“ያለኝን እና አቅሜ የሚፈቅደውን ሁሉ ለባህር ዳር ከተማ ለመስጠት ዝግጁ ነኝ” ፍፁም ዓለሙ

ባለፉት ዓመታት ከፋሲል ከነማ ጋር ጥሩ ጊዜ ያሳለፈና ዘንድሮ ለባህር ዳር ከተማ በመፈረም ጥሩ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው የአማካይ መስመር ተጨዋቹ ፍፁም ዓለሙ በወቅታዊ አቋሙ ዙሪያ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል።


በቅድሚያ ከመጠሪያ ስምህ ልነሳ። ለምን ከኤፍሬም ወደ ፍፁም ቀየርክ? ብዙዎች ኤፍሬም ዓለሙ በሚል ስያሜህ ነው የሚያውቁህ..

ስሜን የቀየርኩት በወላጅ እናቴ ምክንያት ነው። ከልጅነት ጀምሮ እናቴ ፍፁም እንድባል ነበር የምትፈልገው። ሰፈር ውስጥም ሆነ ቤት ውስጥ ፍፁም እየተባልኩ ነበር የምጠራው። ነገር ግን በልጅነቴ አያቴ ትምህርት ቤት ሲያስገባኝ በስህተት ኤፍሬም ብሎ አስመዘገበኝ። በእዚህ አጋጣሚ ነው ዋነኛ ስሜ ኤፍሬም ሆኖ የቀረው። ከወራት በፊት ግን እናቴ ያወጣችልኝን ስም አስጸድቄ ፍፁም እየተባልኩ መጠራት ጀምሬያለሁ።

ባህር ዳር ከተማን እንዴት ተቀላቀልክ? የክለቡንስ ደጋፊዎች እንዴት አገኘሃቸው?

ወደ ባህር ዳር ከተማ የመጣሁት ፍላጎት ስላለኝ ነው። ከፋሲል ከነማ ጋር ያለኝ ውል በመጠናቀቁ እና ክለቡ ያቀረበልኝን ውል ባለመቀበሌ ነው ወደ እዚህ የመጣሁት። የቡድኑን ደጋፊዎች በጣም ልዩ ናቸው። ብድኑ አሸነፈም፣ ተሸነፈም አቻ ወጣም ከቡድኑ አይለዩም። ከመምጣቴ በፊት ስለማቃቸው ብዙም አዲስ አለሆነብኝም። ለእኔ ያደረጉትም አቀባበል ጥሩ ነበር።

በዋና አሰልጣኝነት የመጀመሪያ ክለቡን በያዘው ፋሲል ተካልኝ ነው የምትሰለጥኑት። አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝን እንዴት አገኘኸው?

ከዚህ በፊት ከፋሲል ተካልኝ ጋር አብሬ አልሰራሁም። አሁን እዚህ ተገናኝተናል። ፋሲል በጣም ጥሩ አሰልጣኝ ነው። የሚያሰራን ልምምዶችም በጣም ጥሩ እና ብቃታችንን የሚያጎለብቱ ናቸው። በአብዛኛው ደግሞ ከኳስ ጋር የተገናኙ ልምምዶችን ስለሚያሰራን በደስታ ነው የምንቀበለው። በአጠቃላይ እየሰጠን ያለው ነገር በግሌ ተመችቶኛል።

የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ውድድር እንዴት ነበር? በቋሚነት ከተሰለፍክበት ሁለት ጨዋታዎች በአንዱ ኮከብ በመባል ተመርጠካል። ጠቅለል አድርገህ የሲቲ ካፑን ቆይታ ገምግምልኝ?

እንደሚታወቀው የሲቲ ካፕ ውድድሮች ቡድንን ለመመልከቻነት ነው የሚጠቅሙት። ከዚህ አንፃር በውድድሩ እኛ የቡድናችንን ውህደት ለማምጣት እና በዋናው ውድድር የምንከተለውን አጨዋወት ለመሞከር ጥረናል። ኮከብ ሆኜ የተመረጥኩበት ጨዋታን በተመለከተ አንድ ተጨዋች ኮከብ ሆኖ መመረጥ ስላለበት ነው እንጂ ሁሉም የቡድን ጓደኞቼ በጨዋታው ኮከብ ነበሩ። ሁላችንም ተጋግዘን ነው ጨዋታውን ያከናወነው። ስለዚህ እኔ ብቻ በግል ያደረኩት ጥረት አደለም የቡድን ጓደኞቼም ጭምር እንጂ።

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቡድኑ ስላደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች…

አዳማ ላይ ከጅማ አባጅፋር ጋር የተጫወትንበት ጨዋታ አስቆጪ ነበር። ብዙ ኳሶችን ወደ ግብ ክልል ይዘን እየሄድን አምክነናል። ይህንን ስህተቶቻችንን ተመርኩዘን ከአዳማ ከተመለስን በኋላ ግብ ክልል አካባቢ ያተኮሩ ልምምዶችን ሰርተናል። በዚህም ስህተቶቻችንን በመቐለው ጨዋታ አስተካክለን ለመቅረብ ሞክረናል። እንዳያችሁትም የዓምና የሊጉን አሸናፊ ገጥመን ሦስት ግቦች አስቆጥረናል። ስለዚህ ይህንን ጥሩ ጎን እናስቀጥላለን። ነገር ግን ቡድናችን ድክመቶች የሉበትም ማለት አደለም። ድክመቶቻችን ለመቅረፍ በየቀኑ ስራዎችን እየሰራን እንሄዳለን።

በመቐለው ጨዋታ ጥሩ ስትንቀሳቀስ ነበር። የመጀመሪያ የሜዳችሁ ላይ ጨዋታም ድንቅ ግብ አስቆጥረህ ከደጋፊዎች ጋር በጥሩ ስሜት ተሳሰረሃል (መለያ አውልቆ ደስታ በመግለፅ)። ያቺን ልዩ ግብ ስታስቆጥር ምን ተሰማህ?

ልክ ነው አሪፍ ጎል አስቆጥሬያለሁ። ግብ ካስቆጠርኩ በኋላ በሚገባ ደስታዬን ከደጋፊዎቻችን ጋር ገልጫለሁ። እኔ ሜዳ ላይ መሸነፍ አልወድም። ለዚህም ነው ግብ ሳስቆጥር ስሜታዊ ሆኜ ደስታዬን የገለፅኩት። በጨዋታው ላይ ደግሞ ከፍተኛ ፉክክር ስለነበር ግብ ሳስቆጥር በጣም ደስ አለኝ።

በእዚህ ዓመት የባህር ዳር ከተማ ደጋፊዎች ከፍፁም ዓለሙ ምን ይጠብቁ?

ፈጣሪ ከፈቀደ የተሻለ ነገር ለመስራት አስባለሁ። ያለኝን እና አቅሜ የሚፈቅደውን ሁሉ ለባህር ዳር ከተማ ከተማ ለመስጠት ዝግጁ ነኝ። እኔ እና የቡድን ጓደኞቼ ተጋግዘን ውቡን የባህር ዳር ከተማ ደጋፊ የሚመጥን ስራዎችን ለመስራት አቅደናል። በግሌ ያለኝን ሳልሰስት ለክለቡ ለመስጠት ተዘጋጅቻለሁ።

እንደ ቡድን ባህር ዳር ከተማ በዘንድሮ የውድድር ዓመት ያቀደው እቅድ ምንድን ነው?

ከምንም በላይ ቡድናችን ጥሩ ተፎካካሪ እንዲሆን ነው የምንፈልገው። ዐምና ፋሲል ከነማ ጋር የነበረውን ነገር በጣም ደስ ይል ነበረ። እስከ መጨረሻው እለት ድረስ የዋንጫ ተፎካካሪ ሆኖ መቀጠል ያስደስታል። ይህ ደግሞ ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለሊጉም ውበት እና ድምቀት ወሳኝ ነው። ስለዚህ ዋነኛ ግባችን ጥሩ ተፎካካሪ ሆኖ ውድድሩን ማከናወን የሚል ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ