የአሰልጣኞች ገጽ | አብርሀም ተክለሃይማኖት: የታዳጊዎች ስልጠና (ክፍል 3)

የሀገሪቱ ውጤታማ እና አንጋፋ አሰልጣኞችን የሥራ ህይወት፣ ተሞክሮ እና አስተሳሰብ በሚዳስሰው “የአሰልጣኞች ገፅ” አሰልጣኝ አብርሀም ተክለሃይማኖትን በተከታታይ እያቀረብንላችሁ እንገኛለን። ከ30 ዓመታት በላይ በአሰልጣኝነት ሙያ ያሳለፉት እና በአሁኑ ወቅት የህፃናት ማሰልጠኛ ማዕከል በመመስረት የታዳጊዎች ስልጠና ላይ የተሰማሩት አሰልጣኝ አብርሀም ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ዘለግ ያለ እና በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ቆይታ አድርገዋል። በዛሬው የክፍል ሦስት መሰናዷችን አሰልጣኙ በአሁኑ ወቅት እየሰሩበት ስለሚገኘው የታዳጊዎች እግርኳስ እና ተያያዥ ጉዳዮችን እያነሳን ቆይታ እናደርጋለን።


“Today’s Talent-Tomorrow’s Hero!” በእግርኳሱ ” የዛሬ አበቦች-የነገ ፍሬዎች!” ማለት ይሆን?

★ “Today’s Talent – Tomorrow’s Hero!” የUEFA መፈክር ነው፡፡ ከአስራ ሰባት ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ በነበርኩ ጊዜ የአውሮፓ እግርኳስ ማህበር ከአፍሪካ የወጣት ቡድን አሰልጣኞችን ጠርቶ ስፔን ሄጄ ነበር፡፡ ከሃምሳ ሦስት ሃገራት የተውጣጣን አሰልጣኞች ባርሴሎና ከተማ ላይ ከተምን፡፡ ያኔ የUEFA ፕሬዘዳንት ሚሼል ፕላቲኒ ነበር፡፡ ላ-ሜሲያንም ጎበኘን፤ ከጉብኝቱ ጋር ተያይዞ ወጣቶች ላይ እንዴት እንደሚሰራ ግንዛቤ ተሰጠን፡፡ በወቅቱ በዚሁ የእድሜ እርከን (U-17) የአፍሪካ ምርጥ እና የአውሮፓ ምርጥ ተጫወቱ፡፡ ያኔ ከእኛ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋች ባይመረጥም ከኤርትራ ግን ሁለት ታዳጊዎች በቡድኑ ተካተው ነበር፡፡ ሱዳንም እንዲሁ አንድ ተጫዋች እንዳስመረጠች ትዝ ይለኛል፡፡ የአፍሪካ ሻምፒዮን ከነበረው ቡድን አሰልጣኝ ተመርጦ ምርጡን ቡድን መራ፤ ከአውሮፓም እንዲሁ፡፡ በአውሮፓ ምርጥ ውስጥ ቦያን ኪርኪችን የመሳሰሉ ተጫዋቾች ነበሩ፡፡ በስልጠናው ፕላቲኒ የተወሰኑ ገለጻዎች አደረገልን፤ ካሉሺያ ቦዋሊያና ኢሳ ሃያቱም ነበሩ፡፡ ከሁሉ በተለየ ባርሴሎና ታዳጊዎችን በምን መልኩ አሳድጎ ለወግ-ማዕረግ የሚያበቃበትን መንገድ በግልጽና በቅርበት ተከታትለናል፡፡ ጊዜው እ.ኤ.አ. 2007 አካባቢ ሮናልዲንሆ በአለም እግርኳስ መድረክ የነገሰበት ዘመን ነበር፡፡ ኤቶም የጎመራበት ወቅት ነበር፡፡ የቡድኑ አሰልጣኝ ፍራንክ ራይካርድ ባርሴሎናን እየመራ ልምምድ ሲሰሩ፣ ከአትሌቲክ ቢልባዖ ጋር ደግሞ ጨዋታ ሲያደርጉ ለመታደም ቻልን፡፡

 አንጋፋውን የUEFA ቴክኒክ ዳይሬክተር አንዲ ሮክስበርግን እንዴት አገኘሃቸው?

★ አንዲ ሮክስበርግ ትልቅ ስኮትላንዳዊ የእግርኳስ ባለሙያ፣ ጎበዝ ጸሃፊና በሳል መምህር ነው፡፡ እግርኳስን በትልቅ ደረጃ አልተጫወተም፡፡ ነገርግን በአውሮፓ ታላላቅ የሚባሉ እንደ አርሰን ቬንገር፣ ሰር አሌክስ ፌርጉሰንና የመሳሰሉ አሰልጣኞችን ሰብስቦ ዓመታዊ የአሰልጣኞች ውይይት ያዘጋጃል፤ ያስተምራል፡፡ አንዳንድ ሰው በተፈጥሮው እግርኳስን መምራት፣ መተንተንና ማስተማር ይችላል፡፡ አንዲ ሮክስበርግ ያ ሰው ነው፡፡ አልፎአልፎ የተወሰኑ Newsletters ይልክልኝ ነበር፡፡ UEFAን ከለቀቀ በኋላ በአሜሪካ እንደ አማካሪ ሆኖ ይሰራ እንደነበር አውቃለሁ፡፡ ከዚያ በኋላ እኔም ብዙ መጻጻፍ አቁሜያለሁ፡፡ ሰሞኑንማ ፖለቲከኛ የሆንኩ መሰለኝ በብዛት ስለ ሃገር ነው እየተከታተልኩ ያለሁት፡፡

የቤተሰብ ተፅዕኖ ይሆን ፖለቲካውን እንድትከታተል የገፋፋህ?

★ ይመሥለኛል፤ በቤታችን ሁሉም ወንድሞቼ ፖለቲከኞች ናቸው፡፡ ወደ ስፖርቱ የገባሁት እኔ ብቻ ነኝ፡፡

ህጻናት ላይ እንድትሰራ ያነሳሳህ የ<UEFA> ተመክሮ ነው?

★ እሱ እንኳ ከድሮ ጀምሮ የነበረ ነው፡፡ ፍላጎቱ ከልጅነቴ የተፀነሰ ይመስለኛል፡፡ ጎጃም መምህር ሆኜ እየተጫወትኩ እንኳ የህጻናት ቡድን ነበረኝ፡፡ በ1960ዎቹ ልጅ ሆኜ መቐለ እያለሁም በሰፈር ቡድን እንኳ C,B,A እያልን ነው ወደ ላይ የወጣነው፡፡ ያኔ በከተማዋ እግርኳስ በደማቅ ሁኔታ ይካሄድ ነበር፡፡ ነገርግን የእኛ ታላላቆች ወደ ትግል ሲሄዱ ስፖርቱ ተዳከመ፡፡ በአካባቢው ሰላም ጠፋ፤ እኛም ተበታተንን፡፡ እኔና ገብረመድህን ኃይሌ ወደ ጎጃም ሄድን፡፡ እኔ ከኮተቤ መምህራን ኮሌጅ በአስተማሪነት ተመሮቄ ነበር ወደ እዚያ ያመራሁት፡፡ ሆኖም የህጻናት ስልጠናን ከበፊትም ልሰራበት የማስበው ጉዳይ ነበር፡፡ በእርግጥ በቅርቡ ወደዚያ ሥራ የገባሁበት ምክንያት አንደኛው አሁን ባለው የእግርኳስ ችግር ሲሆን ሁለተኛ ደግሞ በትልቅ ደረጃ ክለቦችን ማሰልጠን ካቆምኩኝ በኋላ ሥራ አልነበረኝም፡፡ ስለዚህ ‘በህጻናት ሥልጠናው ከተሰማራሁ ውጤታማ እሆናለሁ፡፡’ በሚል ዕምነት ገብቼበታለሁ፡፡

ከላይ በተጠቀሰው የUEFA መፈክር መሰረት በኢትየጵያ እግርኳስ “የአሁኖቹ ባለ ተሰጥኦ ህጻናት የነገዎቹ ታላላቅ ተጫዋቾች!” ይሆናሉ ብለህ ታምናለህ? መልሱን በአንተ አካዳሚ ውስጥ ባሉ ታዳጊ ሰልጣኞች ላይ ተመሥርተህ ከመዘንከው አንጻር መስጠት ትችላለህ፡፡

★ ይኸውልህ- እኛ ልጆች ሳለን ኳስን የምንጫወተው ለእርካታ ብቻ ነበር፡፡ አሁን ግን ህጻናቱ ወደ አውሮፓ ለመሄድ እስከ ማለም የደረሰ ሐሳብ ውስጣቸው አለ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ዘመኑ ይመስለኛል፤ Exposure አለ፤ ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥን፣ የመሳሰሉት ምኞቶቻቸውን አተልቆታል፡፡ ዜናዎች ይሰማሉ፤ እንደ ሮናልዶ መሆንን ያልማሉ፡፡ ድሮ እኛ የምናስበው በቅርብ አካባቢያችን ያሉትን ግፋ ሲል ደግሞ መንግስቱ ወርቁን ነበር መሆን የምንሻው፡፡ የአሁኖቹ ልጆች ግን ሩቅ ተሻግረው ይመኛሉ፤ ያልማሉ፡፡ ተገቢ ሥራ ከተሰራባቸው ልዩ ክህሎት ያላቸው ልጆች አሉን፤ ግን ብዙ ተግዳሮቶችን ማለፍ ይጠበቅብናል፡፡ እንደሚታወቀው ከፍተኛ የሜዳ ችግር አለ፤ ያሉትም ፍጹም ምቹ አይደሉም፤ ለህጻናቱ ይቅርና በትልቁ ፕሪምየር ሊግ ለሚጫወቱት እንኳ በትክክል እንዲቀባበሉ የሚያስችሉ አይደሉም፤ ጥራት ያላቸው ሜዳዎች አጥተናል፡፡

ይህን ችግራችን ከመገንዘብ አንስቶ መፍትሄ እስከመስጠት ድረስ ቸልተኝነት ይታይብናል፡፡ በአውሮፓ ሜዳቸውን እንዴት እንደሚንከባከቡ እናያለን፤ ጨዋታ ከመጀመሩ አስርና አስራ አምስት ደቂቃዎች በፊት ሳሩ ውሃ ሲጠጣ እንመለከታለን፤ መሬቱ ደረቅ ሆኖ ተጫዋቾቹ ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደርጉለታል፡፡ ይህን በየሄድኩበት ቦታ ሁሉ ጠይቄና አይቼ የተገነዘብኩት ነው፡፡ አንድ ጊዜ እንዲያውም ‘የሜዳው መርጠብ ተጫዋቾችን እንዲያዳልጥ አያደርግም ወይ?’ ብዬ ስጠይቅ ” መሬቱ ደረቅ ሲሆን የተጫዋቾቹ እግር ይጎዳል፤ ይቆረቁራቸዋል፤ ለቅብብልም አይመቻቸውም፡፡” የሚል ምላሽ አግኝቻለሁ፡፡ የኢትዮጵያ ሜዳዎች ላይ’ኮ ኳሷን እዚህ እየጠበቅሃት እዚያ ነው የምታገኛት፡፡ የእግርኳስ ፌዴሬሽናች ነባር የአዲስ አበባ ስታዲየም አትክልተኛና ዘበኛ የሆነ አንድ ሰው ያለኝን ልንገራችሁ፥ ‘ሜዳው ግን አባት አለው?’ ብዬ ጠየቅሁት፡፡ ” አባቱማ ድሮ ሞቱ፡፡” አለኝ፡፡

ክቡር አቶ ይድነቃቸው ሁሌም ወደ ቢሯቸው ከመግባታቸው በፊት ጠዋት ሜዳውን የመጎብኘት ልማድ ነበራቸው፡፡ በዓለምአቀፍ እግርኳሳዊ ጉዳዮች ብዙ ልምድ ስላዳበሩ የሜዳን ጥቅም ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ እንዳጋጣሚ የተበላሸ ነገር ካዩ የሚመለከተውን አካል ጠርተው “ይህቺን አስተካክሉ፡፡” ይላሉ፡፡ ጨዋታ የሚያምረው ጥሩ የመጫወቻ ሜዳ ሲኖር እንደሆነ ስለሚያውቁ ለሜዳ ጥራት ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣሉ፡፡ በቅርብ ጊዜ ወደ አመራርነት የመጡት ሰዎች ግን አይደለም ሜዳን ማወቅ መደበኛ ሥራቸውን እንኳ በቅጡ በተረዱ፡፡

ጨዋታ ሊጀመር ጥቂት ደቂዎች ሲቀሩ ሜዳን በመቆፈር የማስተካከል ሥራ ሲሰራም እያየን ነው..

★ አዎን! ከላይ የተጠቀሰው ቸልተኝነት ውጤት ነው፡፡ የተጫዋቾች ተሰጥኦ የሚወጣው ሜዳ ሲኖር ነው፡፡ ትልቅ የሜዳ እጦት አለ፤ ያሉትም ደግሞ አሰቃቂ የጥራት ችግር አለባቸው፡፡ ጭራሽ ያልተስተካከሉ ናቸው፡፡ ስለ እውነት ለመናገር የክህሎት ችግር የለብንም፡፡ ኢትዮጵያ የባለ ተሰጥኦዎች ሃገር ናት፡፡

ከበርካታ ዓመታት የክለብና የብሄራዊ ቡድኖች አሰልጣኝነት ቆይታ በኋላ ህጻናትን ወደ ማብቃት ሥራ መመለስ በብዙ አንጋፋ አሰልጣኞች እየተለመደ የመጣ ውሳኔ ይመስላል፡፡ አስራት ኃይሌ በ1990ዎቹ አጋማሽ በቦሌ ኮሚኒቲ ት/ቤት ታዳጊዎችን ሲያሰራ ነበር፡፡ አሰልጣኝ ከማል አህመድ በሃዋሳና በሻሸመኔ፣ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በአዲስ አበባ የተለያዩ ቦታዎች አንተ ደግሞ በመቐለ የህጻናት አካዳሚዎች ከፍታችሁ እየሰራችሁ ትገኛላችሁ፡፡ እናንተ አንጋፋ አሰልጣኞች በትልቅ ደረጃ ካሰለጠናችሁ በኋላ ወደ ህጻናት ስልጠና ለመመለስ አልዘገያችሁም?

★ እጅግ በጣም ዘግይተናል እንጂ! በካሜሮን- የእነ ኤቶን፣ በጋና-የእነ አቢዲ ፔሌን አካዳሚዎች አይቻለሁ፡፡ የኮትዲቯሩን አሴክ ሚሞሳስም ታዳጊዎቹን በየዓመቱ ወደ ስፔን እየወሰደ ተጫዋቾቹ አለምዓቀፍ ልምድ እንዲኖራቸው ያደርጋል፡፡ እኔም ወደ ስፔን በምሄድበት ጊዜ ባጋጣሚ ሞሮኮ አውሮፕላን ጣቢያ ውስጥ አንድ አይነት ቱታ የለበሱ ተጫዋቾችን አይቼ ይዟቸው ወደነበረው ሰው ሄድኩ፡፡ ከዚያ ስለ ልጆቹ ስጠይቀው እነዚህ የአስራ አራት ዓመት ልጆች የኮትዴቩዋሩ ታዋቂ አካዳሚ ህጻናት እንደሆኑና በስፔን ለአንድ ወር የሚቆይ ስልጠና እንደሚወስዱ አስረዳኝ፡፡ እንግዲህ ይህን መሰል ልምድ እያገኙ የሚያድጉ የሃገሪቱ ልጆች የት እንደሚደርሱ ይታወቃል፡፡ እኛ ጋር ደግሞ በሰፈራቸው የሚጫወቱበት ሜዳ ነስተናቸዋል፡፡ በአካዳሚ ደረጃም ቢሆን ኦፊሺያል በሆነ መልኩ ቀድሜ የከፈትኩት እኔ ነኝ ማለት እችላለሁ፡፡ የንግድ ፍቃድ አውጥቼ፣ ግብር እየከፈልኩና መንግስት አውቆት እየሰራሁ ያለሁትን ማለቴ ነው፡፡ በእርግጥ ቀደም ብለው የጀመሩ አሉ፤ ነገርግን ይህንን እያደረግንም መንግስት ዞር ብሎ አያየንም፤ ፌዴሬሽኑም “ወዴት አላችሁ?” አይለንም፡፡  የወደፊቱንም እንጃ!

ወደ ውጪ ሃገርም (አሜሪካ-ቺካጎ) ይዘን የሄድነው እኛ (እኔና ነብሱን ይማረውና-አሰግድ ተስፋዬ) ነበርን፡፡ ለሶስት ተከታታይ ዓመታት ስድሳ ልጆች ይዘን ሄደን ልጆቹን ብዙ ነገሮች እንዲማሩ አደረግን፡፡ የሚገርመው አስር ሜትር ያህል ኳስ ማራቅ የማይችል ሰልጣኝ ነበረን፤ በተመሳሳይ የእድሜ ክልል የሚገኙት የእነርሱ ልጆች ደግሞ ከሜዳው አንደኛው ጫፍ ወደ ሌላኛው ጥግ ያደርሳሉ፡፡ ይህ የልዩነታችን ቁንጽል ማሳያ ይሆናል፡፡ በእርግጥ ኢኮኖሚያቸው የሚፈቅድላቸውን የደህና ቤተሰብ ልጆች ነው ይዘን የሄድነው፤ አካዳሚው የልጆቹን ወጪ የመሸፈን አቅም ስለሌለው እኛ የማስተባበር ሥራ ብቻ ሰራን፡፡ በኢትዮጵያ እግርኳስ ታች ተገቢው ሥልጠና እንደማይሰጥም ማረጋገጫ ሆኖልናል፡፡ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ለህጻናት የእግርኳስ መጫወቻ ተብሎ የተሰራ ሜዳ የለም፤ ለመሥራት ቦታ ብትጠይቅም የሚሰጥህ የለም፡፡ የቀድሞዎቹ ኳስ ሜዳዎችም ህንጻ እየተሰራባቸው ልጆች መጫወቻ እያጡ አስፋልት ላይ እየተጫወቱ ነው፡፡ ወደ መቐለ የሸሸሁትም ምናልባት እዚያ የተሻለ ምቹ ሁኔታ ካለ ብዬ ነው፡፡ በፊትም መቐለ አካዳሚ የመክፈት ሐሳብ ቢኖረኝም እዚህ ያለውን ግን እዘጋዋለሁ ብዬ ፈጽሞ አስቤ አላውቅም፡፡

እንዲህ አይነቱን የአካዳሚ ሥልጠና መስጠት ያለባቸው በትልቅ ደረጃ የሰሩት አሰልጣኞች አይመስሉንም፡፡ ወደ ታች ተመልሶ እንደገና ከመጀመር ሥራውን በዘርፉ ብቁ ለሆኑ ባለሙያዎች በመስጠት እናንተ ከላይ ያለውን የእግርኳስ ከባቢ በማሻሻል ላይ ብታተኩሩ አይሻልም?

★ እኔ እንኳ የማስበው በተቃራኒው ነው፡፡ የነገ የእግርኳሳችን ጀግኖች የሚፈጠሩት ከታች ስለሆነ እኛም እዚያ ላይ መሥራት አለብን፡፡ ከላይ በብሄራዊ ቡድንና በክለቦች ደረጃ ያሉትን ችግሮች የተረዳ ሰው ታች ወርዶ እያስተካከለ ለመምጣት አይከብደውም፡፡ እኔ ትልልቆቹ ወደ ታች ቢወርዱ የሚል ሃሳብ ነው ያለኝ፡፡ አለበለዚያ ሥልጠናው ለማጅ-ለ-ለማጅ አይነት ይሆናል፤ አሰልጣኙ ጀማሪ፥ ሰልጣኞቹ ደግሞ ገና ታዳጊዎች ሲሆኑ ያስቸግራል፡፡ ስለዚህ ቦታው ላይ ልምድ ያለው ሰው ካለ የሥልጠናውን ጥቅም የመተንተን ችሎታ ሊኖረው ይገባል፡፡ ለእኔ መውረድ ብዬም አላስበውም፤ እንዲያውም ታች መሥራት የትልቅነት መገለጫ ነው፡፡ ለጀመሩት ሰዎችም ትልቅ አክብሮትና አድናቆት አለኝ፡፡ ጎንለጎን ፌዴሬሽኑ ሥልጠናው በምን መልኩ እየተካሄደ እንደሆነ ግምገማ ቢያደርግ ጥሩ ይመሥለኛል፡፡ከዚህ በተጨማሪ ፌዴሬሽኑ በማስተባበር፣ በመርዳት፣ በማገዝና በመሳሰሉት አካዳሚዎች እንደ ድርጅቶች በቋሚነት ራሳቸውን እንዲችሉ ቢያደርግ ብዙ ልጆች ልናፈራ እንችላለን፡፡ አሰልጣኞችም ክለብ ማሰልጠን ሲያቆሙ ” ሥራ የለኝም፡፡” ብለው ከሚያማርሩ ወደዚሁ የሥልጠና መስክ ይገባሉ፡፡

በእግርኳስ የክህሎት ሥልጠና ምንድን ነው?

★ በተፈጥሮ የተገኘ ክህሎትን ወደ ውጤታማነት ለመቀየር የሚያስችሉ ስልጠናዎች የክህሎት ማሳደጊያ ዘዴዎች ናቸው፡፡ የተፈጥሮ ሥጦታን በተለያዩ ትምህርቶች ማጎልበት ይቻላል፡፡ በእግርኳስም ሆነ በሌላው የሥራ ዘርፍ መተጋገዝ የግድ ነው፡፡ ጓደኛዬ ሲደክም እኔ መርዳት አለብኝ፡፡ የክህሎት ሥልጠና በህይወት የሚያጋጥሙ ማናቸውንም ተግዳሮቶችና ፈተናዎች የሚታለፉባቸውን መላዎች የማግኘት ትምህርቶችን ሁሉ ያጠቃልላል፡፡ መሸነፍና ማሸነፍ የህይወት ገጽታዎች እንደሆኑና ሽንፈትን በጸጋ የመቀበል ልማድ፣ በስነ ልቦና ለችግሮች እጅ ያለ መሥጠት ትምህርቶችና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ የግል ችሎታን የማዳበር ቴክኒካዊ ሥልጠናም ከክህሎት ልምምዶች አንደኛው ነው፡፡

“በብራዚልና ስፔን ቆይታዬ በቅድመ-ሥልጠና ወቅት የኢትዮጵያ ህጻናትና የእነዚህ ሃገራት ህጻናት ክህሎት ተመሳሳይ መሆኑን ተገንዝቤያለሁ፡፡” ብለሃል፡፡ ሐሳቡን በተለየ መንገድ እንዳናየው የህጻናቱን የክህሎት ተመሳስሎ አብራራልን…

★ ሰው በሰውነቱ ሰው ነው፡፡ ቀለሙ ነጭም ሆነ ጥቁር በቃ ሰው- ሰው ነው፡፡ የሰው ልጅ በተፈጥሮ ከፈጣሪና ከቤተሰብ የሚያገኘው ሥጦታ አለው፡፡ ያንን መክሊት በስልጠና ማዳበርና ያለማዳበር ልዩነት ይፈጥራል፡፡ በስፔን ቆይታዬ የታዳጊዎቹ ሥልጠና ላይ ልጆቹ ሲጫወቱ ሳይ ‘እንዲህማ የእኛም ልጆች ይጫወታሉ፡፡’ ብዬ ደመደምኩ፡፡ ብራዚል ውስጥም በዚኮ አካዳሚ የሚሰለጥኑትን ህጻናት ስመለከት ተመሳሳዩን አሰብኩ፡፡ ልዩነታችን አስፈላጊውን ሥልጠና በተገቢው እድሜ የማግኘት እና ያለማግኘት ዕድል ነው፡፡ ለ<Sophisticated Trainings> የሚጠቅሙ የሥልጠና መሳሪያዎችን በአግባቡ የማሟላትና ያለማሟላትም ነው፡፡

ችሎታ ልክ እንደ ተፈጥሮ ሃብት ነው፡፡ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሃብት የታደለች ሃገር ናት፤ ነገርግ አልተጠቀመችበትም፡፡ የስልጣኔ ኋላ-ቀርነት እና የምጣኔ ሃብት እጥረት ተፈጥሮ የለገሰችንን ጸጋ እንዳንጠቀም ማነቆ ሆነውብናል፡፡ እግርኳሱ ላይም እንዲሁ ነው፡፡ እኔም ያንን የጻፍኩት ከዚህ አንጻር ነው፡፡ ልጆቻችን <Advanced> ሥልጠና ቢያገኙ ፕሮፌሽናል የመሆን አቅም አላቸው፡፡መንገድ ላይ ስሄድ የስድስትና የሰባት ዓመት ልጆች ኳስ ይዘው ጥሩ ሲጫወቱ ‘ማን አሰልጥኗቸው ይሆን?’ ብዬ እገረማለሁ፡፡ ስለዚህ ማንም ህጻን በተፈጥሮ የታደለው ክህሎት አለው፤ ቁምነገሩ የመጠቀምና ያለመጠቀም ጉዳይ ነው፡፡ በሩጫውም ብናይ እንዲሁ ነው-ማንም ተነስቶ አያሸንፍም፤ ተሰጥኦውን በጥሩ ሁኔታ የተጠቀመበት ነው ባለ ድል የሚሆነው፡፡ ኃይሌ ባለ ተሰጥኦ ነው፤ ምሩጽ ባለ ተሰጥኦ ነው፡፡ በተፈጥሮ ያገኙትን ክህሎት በአደባባይ በሚገባ ተጠቀሙ፤ አሸናፊ ሆኑ፡፡
በቅድመ ሥልጠና ወቅት እንደ ማንኛውም ልጅ ጥሩ የሚንቀሳቀሱ ታዳጊዎችን በመመልከት ብቻ ተጫዋቾቻችን በቴክኒክ ክህሎት የበለጸጉ ስለመሆናቸው ድምዳሜ ላይ መድረስ እንችላለን?

★ ጨርሰን መናገር አይቻልም፤ ምክንያቱም ታዳጊዎቹ በተፈጥሮ ካገኙት ስጦታ የተወሰነውን ብቻ ነው የሚጠቀሙት፡፡ ደረጃውን የጠበቀ ሥልጠና ቢጨመርበት በቴክኒክ ስለመበልጸግ ልናነሳ እንችል ይሆናል፡፡ በሥልጠና አለማግኘት ምክንያት ሊያድግ የሚችለው ችሎታቸው ሳይታይ የሚቆሙበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡

በሃገራችን እግርኳስ የተጫዋቾችን ተፈጥሯዊ ችሎታ በቀላሉ በመገንዘብ ረገድ የአሰልጣኞች ሚና እምብዛም እንደሆነ ይነገራል፡፡ ክህሎትን በፍጥነት መረዳት የሚችሉ እንደ ሥዩም አባተ ያሉ ባለ ንስር አይን ባለሙያዎች ቁጥርም አናሳ እንደሆነ ይወራል፡፡ አሰልጣኞቻችን ተሰጥኦን ከማንበብና ከመለየት (Talent Identification) አኳያ ያለባቸው ችግር ከምን የመነጨ ነው?

★ እንግዲህ ይህ ሁኔታ ከስልጠና ፍልስፍና መለያየት ጋር ይያያዛል፡፡ በአሰለጣጠን መርህ የአሰልጣኙ የግል ዕምነት ወሳኝ ድርሻ አለው፡፡ ክህሎትን በመለየት ረገድ ጥሩ እንድትሆን በታዳሚዎች ላይ ያለህ እምነት መሰረታዊ ነው፡፡ አንዳንድ አሰልጣኝ ከተለያዩ ክለቦች ተጫዋቾችን በማዘዋወር ቡድን ይመሰርታል፤ አንዳንዱ ደግሞ ከሥር ያሉ ተጫዋቾችን አሳድጎ ለወግ-ማዕረግ ያበቃል፡፡ አሰልጣኙ ወደ እግርኳሱ የመጣበት መንገድም ተጽዕኖ አለው፡፡ የሥዩም ፍልስፍና ብርቅ የሆኑ ተጫዋቾችን አስገኝቷል፤ እርሱ ድንቅ ተጫዋቾችን ማብቃት ይችላል፡፡

ይቀጥላል…


ክፍል ሁለትን ለማግኘት ይህን ይጫኑ :point_right: ክፍል 2