“ለኮትዲቯሮች አክብሮት ቢኖረንም ራሳችንን ዝቅ አናደርግም።” ሽመልስ በቀለ

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አምበል ሽመልስ በቀለ ከነገው ጨዋታ በፊት ያለውን አስተያየት ለጋዜጠኞች ሰጥቷል።
ስለማዳጋስካሩ ጨዋታ

“በማዳጋስካሩ ጨዋታ ተጨዋቾቹ ጥሩ ተንቀሳቅሰዋል። ሁሉም እንደቡድን ነበር ሲጫወት የነበረው። ከነሱም (ማዳጋስካር) በተሻለ ወደ ጎል ቀርበን አጋጣሚዎችን ፈጥረናል። ነገር ግን ያገኘናቸውን አጋጣሚዎች አለመጠቀማችን የምንፈልገውን ሶስት ነጥብ አሳጥቶናል።”

እንደ አምበልነትህ ቡድኑ የሚጎለው ነገር ምንድን ነው?

“እኔ ይጎላል ብዬ የማስበው የአጥቂ ጉዳይ ነው። በማዳጋስካሩ ጨዋታ ብቻ ሳይሆን ከዛም በፊት ወደ ጎል ደርሰን በአጨራረስ ችግር ኳሶችን ስናባክን ነበር። እርግጥ ቡድኑ ጥሩ ጥሩ አጥቂዎች አሉት። ነገር ግን ተጨዋቾቹ (አጥቂዎቹ) በክለብ ደረጃ የሚያሳዩትን ብቃት በብሄራዊ ቡድን ደረጃ እያሳዩ አይገኝም። ግን በእንቅስቃሴ ደረጃ ተጫዋቾቹ የሚያሳዩት ነገር ጥሩ ነው።”

ተጫዋቾቹ በክለብ ደረጃ የሚያሳዩትን ነገር ለምን ወደ ብሄራዊ ቡድን ማምጣት ከበዳቸው?

“ተጨዋቾቹ ክለብ ላይ ረጅም ጊዜ ይቆያሉ። በየቀኑም ልምምድ ይሰራሉ። ይህ ነገር በክለብ ደረጃ ጠቅሟቸዋል። በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ግን ጨዋታዎችን በተደጋጋሚ ስለማያደርጉ የቸገራቸው ይመስለኛል። በአጠቃላይ ግን አዲስ እና ወጣት ተጨዋቾች በመሆናቸው ብቃታቸውን ይዘው የሚቆዩ ከሆነ ጉዳይ ወደፊት ይስተካከላል።”

ስለ ተጋጣሚ ቡድን እና ስለ ቡድኑ ዝግጅት?

“ኮትዲቯር ትልቅ ቡድን ነው። ትላልቅ ተጨዋቾችን የያዘ ቡድን ነው። ነገር ግን ለነሱ አክብሮት ቢኖረንም ራሳችንን ወደ ታች አናደርግም። እነሱ የተሻለ ቦታ ቢጫወቱም እኛም ጋር ኳስ የሚችሉ ተጨዋቾች አሉ። ነገም ከእነሱ (ኮትዲቯሮች) የተሻለ እንጫወታለን ብዬ አስባለሁ። በስነ ልቦናም ረገድ በተሻለ ተዘጋጅተናል።”

ከነገው ጨዋታ ምን እንጠብቅ?

“ነገ ጥሩ ውጤት ይመጣል ብዬ በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ። ውጤቱን አብረን እናያለን።”


© ሶከር ኢትዮጵያ