የአሰልጣኞች አስተያየት | ጅማ አባ ጅፋር 0–0 ባህር ዳር ከተማ

ከትናንት በቀጠለው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመርያ ሳምንት አዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም ላይ የተካሄደው የጅማ አባ ጅፋር እና የባህር ዳር ጨዋታ 0-0 ከተጠናቀቀ በኋላ አሰልጣኞች ይህን ብለዋል።

“ዛሬ ግን በደጋፊያችን ፊት ብንጫወት ኖሮ አሸንፈን እንወጣ ነበር” ጳውሎስ ጌታቸው – ጅማ አባ ጅፋር

” ለእኔ የሚያስደስተኝ ይሄ ነው፤ በሙሉ ወጣት ተጫዋቾች ናቸው። ቡድናችን ላይ ብዙ ችግሮች አሉ። በዛሬው ጨዋታም ሦስት ወሳኝ የውጭ ተጫዋቾችን አልተጠቀምንም። እንዲሁም ስምንት ተጫዋቾች ከደሞዝ ክፍያ ጋር በተያያዘ በአዳማ ዋንጫ ላይ ከቡድኑ ጋር ማቀናጀት ሳይችሉ ቀርተው ነው በቀጥታ ወደዚህ ጨዋታ ነው የገቡት። በእንቅስቃሴው በጣም ተደስቻለው ተስፋ ሰጪ ነገር አይቻለው። የእኔ መመርያ ይሄ ነው። በሱሉልታ፣ በሀዲያ፣ ዓምና ደግሞ በባህር ዳር እንዲህ ያሉ በወጣቶች የተገነባ ቡድን በመስራት ነው። ከእኔ የተሻለ ስብስብ ካለው፣ በጣም ከተደራጀ ቡድን ጋር ተጫውተን ይህን ውጤት ይዘን መውጣት መልካም ጅማሬ ነው። ዛሬ ግን በደጋፊያችን ፊት ብንጫወት ኖሮ አሸንፈን እንወጣ ነበር።”

” ከዕረፍት መልስ የቡድናችን የተዳከመው አብዛኛዎቹ ተጫዋቾች ከሜዳ የራቁ በመሆናቸው ድካም ተሰምቷቸው እንጂ ጨዋታውን መጨረስ የነበረብን ከእረፍት በፊት ነበር። እንደ ተመለከታችሁት የመስመር አጥቂዎችን ነው አጥቂ አድርገን የተጠቀምነው። የነበሩን ድክመቶች ተቀብለን ውጤታማ ቡድን ለመስራት እስከ መጨረሻው ድረስ እታገላለው”።

” በሁለተኛው አጋማሽ ተጫዋቾቼ የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል” ፋሲል ተካልኝ – ባህር ዳር ከተማ

“እንደ መጀመርያ ጨዋታ ውጤቱ መጥፎ አይደለም። ግን የዛሬውን ጨዋታ በሁለት መንገድ ከፍዬ ነው የማየው። በመጀመርያው አጋማሽ ትንሽ ደካማ ነበርን በተለይ የማጥቃት ሽግግራችን ቀዝቃዛ እና ፍጥነት አልባ ነበር። በቀላሉ የጎል እድል እናገኝ የነበርንበትን አጋጣሚ አበላሽተናል። በሁለተኛው አርባ አምስት ግን ተጫዋቾቼ የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል። ተጭነው ተጫውተዋል፣ ብዙ የጎል እድሎችን ፈጥረዋል፣ በመጨረሻም ማሸነፍ ብንፈልግም ሳይሳካ ቀርቷል። እነዚህን ስህተቶች ለቀጣይ ጨዋታ እናርማለን ”

“ዕድሎችን አለመጠቀም ችግር ታይቶብናል። አንደኛ ሳጥን ውስጥ ያለመረጋጋት፣ ሁለተኛ የውሳኔ ስህተት አይቻለው። ይህ ደግሞ በሥራ የሚመጣ ነው። ዋናው ነገር ወደ ጎል ብዙ መድረሳችን፣ የጎል ዕድል መፍጠራችን ነው። የቀረውን ማሻሻል ይጠበቅብናል።”


© ሶከር ኢትዮጵያ