቼ ላይ ተፅእኖ ፈጥሯል ብዬ አላምንም። ያገኝናቸውን እድሎች ባንጠቀምም ወጥ የሆነ መከላከል ስላየሁባቸው በተጫዋቾቼ ኮርቼባቸዋለሁ።


© ሶከር ኢትዮጵያ