ሪፖርት| ስሑል ሽረ ዓመቱን በድል ጀምሯል

ስሑል ሽረዎች በዲድዬ ሌብሪ ብቸኛ ግብ ኢትዮጵያ ቡናን አሸንፈዋል።

በፈጣን የጨዋታ እንቅስቃሴ የጀመረው ጨዋታው በሁለቱም ቡድኖች ጥሩ እንቅስቃሴ የታየበት እና በርካታ ዕድሎች የተፈጠሩበት ነበር። በተለይም ባለሜዳዎቹ በርካታ ሙከራዎች ያደረጉበት አጋማሽ ነበር።

በሁለቱም ፈጣን የመስመር ተጫዋቾች መሰረት አድርገው ለማጥቃት የሞከሩት ሽረዎች በተጠቀሰው አጨዋወት በርካታ ዕድሎች ፈጥረዋል። በተለይም አብዱለጢፍ መሐመድ ከመስመር አሻግሮት ሳሊፍ ፎፋና ያመከነው ዕድል እና በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው አብዱልለጢፍ መሐመድ ከመስመር ተጫዋች አታሎ ገብቶ በመምታት ተ/ማርያም ሻንቆ ያዳነው ኳስ ባለሜዳዎቹን መሪ ለማድረግ የተቃረቡ ዕድሎች ነበሩ።

ሽረዎች ከተጠቀሱት ሙከራዎች ውጭም በአክሊሉ ዋለልኝ እና በያስር ሙገርዋ ዕድሎችን ፈጥረው የነበረ ሲሆን በኢትዮጵያ ቡና የኳስ አመሰራረት ስህተቶች የተገኙ ዕድሎችም በርካታ ነበሩ።

በሃያ አራተኛው ደቂቃ ሽረዎች በዲድዬ ለብሪ ግብ አስቆጥረው መሪ መሆን ችለዋል። አማካዩ በሳጥን ውስጥ ያገኛትን ኳስ መትቶ ነበር ያስቆጠረው።

በጨዋታው ከኋላ ኳስ በመመስረት እና ዝግ ባለ የማጥቃት ሽግግር ለማጥቃት የሞከሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች በርካታ ዕድሎች ባይፈጥሩም በታፈሰ ሰለሞን በሁለት አጋጣሚዎች ንፁህ የግብ ዕድል አምክነዋል። አማካዩ ከተካላካዮች አምልጦ ገብቶ ከግብ ጠባቂው አንድ ለአንድ ተገናኝቶ በመምታት ምንተስኖት አሎ በቀላሉ ያዳነው ሙከራ እና አማካዩ በደካማ ውሳኔ አሰጣጥ ያመከናት ወርቃማ ዕድል ይጠቀሳሉ።

ጥቂት የግብ ሙከራዎች እና ፈጣን የ ጨዋታ እንቅስቃሴ በታየበት ሁለተኛው አጋማሽ ሽረዎች በተመሳሳይ አጨዋወት ወደ ሜዳ ሲመለሱ ኢትዮጵያ ቡናዎች የተጫዋች ለውጥ አድርገው በተወሰነ መልኩ የሚያጠቁበት መንገድ ላይ ለውጥ አድርገው ነበር የተመለሱት።

ሙከራ ለማድረግ እንግዶቹ ቀዳሚ ሲሆኑ በእንዳለ ደባልቄ አማካኝነት አቻ ለመሆን ተቃርበው ነበር። ሆኖም ቡናዎች ከኳስ ቁጥጥር ብልጫ ባሻገር ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ተጠግተው ያለቀላቸው የግብ ዕድሎች መፍጠር አልቻሉም።

በአንፃሩ ሽረዎች ከመስመር በሚነሱ ኳሶች በርካታ ዕድሎች ፈጥረዋል። ከነዚህም ረመዳን የሱፍ ከመስመር አሻግሮት ሳሊፍ ፎፋና ያልተጠቀመበት፣ ዲድየ ለብሪ ከተክለማርያም ሻንቆ ጋር ተገናኝቶ ያመከነው፣ አክሊሉ ዋለልኝ ከቅጣት ምት መትቶ ተክለማርያም ሻንቆ እንደምንም ወደ ውጭ ያወጣው እንዲሁም ሳሊፍ ፎፋና በተጫዋቾች የቅብብል ስህተት ያገኘውን ኳስ ሞክሮ አግዳሚውን ጨርፎ የወጣበት ሙከራዎች ለግብ የቀረቡ ነበሩ።

ጨዋታው ከዕረፍት በፊት በተቆጠረው ጎል ተጨማሪ ለውጥ ሳይታይበት በስሑል ሽረ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ