የሴካፋ ምድብ ድልድል ኢትዮጵያ እና ኤርትራን አገናኝቷል

አስራ ሁለት ሀገራትን በሦስት ምድቦች ከፍሎ የሚደረገው የሴካፋ ወንድ ብሔራዊ ቡድኖች ዋንጫ እና ለመጀመርያ ጊዜ የሚከናወነው የሴካፋ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ዋንጫ የዕጣ ማውጣት ሥነ-ስርዓት ዛሬ በታንዛንያ ተከናውኗል።

በዩጋንዳ አስተናጋጅነት ከኅዳር 27 እስከ ታኅሳስ 9 ድረስ የሚደረገው የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ሀገራት ዋንጫ ውድድር ላይ በዞኑ ውስጥ የሚገኙ ሀገራትን ተሳታፊ በሚያደርግ ሲሆን በዚህ ሻምፒዮና ዲሞክራቲክ ሪፐሊክ ኮንጎ በተጋባዥነት መሳተፏም ተረጋግጧል፡፡

በሦስት ምድቦች ተከፍሎ ከሁለት ሳምንታት በኃላ በካምፓላ በሚሰናዳው ውድድር ላይ ሀገራችን ኢትዮጵያ በምድብ አንድ ከዩጋንዳ፣ ቡሩንዲ እና ኤርትራ ጋር ስትደለደል በምድብ ሁለት ደግሞ ሱማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን እና ተጋባዧ ዲሞክራቲክ ኮንጎን የያዘ ሲሆን በመጨረሻው ምድብ ሦስት ደግሞ ኬንያ፣ ታንዛኒያ ጅቡቲ እና ዛንዚባር ተካተዋል፡፡

ድልድሉ ለዓመታት ከተቋረጠው ግንኙነታቸው በኋላ ባለፈው ዓመት ወደ መልካም ግንኙነት የተመለሱት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ከረጅም ዓመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ በብሔራዊ ቡድን ደረጃ እርስ በእርስ ጨዋታ የሚያደርጉበት አጋጣሚን ፈጥሯል።

በተመሳሳይ ዛሬ የሴካፋ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ዋንጫ የምድብ ድልድልም ይፋ ሆኗል፡፡ ኅዳር 29 በዩጋንዳ በሚጀመረው በዚህ ውድድር ላይ ሰባት ሀገራትን የሚያሳትፍ ሲሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ለዚህ ውድድር አዲስ አሰልጣኝ ከቀጠረ በኃላ በውድድሩ ላይ ተሳታፊ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

በድልድሉ መሠረት እንደ ወንዶቹ ሁሉ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በዚህም ውድድር በአንድ ምድብ ተገናኙ ሲሆን በምድብ አንድ ኢትዮጵያ፣ ዩጋንዳ፣ ኤርትራ እና ደቡብ ሱዳን ፤ ምድብ ሁለት ደግሞ ታንዛንያ፣ ቡሩንዲ እና ጅቡቲን አቅፏል፡፡

ሶከር ኢትዮጵያ ባገኘችው መረጃ መሠረት አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ እና ረዳቶቹ በሴካፋ ዋንጫ ላይ ቡድኑን ለማዘጋጀት ከቀጣዩ ሳምንት ጀምሮ ወደ ልምምድ የሚገቡ ሲሆን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሚጀመርበት ወቅት ከመሆኑ አንፃር ከአንድ ክለብ ሁለት ሁለት ተጫዋቾችን ብቻ እንደሚመርጡ ተሰምቷል። በስብስባቸው ውስጥም በርካታ አዳዲስ እና ወጣት ተጫዋቾችን በውድድሩ ላይ ይዞ ለመቅረብ እንዳሰቡም ሰምተናል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ