ወልቂጤ ከፋሲል ከነማ ለሚያደርገው ጨዋታ የስታዲየም ለውጥ አድርጓል

የዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን በበላይነት የሚመራው ዐቢይ ኮሚቴ ባደረገው ግምገማ መሠረት ወልቄጤ ከተማዎች ሜዳቸው በቂ ሆኖ ባለመገኘቱ ለተወሰነ ጊዜ የሜዳ ለውጥ እንዲያደርጉ መወሰኑ የሚታወስ ነው።

የወልቂጤ ቡድን ስታዲየምን ደረጃ የማሻሻል ሥራዎች እየተከወኑ ቢገኙም ግንባታቸው በሚጠበቀው ጊዜ መጠናቀቅ ባለመቻላቸው ለተወሰኑ ወራት በሜዳቸው የሚያደርጓቸውን ጨዋታዎች በተቀያሪ ሜዳ እያደረጉ የሚገኙት ሰራተኞቹ የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታቸውን ባቱ ሼር ሜዳ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ማድረጋቸው እና ያለ ጎል በአቻ ውጤት ማጠናቀቃቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።

ቡድኑ በቀጣይ ቅዳሜ ከፋሲል ከነማ ጋር ለሚያርደርገው ጨዋታ ከቦታ ርቀት አንፃር የቅርብ ጎረቤታቸው ወደሆነው የሆሳዕናው አቢዮ ኤርሳሞ ስታዲየም መዞራቸው ታውቋል። በደብዳቤ ፍቃደኛነታቸውን የገለፁት የሆሳዕና የበላይ ኃላፊዎችም በዚህ ሳምንት ወደ ድሬዳዋ በማምራታቸው ሜዳውን ለጨዋታው ዝግጁ እንደሆነ አያይዘው ገልፀዋል።

በተያያዘ ዜና በቅርቡ የስታዲየማቸውን የመጫወቻ ሜዳ ሳር ለማልበስ የቁፋሮ ስራዎችን አጠናቀው ሳር ማልበስ ስራ ሙሉ ለሙሉ ያጠናቀቁት ወልቂጤ ከተማዎች ሳሩ ሙሉ ለሙሉ ያደገ ቢሆንም የበለጠ ውበት እና ረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጥ በማለት ይህን ሳምንት ከሜዳው ውጪ በማድረግ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ በሜዳው እንደሚያከናውን ይጠበቃል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

error: