የደቡብ ሠላም የከፍተኛ ሊግ ዋንጫ በሀምበሪቾ አሸናፊነት ተጠናቀቀ

ለአስር ቀናት ያህል ወደ ውድድሩ ዘግይቶ የገባው ዲላ ከተማን ጨምሮ በአምስት ክለቦች መካከል ሲደረግ የነበረው የደቡብ ሰላም የከፍተኛ ሊግ ክለቦች ዋንጫ ሀምበሪቾ ዱራሜን በነጥብ ብልጫ አሸናፊ በማድረግ ተፈፅሟል፡፡

ለሦስተኛ ጊዜ በደቡብ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን እየተመራ ሲደረግ የቆየው ይህ ውድድር ቡታጅራ ከተማ፣ ጌዴኦ ዲላ፣ ሀላባ ከተማ እና ሀምበሪቾ ዱራሜን ከከፍተኛ ሊጉ፤ ጂንካ ከተማን ከአንደኛ ሊግ ያሳተፈ ሲሆን ሁሉም ቡድኖች እርስ በርስ ጨዋታ ካደረጉ በኋላ አብላጫ ነጥብ የሰበሰበው ቡድን አሸነፊ ይሆናል።

ሀምበሪቾ ዱራሜ ትላንት በፍፃሜው ጨዋታ ጌዴኦ ዲላን 2ለ0 በሆነ ውጤት በመርታት በአስር ነጥቦች የውድድሩ አሸናፊ ሆኗል፡፡ ከሁለቱ ጨዋታ በመቀጠል ሀላባ ከተማን ከጂንካ ከተማ አገናኝቶ ሀላባ 1ለ0 በማሸነፍ በአንድ ነጥብ ከሻምፒዮኑ አንሶ በኹለተኝነት ውድድሩን ፈፅሟል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የሽልማት ሥነ-ስርዓት በቦታው በተገኙ እንግዶች የተፈፀመ ሲሆን በዚህም መሠረት የሀምበሪቾ ዱራሜው ዳግም በቀለ ኮከብ ግብ አግቢ፣ በረከት ግዛው ከጂንካ የውድድሩ ኮከብ ተጫዋች፣ የሀምበሪቾው አሰልጣኝ ዓለማየሁ አባይነህ ኮከብ አሰልጣኝ ሆነው ተሸልመዋል። ቡታጅራ ከተማ የስፖርታዊ ጨዋነቱን አዘጋጁ ሀላባ ከተማ በምርጥ መስተንግዶ ተሸላሚ ሲሆን ለውድድሩ መሳካት አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት የምስጋና ሰርተፊኬት ከተሰጠ በኃላ የተዘጋጀውን ዋንጫ ሀምበሪቾ ለተከታታይ ሁለተኛ ጊዜ በማንሳት ተጠናቋል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ