አአ ከተማ ዋንጫ | ሰበታ ከተማ የፍፃሜ ተፋላሚ መሆኑን አረጋገጠ

በ14ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የመጀመሪያ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ሰበታ ከተማ መከላከያን በመርታት በመጪው እሁድ የሚደረገው የፍፃሜ ተፋላሚ መሆኑን አረጋግጧል።

ቀዝቀዝ ባለ የአየር ንብረት የተካሄደው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በተለይ በመጀመሪያ አጋማሽ ጨዋታ መከላከያዎች የተሻሉ ነበሩ። በዚህም የጨዋታውን የመጀመሪያ ሙከራ በ3ኛው ደቂቃ ላይ ቴዎድሮስ ታፈሰ በግሩም ሁኔታ ያሳለፈለትን ኳስ ፍቃዱ ዓለሙ መትቶ ኢላማዋን ሳትጠብቅ በቀረችው ሙከራ ማድረግ ችለዋል።

በተቃራኒው እንደሰሞኑ ጨዋታዎች ሁሉ በመጀመሪያው አጋማሽ ደካማ የነበሩት ሰበታዎች በ21ኛው ደቂቃ ቀዳሚ የሆኑበትን ግብ በግሩም መልሶ ማጥቃት የተገኘውን ኳስ ታደለ መንገሻ አማካኝነት ማስቆጠር ችለዋል።

ከግቧ መቆጠር በኃላ ሰበታዎች ልዩነታቸውን ሊያሰፉበት የሚችሉትን አጋጣሚ ቢያገኙም መስኡድ መሀመድ ከመከላከያው ግብጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ሊያመክናት ችሏል።

ምንም እንኳን ግብ ቢያስተናግዱም መከላከያዎች በፍጥነት ወደ ግብ ለመድረስ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል በዚህም ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ ተፈራ አንለይ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ በሰበታ ተከላካዩች ስህተት ታግዞ ዳዊት ተፈራ በ37ኛው ደቂቃ ባስቆጠራት ግብ ሁለቱ ቡድኖች 1ለ1 በሆነ ውጤት ወደ መልበሻ ክፍል ሊያመሩ ችለዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ በ54ኛው ደቂቃ ባኑ ዲያዋራ ላይ ዘነበ ከበደ በሰራው ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ዲያዋራ ራሱ በመምታት አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።

ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው በተለየ የኃይል አጨዋወት በርከት ያለበት ነበር፤ መከላከያዎች ወደ ጨዋታው ለመለለስ ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም በቀጥተኛ አጨዋወት ላይ ያተኮረው መንገዳቸው ግን ውጤታማ አልነበረም። በአንፃሩ ሰበታዎች በሁለተኛው አጋማሽ እንደ ወልዋሎው ጨዋታ ሁሉ ጥሩ የመልሶ ማጥቃት ቡድን መሆናቸውን አስመስክረዋል።


በ85ኛው ደቂቃ ላይ የእለቱ ረዳት ዳኛ ከጨዋታ ውጭ በማለቷ የመከላከያ ተጫዋቾች መዘናጋታቸውን ተከትሎ የተገኘውን ኳስ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ዳዊት እስጢፋኖስ የቀድሞ ክለቡ ላይ እጅግ ማራኪ የሆነች ኳስን ከረጅም ርቀት ማስቆጠር ችሏል። ከግቧ መቆጠር በኋላ ዳዊት ለቀድሞ ክለቡ ደጋፊዎች ወታደራዊ ሰላምታ በመስጠት ደስታውን ገልጿል።

ጨዋታው በሰበታ ከተማዎች 3-1 አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ ሰበታ በመጪው እሁድ በተጠባቂው የፍፃሜ ጨዋታ የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡናን አሸናፊ የሚገጥም ይሆናል።


በጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ ዩጋንዳዊው የሰበታ ከተማ ተከላካይ በሰራው ጥፋት በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ሲወገድ የሰበታ ከተማው ታደለ መንገሻ የጨዋታው ኮከብ በመሆን ተመርጧል።


© ሶከር ኢትዮጵያ