ፕሪምየር ሊግ 2ኛ ሳምንት | የሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ 11

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 2ኛ ሳምንት ቅዳሜ ተጀምሮ ትላንት ተገባዷል። በስምንቱ ጨዋታዎች ነጥረው የወጡ 11 ተጫዋቾችን እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

* ምርጫው የሚከናወነው የሶከር ኢትዮጵያ ሪፖርተሮች በተመለከቷቸው ጨዋታዎች ላይ ለተጫዋቾች በሰጡት የተናጠል ነጥብ ላይ የተመረኮዘ ነው።

*አሰላለፍ፡ 3-4-3


ግብ ጠባቂ

ቤሌንጋ ኢኖህ (ሀዋሳ ከተማ)

ግዙፉ ግብጠባቂ መከላከልን መርጠው የገቡት ሀዋሳ ከተማዎች ከሀዲያ ሆሳዕና አንድ ነጥብ ይዘው እንዲወጡ ከፍተኛ ሚና ከተወጡት ተጫዋቾች ውስጥ ከግንባር ቀደሞች ተርታ ይሰለፋል። በጨዋታው ቤሊንጋ ጎል መሆን የሚችሉ አራት አጋጣሚዎችን ያዳነበት ሂደት ለቡድኑ ስለዋለው ውለታ ምስክሮች ናቸው።


ተከላካዮች

ጊት ጋትኮች (ሲዳማ ቡና)

በክረምቱ ሲዳማ ቡናን የተቀላቀለው ጊት ቡድኑ ስሑል ሽረን 4-1 በረታበት ጨዋታ በተክለ ሰውነታቸው ፈርጣማ የሆኑትን የስሁል ሽረ አጥቂዎችን በማቆም ረገድ የተዋጣለት ነበር። በተለይ ቡድኑ ለመልሶ ማጥቃት ተጋላጭ በሚሆንባቸው ወቅቶች በአንድ ለአንድ ላይ ግንኙነቶች ላይም የነበረው ስኬት ተጠቃሽ ናቸው።

መናፍ ዓወል (አዳማ ከተማ)

እርጋትን የተላበሰው መናፍ ቡድኑ ወልቂጤ ከተማን ባሸነፈበት ጨዋታ አስደናቂ ብቃቱን ማሳየት ችሏል። እያንዳንዱ እንቅስቃሴውን በከዕድሜው በቀደመ ማስተዋል የሚጫወተው ወጣቱ ተከላካይ በወልቂጤው ጨዋታ ላይ ጃኮ አራፋትን ከጨዋታው ሙሉ ለሙሉ እንዲነጠል በማድረግ ዓይነተኛ ሚናን ተውጥቷል።

ላውረስ ላርቴ (ሀዋሳ ከተማ)

ከሜዳው ውጪ ነጥብ ተጋርቶ በተመለሰው የአዲሴ ካሳ ስብስብ የመከላከል አደረጃጀትን ከኋላ በመሆን በጥሩ ብቃት ሲመራ ተስተውሏል። ተጫዋቹ እንደ ጊት ጋትኮች ሁሉ ግዙፍ አካላዊ ቁመና ያላቸው የሀዲያ የአጥቂ ተሰላፊዎችን እንቅስቃሴ በመገደብ በኩል ስኬታማ ነበር።


አማካዮች

ይሁን እንደሻው (ሀዲያ ሆሳዕና)

ምንም እንኳን በሜዳቸው ከሀዋሳ ነጥብ ተጋርተው ቢወጡም ይሁን እንደሻው በአዲሱ ቡድኑ የመሀል ሜዳ እንቅስቃሴ በጥሩ ብቃት መምራት ችሏል። በተለይም ለፊት መስመር ተሰላፊ ተጫዋቾች ተደጋጋሚ ተሻጋሪ ኳሶችን በመጣል በኩል የተወጣለት ነበር።

ፍፁም ዓለሙ (ባህር ዳር ከተማ)

ባህርዳር ከተማ መቐለን በረታበት ጨዋታ ፍፁም የግሉየል ብቃቱን ያሳየበት ማራኪ ግብን ከማስቆጠር ባለፈ የቡድኑን የማጥቃት ሒደት በመምራት እንዲሁም ቡድኑ በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ወቅት ሽግግሮችን በማስጀመር ስኬታማ ጨዋታን አሳልፏል።

ሽመክት ጉግሳ (ፋሲል ከነማ)

ታታሪው ሽመክት ቡድኑ ድሬዳዋ ከተማን 5-0 ሲረታ ሁለት ግቦችን ከማስቆጠሩ በዘለለ ሙሉ ሜዳ አካሎ አንድ ጎል በጥሩ ሁኔታ ሲያመቻች በመስመር በኩል ድሬዳዋ ከተማን እረፍት ሲነሳ ውሏል።

ሱራፌል ዳኛቸው (ፋሲል ከነማ)

የፋሲል ከነማ የማጥቃት እንቅስቃሴን የሚያስጀምረው ሱራፌል ድሬዳዋ ከተማን ሲረቱ የማጥቃት እንቅስቃሴን በማስጀመር ከሁሉም ጎሎች ጀርባ አስተዋጽኦ ነበረው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ሲያሻው የጨዋታ እንቅስቃሴን በማፍጠን አሊያም በማዘግየት የጨዋታውን ሂደት በመቆጣጠር ረገድም ውጤታማ ነበር።


አጥቂዎች

አዲስ ግደይ (ሲዳማ ቡና)

ፈጣኑ የመስመር አጥቂ ዘንድሮም የሲዳማ ቡና ውጤት ቁልፍ በእጁ እንዳለ አስመስክሯል። ስሑል ሽረን ሲረቱ በተለይ ከዳዊት ተፈራ የሚላኩትን ረጃጅም ኳሶችን በመቆጣጠር በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረስ ለሽረ ተከላካዮች ከመሆንም ባለፈው በጨዋታው እጅግ ማራኪ የሆነችን የቅጣት ምት ጎል ጨምሮ ሁለት ጎል ማስቆጠር ችሏል።

ሙጂብ ቃሲም (ፋሲል ከነማ)

የፋሲል ሁነኛ የጎል አማራች እየሆነ የመጣው ሙጂብ ቃሲም የውድድር ዘመኑን የመጀመሪያ ሐት-ትሪክ በሳምንቱ መጨረሻ መስራት ችሏል። ምህረት የለሽ ሆኖ የዋለው ሙጂብ በተለይም የመጀመሪያዋን ግብ ሲያስቆጥር ከራሱ የሜዳ ክፍል ኳሱን ያዞ የሄደበትና ተጫዋቾችን አታሎ ያስቆጠረበት መንገድ እጅግ አስደናቂ ነበር።

ካርሎስ ዳምጠው (ወልዋሎ)

ሁለገቡ ካርሎስ በአዲሱ የዮሐንስ ሳህሌ ወልዋሎ ስብስብ ውስጥ የመጀመሪያ ሁለት ሳምንታት እያንፀባረቀ ይገኛል። በሳምንቱ መጨረሻ ወላይታ ድቻን ሲረቱ አንድ ግብ ከማስቆጠርም ባለፈ ጥሩ መንቀሳቀስ ችሏል።


ተጠባባቂዎች

በሳምንቱ መልካም እንቅስቃሴ ካደረጉ ተጫዋቾች መካከል በግብ ጠባቂ ሥፍራ የወላይታ ድቻው መክብብ ደገፉ፣ በተከላካይ ስፍራ ሁለት ኳሶችን ለጎል በማመቻቸት ስኬታማ ቀን ያሳለፈው የፋሲል ከነማው የቀኝ መስመር ተከላካይ ሰዒድ ሀሰን እና ጥሩ የመከላከል እንቅስቃሴ ያሳየው የቅዱስ ጊዮርጊሱ ኤድዊን ፍሪምፖንግ፣ በአማካይ ስፍራ የሀዲያ ሆሳዕናው አማካይ አፈወርቅ ኃይሉ ሁለት ኳሶችን በማመቻቸት ለባህር ዳር ድል ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከተው የመስመር አጥቂው ወሰኑ ዓሊ፣ በተመሳሳይ ከመስመር እየተነሳ አደጋ ከመፍጠር ባለፈ አንድ ኳስ አመቻችቶ አንድ ጎል ያስቆጠረው ሀብታሙ ገዛኸኝ እና ብቸኛዋን ጎል አስቆጥሮ አዳማን ለድል ያበቃው ዳዋ ሆቴሳ የሳምንቱ ምርጥ 11 ውስጥ በተጠባባቂነት የተያዙ ተጫዋቾች ናቸው።


© ሶከር ኢትዮጵያ